Get Mystery Box with random crypto!

††† እንኳን ለታላቁ ሐዋርያና ሰማዕት ቅዱስ ፖሊካርፐስ እና ቅዱስ አውሳብዮስ ሰማዕት ዓመታዊ የዕ | ✞ገድለ ቅዱሳን✞

††† እንኳን ለታላቁ ሐዋርያና ሰማዕት ቅዱስ ፖሊካርፐስ እና ቅዱስ አውሳብዮስ ሰማዕት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!†††

††† ቅዱስ ፖሊካርፐስ †††

†††ቅዱስ ፖሊካርፐስ:-
*ከ70 እስከ 156 ዓ/ም የነበረ::
*ዮሐንስ ወንጌላዊ በራዕዩ ከመሰከረላቸው 7ቱ አብያተ ክርስቲያናት የአንዱ (የሰርምኔስ) ዻዻስ የነበረ::
*ከሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ቃል በቃል የተማረና ደቀ መዝሙሩ የነበረ አባት ነው::

ታላቁ አግናጥዮስ (ምጥው ለአንበሳ) የዚህ ቅዱስ ባልንጀራ ነበር:: ከ46 ዓመታት በላይ በፍፁም ትጋት ቤተ ክርስቲያንን አገልግሎ አረማውያን በ86 ዓመቱ በአደባባይ በእሳት አቃጥለው ገድለውታል:: አባቶቻችን "ሐዋርያዊ" ሲሉ ይጠሩታል::

††† ዳግመኛ በዚህ ዕለት በ1888 ዓ/ም በቅዱስ ጊዮርጊስ ምልጃና ረዳትነት አባቶቻችን አድዋ ላይ ጣልያንን ድል አድርገዋል:: ቅዱስ ጊዮርጊስን እና ደጉን ንጉሥ ዳግማዊ አፄ ምኒልክን እናስባቸው ዘንድ ይገባል::

††† ቅዱስ አውሳብዮስ ሰማዕት †††

በቤተ ክርስቲያን ስመ ጥር ከሆነ ቅዱሳን ሰማዕታት አንዱ ቅዱስ አውሳብዮስ ነው:: ተወልዶ ያደገው በምድረ አንጾኪያ (ሶርያ) ሲሆን ዘመኑም 3ኛው መቶ ክ/ዘ ነው:: አባቱ ታላቁ ሰማዕት ቅዱስ ፋሲለደስ ነው:: እናቱም ቡርክት ሶፍያ ትባላለች::

ሰማዕቱ ቅዱስ መቃርስ ትንሽ ወንድሙ መሆኑም ይታወቃል:: ቅዱሳን እነ ፊቅጦር : ገላውዴዎስ : ቴዎድሮስ : ዮስጦስ : አባዲር . . . ባልንጀሮቹ ሆነው ኑረዋል::

ቅዱስ አውሳብዮስ የቅዱስ ፋሲለደስ ፍሬ ነውና ጾምና ጸሎትን የሚያዘወትር ሆነ:: በቤተ መንግስት ውስጥ ስንት የተደላደለና የተቀማጠለ ነገር እያለ እርሱ ግን እንደ ቡሩክ አባቱ ንጽሕናን መረጠ:: የወርቅ ካባ ደርቦ ሲሰግዱ ማደር ምን ይደንቅ!

ያ ዘመን እጅግ ግሩም የሆኑ ቅዱሳን በቤተ መንግስት የታዩበት ነበር:: ቅዱስ አውሳብዮስ በምጽዋት : በጾምና ጸሎት የሚኖር ቢሆንም በየጊዜው ወደ ጦርነት ይላክ ነበር:: ምክንያቱም እርሱ ኃያል የጦር ሰው : የሠራዊቱም ሁሉ አለቃ ነውና:: በሔደበት ሁሉም በእግዚአብሔር ኃይል ድል ያደርግ ነበር::

አንድ ጊዜም ከፋርስ ቁዝ ሰዎች ጋር ጦርነት ውስጥ ገቡ:: ይህንን ጦርነት በበላይነት እንዲመሩ ቅዱሳን አውሳብዮስና ዮስጦስ በኑማርያኖስ (ንጉሡ ነው) ተሹመው ወደ ሠልፍ ገቡ::

