✞ ✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞ ✞ ❖ የካቲት 13 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት +*" ማር ፊቅጦር "*+ =>ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በደማቸውና በገድላቸው ያስጌጡ ብዙ ሰማዕታት አሉ:: ነገር ግን ከኮከብም ኮከብ ይበልጣልና ማን እንደ ጊዮርጊስና እስጢፋኖስ! ከእነርሱ ቀጥለው ከሚጠሩ ሰማዕታት ደግሞ አንዱና ዋነኛው ቤተ ክርስቲያን "ማር" የምትለው ቅዱስ ፊቅጦር ነው:: =>እስኪ ከበዛው መዓዛ-ገድሉ ጥቂት እንካፈል:- +ቅዱስ ፊቅጦር አባቱ ኅርማኖስ ይባላል:: አረማዊና ጨካኝ ነው:: እናቱ ግን የተመሰገች ቅድስት ማርታ ትባላለች:: ልጇን እንደሚገባ አሳድጋው 20 ዓመት ሲሞላው የአንጾኪያ ንጉሥ የሠራዊት አለቃና በመንግሥቱ 3ኛ አድርጐ ሾመው:: +የድሮዋ አንጾኪያ (ሮም) እንደ ዛሬዋ አሜሪካ ዓለምን የተቆጣጠረች ሃገር ነበረች:: ቅዱስ ፊቅጦር ደም ግባቱ ያማረ: በጦርነትም ኃይለኛ ስለ ነበር ሁሉ ያከብሩት: ይወዱትም ነበር:: +እርሱ ግን ቀን ቀን ሲጾም: ነዳያንን ሲያበላ ይውል ነበር:: ሌሊት ደግሞ እኩሉን ሲጸልይና ሲሰግድ እኩሉን የእስረኞችን እግር ሲያጥብ ያድር ነበር:: ይህ ሁሉ ሲሆንኮ እርሱ የንጉሡ 3ኛ: የሠራዊትም አለቃ ነው:: በዘመኑ የሚያገድፍ ምግብና የወይን ጠጅ በአፉ ዙሮ አያውቅም:: +ከነገር ሁሉ በሁዋላ ንጉሡ ዲዮቅልጢያኖስ ካደ:: ዘመነ ሰማዕታትም ጀመረ:: አብያተ ክርስቲያናት ተቃጠሉ:: ከ47 ሚሊየን በላይ ክርስቲያኖች በመንኮራኩር ተፈጩ:: በመጋዝ ተተረተሩ:: ለአራዊት ተሰጡ:: በግፍም ተጨፈጨፉ:: ቀባሪ አጥተውም ወደቁ:: +በዚሕ ጊዜ ማር ፊቅጦር እናቱን ቅድስት ማርታን በዕንባ ተሰናብቶ ወደ ንጉሡ ቀርቦ በክርስቶስ ስም ታመነ:: ክፉ አባትም በልጁ ላይ ሞትን መከረ:: +ከዚያም ቅዱሱን አፉን በብረት ለጉመው ወደ ምድረ ግብፅ አወረዱት:: መሪያቸው እንዳልነበረ ወታደሮቹ መኩዋንንቱ ሁሉ ተዘባበቱበት:: እርሱ ከምድራዊ ንግሥና ሰማያዊ መንግስትን: በሰዎች ፊት ከመክበር ስለ ክርስቶስ ሲል መናቅን መርጧልና:: +ለቀናት: ለወራትና ለዓመታት መኩዋንንቱ እየተፈራረቁ አሰቃዩት:: በርሱ ላይ ያልሞከሩት የስቃይ ዓይነት አልነበረም:: አካሉን ቆራርጠዋል: ዓይኖቹን አውጥተዋል: ምላሱንም ቆርጠዋል:: ሚያዝያ 27 ቀን ግን በሰይፍ አንገቱን ቆርጠውታል:: ስለዚህም እናት ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ማክበር ታከብረዋለች:: ❖እግዚአብሔርም ለቅዱስ ፊቅጦር እንዲህ አለው:- "እንደ አቅሙ ስምህን የጠራ: መታሠቢያህን ያደረገ: ስምህን ያከበረ: የብርሃን ልብስ አጐናጽፌ ወደ መንግስተ ሰማያት አስገባዋለሁ::" ❖ይህች ቀን ማር ፊቅጦር የተወለደባት ናት፡፡ እናቱን ቅድስት ማርታ (ሶፍያንም) እናስባለን፡፡ ❖ቸሩ አምላከ ፊቅጦር ሁላችንም ይማረን:: ከቃል ኪዳኑ አሳትፎ ለርስቱ ያብቃን:: ✞✞ ቅዱስ አውሳብዮስ ካልዕ (ጥዑመ ዜና) ✞✞ => ቅዱስ አውሳብዮስ በወጣትነቱ ከተባረከች ሚስቱ ጋ በድንግልና የኖረ; በዘመኑ ባሕር ውስጥ ሰጥሞ ይጸልይ; 4,000 አቡነ ዘበሰማያት በአንድ ቀን ያደርስ የነበረ; ስለ ሃይማኖትም በቀስት የተወጋ; በእሳት የቃጠለ; አካሉን ቆራርጠው የጣሉትና እግዚአብሔር ከሞት ያስነሳው ጻድቅና ሰማዕት ነው:: ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላ ከነሥጋው ወደ ሰማይ ተነጥቆ ለ14 ዓመታት ቆይቷል:: ወደ ምድርም ተመልሶ ለ40 ዓመታት በሐዋርያነት ከ85,000 በላይ አሕዛብን ወደ ሃይማኖት መልሷል:: ጌታም በስምህ የተማጸነውን እስከ 7 ትውልድ እምርልሃለሁ ብሎታል::" ❖አባቶቻችን ደግሞ ስም አጠራሩ የከበረ ዜና ሕይወቱ ያማረ ሲሉ ይጠሩታል:: ❖ ከበረከቱ ያድለን:: ✞ የካቲት 13 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.ቅዱስ አውሳብዮስ ጻድቅ (ጥዑመ ዜና) 2.ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት (ልደቱ) 3.ቅዱስ ሰርግዮስ ሰማዕት 4.ቅዱስ መፁን ቀሲስ 5.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሰማዕት (የቅ/ፋሲለደስ ልጅ) 6.አባ ጢሞቴዎስ ሊቀ ዻዻሳት 7.አባ ክፍላ 8.አባ ኅብስ =>ወርኀዊ በዓላት 1.እግዚአብሔር አብ 2.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላዕክት 3."99ኙ" ነገደ መላዕክት 4.ቅዱስ አስከናፍር 5."13ቱ" ግኁሳን አባቶች 6.ቅዱስ አርሳንዮስ ጠቢብ ገዳማዊ 7.አቡነ ዘርዐ ቡሩክ =>+"+ እግዚአብሔር ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ : እስከ አሁንም ስለምታገለግሏቸው ያደረጋችሁትን ሥራ : ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመጸኛ አይደለምና:: በእምነትና በትእግስትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን::+"+ (ዕብ. 6:10-13) ✞ ✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞ ✞ 459 views05:22