Get Mystery Box with random crypto!

††† እንኳን ለአባታችን ቅዱስ አጋቢጦስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። † | ✞ገድለ ቅዱሳን✞

††† እንኳን ለአባታችን ቅዱስ አጋቢጦስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ አጋቢጦስ †††

††† ቅዱስ አጋቢጦስ:-
*ይህንን ዓለም ንቆ ለበርካታ ዘመናት በፍፁም ምናኔ የኖረ::
*ምድራዊ ሃብትና ሹመት ሞልቶለት ሳለ ከሁሉ የክርስቶስን ፍቅር የመረጠ::
*ከደግነቱ ብዛት የተነሳ ምግብ ሲያዘጋጅ ሽምብራውን ከክቶ ለሌሎች ከሰጠ በሁዋላ ለራሱ የሚመገበው ገለባውን (አሠሩን) ነበር::

ሌሊቱን በጸሎት ለመትጋት ማታ ማታ አመድ ይመገብ ነበር:: በዚህም ቅዱስ ዳዊት "አመድን እንደ እህል በላሁ" ያለው በዚህ ቅዱስ ሕይወት ላይ ተገልጧል:: (መዝ. 101:9)

ቅዱስ አጋቢጦስ በዘመኑ ከሠራቸው ይህኛው እጅግ ይገርመኛል:: እርሱ በበርሃ የነበረበት ዘመኑ የሰማዕታት በመሆኑ ብዙ ክርስቲያኖች በርጉማን መክስምያኖስና ዲዮቅልጢያኖስ ተገድለዋል:: ቅዱሱን ግን በአካባቢው የነበረ ሃገረ ገዢ ከበዓቱ አስወጥቶ ወደ ውትድርና ሥራ አስገብቶታል::

ሰይጣን በዚህ ከተጋድሎና ከቅድስና ሕይወት እንደሚያርቀው ተማምኖ ነበር:: ቅዱስ አጋቢጦስ ግን በወታደሮች መካከል ሆኖም ተጋድሎውን ቀጠለ:: የጦር ሠራዊት አለቃ አድርገው ቢሾሙትም እርሱ ከበጐ ማንነቱ ፈጽሞ አልተለወጠም::

ክርስቲያን ማለት እንዲህ ነውና:: ክርስትና ሲመቸን : ሲመቻችልን : በአጋጣሚ ወይም በምክንያት የምንኖረው ሕይወት አይደለም:: ፍጹም ፍቅር የጊዜ : የቦታ : የሁኔታ ገደብ የለውምና አባቶቻችን በጊዜውም : ያለ ጊዜውም ጸንተው ክርስቶስ መድኃኒታችንን አስደሰቱ::

ከቅዱስ ዻውሎስ ጋርም እንዲህ ሲሉ ዘመሩ:- "መኑ ያኀድገነ ፍቅሮ ለክርስቶስ" (ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል!)

ወደ ቀደመው ነገራችን እንመለስና ቅዱስ አጋቢጦስ ለዘመናት ሰው ሳይገድል : ፈጣሪውን ሳይበድል : ከጾም ከጸሎት : ከምጽዋትና ትሕርምት ሳይጐድል ኖረ:: በዚህም ሰይጣንን አሳፈረ:: ዘመነ ሰማዕታትም አለፈ::

በዚህ ጊዜም ወደ በዓቱ ለመመለስ መንገድን ይፈልግ : ይጸልይም ገባ:: እግዚአብሔርም ወደ በርሃ የሚመለስበትን መንገድ በቸርነቱ አቀናለት::
ነገሩ እንዲህ ነው::
ዘመነ ሰማዕታት አልፎ ራትዕ (የቀና) ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ነገሠ:: ስደት ቆመ:: የታሠሩ ተፈቱ:: አብያተ ክርስቲያናት ታነጹ:: ለክርስቲያን ቀደምቶቻችንም ታላቅ ተድላ ሆነ::

ጊዜው ለሁሉ ክርስቲያን የተድላ ቢሆንም አንድ ወጣት በደዌ ሰይጣን ያሰቃየው ነበር:: ወጣቱ የንጉሡ የቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ባለሟል : ባለብዙ ሃብት : መልኩ ያማረ ነውና ሁሉ ያዝንለታል:: ይልቁኑ ቅዱሱ ንጉሥ ተጨነቀለት::

አንድ ቀን ግን ከወታደሮቹ አንዱ ያን ወጣት "አንተንኮ አጋቢጦስ ይፈውስህ ነበር" ይለዋል:: ወጣቱ ግን አላወቀምና "ከመቼ ወዲህ የጦር አለቃ እንዲህ አድርጐ ያውቃል?" ሲል በጥያቄ ይመልስለታል:: ወታደሩ ግን ቀስ አድርጐ ምሥጢሩን ይነግረዋል::

ይህ ነገር ሲያያዝ ከንጉሡ ደርሶ ቅዱስ አጋቢጦስን አስጠርቶ "እባክህ ፈውስልኝ?" ይለዋል:: "ካዳንክልኝም የፈለግኸውን አደርግልሃለሁ" ሲል ያክልለታል:: ቅዱስ አጋቢጦስም ወደ ፈጣሪው ለምኖ ሰይጣንን ይገስጸዋል:: በቅጽበትም በክርስቶስ ኃይል ወጣቱ ይድናል::

ቅዱስ ቆስጠንጢኖስም ከደስታው ብዛት "ምን ላድርግልህ?" ቢለው ቅዱሱ "ከሹመቴ ሻረኝ : ወደ በርሃ አሰናብተኝ" ብሎ መሻቱን ገለጸለት:: ቅዱሱ ንጉሥም በመገረም ቡራኬውን ተቀብሎ ወደ በርሃ ሸኝቶታል::

ወገኖቼ! . . . በዓለማዊም ሆነ በመንፈሳዊው እርከን ስልጣንን የሚንቁ ሰዎችን ካላገኘን መፍትሔው ሩቅ ነው:: እኛም ከሥልጣን መሻት እንራቅ:: ማር ይስሐቅ እንደ ነገረን ሰይጣን ያደረበት ሰው ሹመትን (ሥልጣንን) በመሻቱ ይታወቃልና::

ቅዱሱ በፍፃሜ ዘመኑ እረኝነት (ዽዽስና) ተሹሞ ብዙ ኢ-አማንያንን ወደ ክርስትና መልሶ: ድውያንን ፈውሶ: እውራንን አብርቶ: በርካታ ተአምራትንም አድርጎ በዚህች ቀን አርፏል::

††† ልመናው በረከቱ ይደርብን::

††† የካቲት 24 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አጋቢጦስ (ጻድቅ ኤዺስቆዾስ)
2.ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሰማዕት (ዘጋዛ)
3.ቅዱስ ሚናስ ዘቆዽሮስ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት (መምሕረ ትሩፋት)
2.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
3.ቅዱስ ሙሴ ፀሊም
4.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
5.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
6."24ቱ" ካኅናተ ሰማይ (ሱራፌል)

††† "የሚያሳድዷችሁን መርቁ . . . ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ:: ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ:: እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ:: የትዕቢትን ነገር አታስቡ:: ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ::" †††
(ሮሜ. 12:14-16)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††