በጦርነቱ ጐዳና ላይ ሳሉ ግን አንድ አታላይ ሰላይ በጠላት እጅ እንዲወድቁ አደረጋቸው:: የተማረኩና የታሠሩ ዮስጦስና ሠራዊቱ ሲሆኑ ቅዱስ አውሳብዮስ ይህን ሰምቶ አለቀሰ:: ወደ ፈጣሪውም እየተማጸነ ለመነ::

በዚህ ጊዜ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማይ ወርዶ አረጋጋው:: ድል መንሳትንም ሰጥቶት አደጋ ጥሎ ባልንጀራውን ዮስጦስን አስፈታው:: ጠላቶቻቸውንም እያሳደዱ አዋረዷቸው:: "ወመጠውከኒ ዘባኖሙ ለጸርየ" እንዳለ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ::

ከዚህ ሠልፍ በሁዋላ ቅዱሳን አውሳብዮስና ዮስጦስ በድል አድራጊነት ወደ አንጾኪያ ሲመለሱ ግን አንጀትን የሚቆርጥ ዜና ደረሳቸው:: አምላከ አማልክት ክርስቶስ ተክዶ ጣዖታት (እነ አዽሎን : አርዳሚስ) እየተሰገደላቸውም ደረሱ:: ይህንን ያደረገ ደግሞ የሰይጣን ታናሹ የሆነ ርጉም ዲዮቅልጢያኖስ ነው::

ቅዱሳኑንም ለጣዖት ስገዱ ሲል በአደባባይ ጠየቃቸው:: ድፍረቱ ያናደደው ቅዱስ አውሳብዮስ ግን ሰይፉን መዞ ወደ ንጉሡ ተራመደ:: ያን ጊዜ ንጉሡ ሸሽቶ ሲያመልጥ መሣፍንቱን ሜዳ ላይ በተናቸው:: አባቱ ቅዱስ ፋሲለደስ ባይገለግለው ኖሮ ኃያል ነውና ባላተረፋቸው ነበር::

ከቀናት በሁዋላ ግን ቅዱስ አውሳብዮስ በጾምና ጸሎት ሰንብቶ ሰማዕት ለመሆን ልቡ ቆረጠ:: ቅዱስ ሚካኤልና አባቱ ፋሲለደስም በምክር አበረቱት:: እርሱም በአጭር ታጥቆ በከሐዲው ንጉሥ አደባባይ ላይ ቆመ::

"እኔ ክርስቲያን ነኝ:: ክርስቶስን አመልካለሁ:: ለእርሱም እገዛለሁ:: ጣዖታት ግን ድንጋዮቸ ናቸውና አይጠቅሙም:: የሚሰግድላቸውም የረከሠ ነው::" ሲል አሰምቶ ተናገረ:: ንጉሡ ዲዮቅልጢያኖስ እዚያው ሊገድለው ፈልጐ ነበር:: ቅዱሱ ተወዳጅ ሰው ነበርና ሁከት እንዳይነሳ አውሳብዮስ ወደ አፍሪቃ (ግብጽ) ሒዶ እንዲገደል ተወሰነበት::

በምድረ ግብጽም አረማውያን በእሳትም : በግርፋትም : በስለትም ብዙ አሰቃዩት:: ቅዱስ ሚካኤል ግን ገነትን አሳይቶ ከደዌው እየፈወሰ ተራዳው:: በመጨረሻም በዚህች ቀን ገድለውት አክሊለ ክብርን ተቀዳጅቷል::

††† አምላከ ቅዱሳን ሰማዕታት ጽናታቸውን አድሎ ከበረከታቸው ይክፈለን::

††† የካቲት 23 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ፖሊካርፐስ ሐዋርያዊ ሰማዕት (የሰርምኔስ ዻዻስ)
2.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት (አባቶቻችንን አድዋ ላይ የረዳበት)
3.ቅዱስ አውሳብዮስ ሰማዕት (የቅዱስ ፋሲለደስ ልጅ)
4.ቅዱስ አውስግንዮስ ሰማዕት

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
2.ቅዱስ ሰሎሞን ንጉሠ እስራኤል
3.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
4.አባ ሳሙኤል
5.አባ ስምዖን
6.አባ ገብርኤል

††† "በሰርምኔስም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልዐክ እንዲህ ብለህ ጻፍ:- ሞቶ የነበረው: ሕያውም የሆነው: ፊተኛውና መጨረሻው እንዲህ ይላል:-
'መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ . . . እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን: የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ::" †††
(ራእይ 2:8)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††