✞ ✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞ ✞ ❖የካቲት ፳፪ (22) ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት + " አቡነ አቢብ (አባ ቡላ) " + +ይህን ታላቅ ቅዱስ በምን እንመስለዋለን! *እኛ ኃጥአን ጣዕመ ዜናውን: ነገረ ሕይወቱን ሰምተን ደስ ተሰኝተናል! *ቅዱሱ አባታችን:- "ቡላ-የእግዚአብሔር አገልጋይ" ብለን እንጠራሃለን:: *ዳግመኛም "አቢብ-የብዙኃን አባት" ብለን እንጠራሃለን:: +እርሱ ቅሉ አባትነትህ አንተን ለመሰሉ ቅዱሳን ቢሆንም እኛን ኃጥአንን ቸል እንደማትለንም እናውቃለን:: *አባ! ማነው እንዳንተ የክርስቶስን ሕማማት የተሳተፈ! *ማን ነው እንዳንተ በፈጣሪው ፍቅር ብዙ መከራዎችን የተቀበለ! *ማንስ ነው እንዳንተ በአንዲት ጉርሻ አማልዶ ርስትን የሚያወርስ! *የፍጡራንን እንተወውና በፈጣሪ አንደበት ተመስግነሃልና ቅዱሱ አባታችን ላንተ ክብር: ምስጋናና ስግደት በጸጋ ይገባሃል እንላለን:: +" ልደት "+ +አባታችን አቡነ አቢብ የተወለደው በ3ኛው መቶ ክ/ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ሲሆን ሃገረ ሙላዱ ሮሜ ናት:: ወላጆቹ ቅዱስ አብርሃምና ቅድስት ሐሪክ እጅግ ጽኑ ክርስቲያኖች ነበሩ:: ልጅ ግን አልነበራቸውም:: ዘመነ ሰማዕታት ደርሶ ስደት በሆነ ጊዜ እነርሱም በርሃ ገቡ:: +በዚያም ሳሉ በቅዱስ መልአክ ብሥራት ሐሪክ ጸንሳ ብሩሕ የሆነ ልጅ ወለደች:: ቅዱሱ ሕጻን ሲጸነስ ማንም ሳይተክለው የበቀለው ዛፍ ላይ መልአኩ እንዲህ የሚል የብርሃን ጽሑፍ ጽፎበት ወላጆቹ ዐይተዋል:: "ቡላ ገብሩ ለእግዚአብሔር: ወቅዱሱ ለአምላከ ያዕቆብ: ዘየኀድር ውስተ ጽዮን" +" ጥምቀት "+ +ቅዱሱ ሕጻን ከተወለደ በኋላ ሳይጠመቅ ለ 1 ዓመት ቆየ:: ምክንያቱም ዘመኑ የጭንቅ ነውና ካህናትን እንኳን በዱር በከተማም ማግኘት አይቻልም ነበር:: እመቤታችን ግን ወደ ሮሙ ሊቀ ዻዻሳት አባ ሰለባስትርዮስ ሒዳ አጥምቀው አለችው:: +ወደ በርሐ ወርዶ ሊያጠምቀው ሲል ሕጻኑ ተነስቶ: እጆቹንም ዘርግቶ:- "አሐዱ አብ ቅዱስ: አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውዕቱ መንፈስ ቅዱስ" ብሎ አመስግኖ ተጠመቀ:: ከሰማይም ሕብስና ጽዋዕ ወርዶላቸው ሊቀ ዻዻሳቱ ቀድሶ ሁሉንም አቆረባቸው:: የሕጻኑ ወላጆች "ለልጃችን ስም አውጣልን" ቢሉት "ቡላ" ብሎ ሰየመው:: እነርሱም ምሥጢሩን ያውቁ ነበርና አደነቁ:: +" ሰማዕትነት "+ +የቅዱሱ ቡላ ወላጆች ለ10 ዓመታት አሳድገውት ድንገት ሕዳር 7 ቀን ተከታትለው ዐረፉ:: ሕጻኑን የማሳደግ ኃላፊነትን የአካባቢው ሰዎች ሆነ:: ሕጻኑ ቡላ ምንም የ10 ዓመት ሕጻን ቢሆንም ያለ ማቁዋረጥ ሲጾም: ሲጸልይ ክፉ መኮንን "ለጣዖት ስገዱ" እያለ መጣ:: +በዚህ ጊዜ በሕጻን አንደበቱ አምልኮተ ክርስቶስን ሰበከ:: በዚህ የተበሳጨ መኮንኑ ስቃያትን አዘዘበት:: በጅራፍ ገረፉት: በዘንግ ደበደቡት: ቆዳውን ገፈፉት: በመጋዝ ቆራርጠውም ጣሉት:: ነገር ግን ኃይለ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበርና 2 ጊዜ ከሞት ተነሳ:: በመጨረሻ ግን ሚያዝያ 18 ቀን ተከልሎ ሰማዕት ሆኗል:: +" ገዳማዊ ሕይወት "+ +ቅዱስ ቡላ ሰማዕትነቱን ከፈጸመ በኋላ ቅዱስ ሚካኤል በአክሊላት አክብሮ ወስዶ በገነት አኖረው:: ከሰማዕታትም ጋር ደመረው:: በዚያም ቡላ ቅዱስ ጊዮርጊስን ተመልክቶ ተደነቀ:: መንፈሳዊ ቅንዐትን ቀንቷልና "እባክህን ወደ ዓለም መልሰኝና ስለ ፍቅርህ እንደ ገና ልጋደል" ሲል ጌታን ለመነ:: +ጌታችን ግን "ወዳጄ ቡላ! እንግዲህስ ሰማዕትነቱ ይበቃሃል:: ሱታፌ ጻድቃንን ታገኝ ዘንድ ግን ፈቃዴ ነውና ሒድ" አለው:: ቅዱስ ሚካኤልም የቅዱስ ቡላን ነፍስ ከሥጋው ጋር አዋሕዶ: ልብሰ መነኮሳትንም አልብሶ ግብጽ በርሃ ውስጥ አኖረው:: +" ተጋድሎ "+ +አባ ቡላ ወደ በርሃ ከገባ ጀምሮ ዐርብ ዐርብ የጌታን ሕማማት እያሰበ ራሱን ያሰቃይ ገባ:: ራሱን ይገርፋል: ፊቱን በጥፊ ይመታል: ሥጋውን እየቆረጠ ለአራዊት ይሰጣል: ከትልቅ ዛፍ ላይ ተሰቅሎ ወደ ታች ይወረወራል:: +በጭንቅላቱ ተተክሎ ለብዙ ጊዜ ጸልዮ ጭንቅላቱ ይፈሳል:: ሌላም ብዙ መከራዎችን የጌታን ሕማማት እያሰበ ይቀበላል:: ስለ ጌታ ፍቅርም ምንም ነገር ሳይቀምስ ለ42 ዓመታት ጹሟል:: ጌታችንም ስለ ክብሩ ዘወትር ይገለጥለት ነበር:: +የሚታየውም እንደ ተወለደ: እንደ ተጠመቀ: እንደ ተሰቀለ: እንደ ተነሳ: እንዳረገ እየሆነ ነበር:: አንድ ቀንም ጌታችን መጥቶ "ወዳጄ ቡላ! እንዳንተ ስለ እኔ ስም መከራ የተቀበለ ሰው የለም:: አንተም የብዙዎች አባት ነሕና ስምህ አቢብ (ሃቢብ) ይሁን" አለው:: "እስከ ይቤሎ አምላክ ቃለ አኮቴት ማሕዘኔ: ረሰይከኑ ለባሕቲትከ ኩነኔ: ዘመጠነዝ ታጻሙ ነፍስከ በቅኔ" እንዲል:: +" ዕረፍት "+ +አቡነ አቢብ ታላቁ ዕብሎን ጨምሮ በርካታ ደቀ መዛሙርትን አፈራ:: ከእመቤታችን ጋርም ዕለት ዕለት እየተጨዋወተ ዘለቀ:: በተጋድሎ ሕይወቱም ከ10 ጊዜ በላይ ሙቶ ተነስቷል:: በዚህች ቀን ሲያርፍ ገዳሙ በመላእክት ተሞላ:: +ጌታም ከድንግል እናቱ ጋር መጥቶ "ወዳጄ ቡላ! ስምህን የጠራውን: መታሰቢያህን ያደረገውን እምርልሃለሁ:: አቅም ቢያጣ አምላከ አቢብ ማረኝ ብሎ 3 ጊዜ በዕለተ ዕረፍትህ የሚለምነኝን: በስምሕ እንኳ ቁራሽ የሚበላውን ሁሉ እምርልሃለሁ" ብሎት ነፍሱን በክብር አሳረገ: በሰማይም ዕልልታ ተደረገ:: ✞አምላከ ጻድቃን ወሰማዕት በቃል ኪዳናቸው እንዲምረን ቸርነቱ ይርዳን:: በረከታቸውንም አትርፎ ይስጠን:: ✞ ✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞ ✞ 655 views04:07