✞ ✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞ ✞ ❖የካቲት ፲፰ (18) ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት +*" ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ "*+ =>ቅዱስ ያዕቆብ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያደገ: የአረጋዊው ቅ/ዮሴፍ የመጨረሻ ልጅ : በንጽሕናውና ድንግልናው የተመሠከረለት : ከጸሎትና ገድል ብዛት እግሩ ያበጠ : የመጀመሪያው የኢየሩሳሌም ኤዺስ ቆዾስ ሲሆን ቁጥሩም ከ72ቱ አርድዕት ነው:: ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:- =>ይህ ቅዱስ ሐዋርያ በአባቶቻችን ሐዋርያት መካከል ትልቅ ሞገስ የነበረውና የጌታችን ወንድም ተብሎ የተጠራ ነው:: ቅዱስ ያዕቆብ ወላጅ አባቱ አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ (የእመቤታችን ጠባቂ) ሲሆን በልጅነቱ ጥላው የሞተችው እናቱ ደግሞ ማርያም ትባላለች:: በቤት ውስጥም ስምዖን: ዮሳና ይሁዳ የተባሉ ወንድሞችና ሰሎሜ የምትባል እህትም ነበረችው:: +እናቱ ማርያም ከሞተች በሁዋላ ዕጉዋለ ማውታ (ደሃ አደግ) ሆኖ ነበር:: ነገር ግን በፈቃደ እግዚአብሔር አረጋዊ ዮሴፍ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ከቤተ መቅደስ ሊጠብቃት (ሊያገለግላት) ተቀብሎ ሲመጣ ያ ቤተሰብ ተቀየረ:: የበረከት: የምሕረትና የሰላም እመቤት የአምላክ እናቱ ገብታለችና ያ የሐዘን ቤት ደስታ ሞላው:: +እመ ብርሃን ግን ገና ወደ ዮሴፍ ልጆች ስትደርስ አለቀሰች:: የአክስቷ ልጆች የሚንከባከባቸው አጥተው ቆሽሸው ነበር:: በተለይ ደግሞ ትንሹ ቅዱስ ያዕቆብ ያሳዝን ነበር:: እመ ብርሃን ማረፍ አልፈለገችም:: ወዲያው ማድጋ አንስታ ወደ ምንጭ ወርዳ ውሃ አምጥታ የሕጻኑን ገላ አጠበችው:: (በአምላክ እናት የታጠበ ሰውነት ምስጋና በጸጋ ይገባዋል!) +እመቤታችን ጌታ ከመወለዱ በፊት ለ9 ወራት: ከተወለደ በሁዋላ ደግሞ ለ2 ዓመታት ሕጻኑን ያዕቆብን ተንከባከበችው:: ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት ግን ድንግል ማርያም አምላክ ልጇን ይዛ ተሰዳለችና ተለያዩ:: ከስደት መልስ ግን ለ25 ዓመታት ቅዱስ ያዕቆብ ከጌታችን ጋር ሲያድግ ወላጅ እናቱ ትዝ ብላው አታውቅም:: አማናዊቷ እናት ከጐኑ ነበረችና:: +ሊቃውንት እንደ ነገሩን እመቤታችን ለቅዱስ ያዕቆብ ያልሰጠችው ነገር ቢኖር ሐሊበ ድንግልናዌ (የድንግልና ወተትን) ብቻ ነው:: ስለዚህም:- "እመ ያዕቆብ በጸጋ ማርያም ንግሥተ ኩሉ" ይላል መጽሐፍ:: (መልክዐ ስዕል) +ቅዱስ ያዕቆብ "የጌታ ወንድም" ተብሎ በተደጋጋሚ በሐዲስ ኪዳን ተጠርቷል:: ለዚህ ምክንያቱ:- 1.ለ30 ዓመታት ሳይነጣጠሉ አብረው በማደጋቸው፡፡ 2.የጌታችን የሥጋ አያቱ (የቅድስት ሐና) የእህት ልጅ በመሆኑ፡፡ 3.በዮሴፍ በኩልም የአንድ ቅድመ አያት ልጆች በመሆናቸው፡፡ 4.ጌታችን ከትህትናው የተነሳ ደቀ መዛሙርቱን "ወንድሞች" ይላቸው ስለ ነበር ነው:: (ሥጋቸውን ተዋሕዶ ተገኝቷልና) +ራሱ ቅዱስ ያዕቆብ ግን "የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ነኝ" ብሎ በፈጣሪና በፍጡር መካከል ያለውን ልዩነት ገልጧል:: (ያዕ. 1:1) ቅዱስ ያዕቆብ ጌታችን ሲያስተምር ተከተለው:: ¤ከ72ቱ አርድእት ተቆጠረ ¤3 ዓመት ከ3 ወር ወንጌልን ተማረ ¤ለመጀመሪያ ጊዜ ከድንግል ማርያምና ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ሆኖ "የጌታን ትንሳኤ ሳላይ እሕል አልቀምስም" ብሎ ማክፈልን አስተማረ ¤መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ወንጌልን አስተማረ ¤የኢየሩሳሌም የመጀመሪያው ሊቀ ዻዻስ ሆኖ አገለገለ ¤በመጀመሪያዎቹ የክርስትና ዘመናት የሐዋርያት ሲኖዶሶችን በሊቀ መንበርነት መራ ¤ሙታንን አስንስቶ: ድውያንን ፈውሶ: የመካኖችን ማሕጸን ከፍቶ: አጋንንትንም አስወጥቶ ብዙ ተእምራትን ሠራ:: እጅግ ብዙ አይሁዳውያንን ወደ አሚነ ክርስቶስ መልሶ መልካሙን ገድል ተጋደለ:: +በመጨረሻ ዘመኑ ያላመኑ የአይሁድ አለቆች ወደ ቤቱ ተሰብስበው "የናዝሬቱ ኢየሱስ ማነው? የማንስ ልጅ ነው?" ሲሉ ጠየቁት:: እነርሱ ሰይጣን በሰለጠነበት ልቡናቸው "የዮሴፍ ልጅ ነው: የእኔም ወንድሜ ነው" እንዲላቸው ጠብቀው ነበር:: (ሎቱ ስብሐት ወአኮቴት!) +በልቡናቸው ያሰቡትን ተንኮል የተረዳው ሐዋርያ ወደ ቤቱ ጣራ ወጥቶ መናገር ጀመረ:: "ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ: ወልደ አብ ወልደ ማርያም: ሥግው ቃል: እግዚአብሔር ነው:: እኔም ፍጡሩና ባሪያው እንጂ እንደምታስቡት ወንድሙ አይደለሁም" አላቸው:: +ንዴታቸውን መቆጣጠር ያልቻሉት አይሁድ ከላይ ወጥተው ወደ መሬት ወረወሩት:: በገድል የተቀጠቀጠ አካሉንም እየተፈራረቁ ደበደቡት:: አንዱ ግን ከእንጨት የተሠራ ትልቅ ገንዳ አምጥቶ የቅዱሱን ራስ ደጋግሞ መታው:: ጭንቅላቱም እንዳልነበር ሆነ:: ሰማዕቱ ሐዋርያ ቅዱስ ያዕቆብ ወደ ወደደው ክርስቶስ በዚህች ቀን ሔደ:: +ቅዱሱ ሐዋርያ ያዕቆብ ቤቱን እንደ ቤተ መቅደስ አበው ሐዋርያት ይጠቀሙባት ነበር:: በመላ ዘመኑ የሚያገድፍ ነገር (ጥሉላት) ቀምሶ: ጸጉሩን ተላጭቶ: ገላውን ታጥቦና ልብሱን ቀይሮ አያውቅም:: "ወዝንቱ ጻድቅ እኅወ እግዚእነ:: ኢያብአ ውስተ አፉሁ ሥጋ ወወይነ:: ወኢገብረ ሎቱ ክልኤተ ክዳነ::" እንዲል:: +ከጾም: ከጸሎትና ከመቆሙ ብዛትም እግሩ አብጦ አላራምድህ ብሎት ነበር:: ስለዚህም አበው "ጻድቁ (ገዳማዊው) ሐዋርያ" ይሉታል:: ቅዱሱ ሐዋርያ "የያዕቆብ መልዕክት" የሚለውን ባለ 5 ምዕራፍ መልዕክት ጽፏል:: =>ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሙ ይባል ዘንድ ካደለው ሐዋርያ በረከትን ያድለን:: በምልጃውም ምሕረትን ይላክልን:: =>የካቲት 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (የቅዱስ ዮሴፍ ልጅ : ከ72ቱ አርድእት አንዱ) 2.ቅዱስ አባ መላልዮስ ጻድቅ ሊቀ ዻዻሳት (በአንጾኪያ ሊቀ ዽዽስና ተሹሞ በአርዮሳውያን ብዙ ግፍ የደረሰበትና በስደት ያረፈ አባት ነው) =>ወርሐዊ በዓላት 1.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ 2.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት 3.አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ 4.ማር ያዕቆብ ግብፃዊ =>+"+ የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ያዕቆብ: ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች:: ሰላም ለእናንተ ይሁን:: ወንድሞቼ ሆይ! የእምነታችሁ መፈተን ትዕግስትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት:: ትዕግስትም ምንም የሚጐድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም:: +"+ (ያዕ. 1:1) > 860 views14:39