Get Mystery Box with random crypto!

††† እንኳን ለጻድቁ አባ አውሎግ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። ††† * | ✞ገድለ ቅዱሳን✞

††† እንኳን ለጻድቁ አባ አውሎግ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††
*
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† አባ አውሎግ አንበሳዊ †††

††† አባ አውሎግ ማለት:-
*ከቀደመው ዘመን ጻድቃን አንዱ::
*እንደ ገዳማውያን ፍፁም ባሕታዊ::
*እንደ ሐዋርያት ብዙ ሃገራትን በስብከተ ወንጌል ያሳመኑ::
*በግብፅና በሶርያ በርሃዎች ለ90 ዓመታት የተጋደሉ ጻድቅና ሐዋርያ ሲሆኑ የሚጉዋዙበትና የሚታዘዛቸው ግሩም አንበሳ ነበር::
*በዚህም አባ አውሎግ "አንበሳዊ" ስትል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትጠራቸዋለች::

አባ አውሎግ ከሚታወቁበት አገልግሎት አንዱ ስብከተ ወንጌል ነው:: ምንም እንኩዋ ገዳማዊ ቅዱስ ቢሆኑም ያላመኑትን ለማሳመን : ያመኑትንም ለማጽናት ተጋድለዋል::

እግዚአብሔር በሰጣቸው አናብስት በአንዱ ላይ ተጭነው (መዝ. 90) : በሌላኛው ላይ እቃቸውን አስቀምጠው በየአኅጉራቱ ከመምህራቸው ቅዱስ አውሎጊን ጋር ይዘዋወሩም ነበር:: የጌታ ቸርነት ሆኖም አናብስቱ የቅዱሳኑን ፈቃድ ሳይነገራቸው ያውቁ ነበር::

ሲርባቸውም ተግተው ይመግቧቸው ነበር:: እንዲያውም አንዴ ቅዱሳኑ እንደራባቸው አንዱ አንበሳ ሲያውቅ ከበርሐ ወደ ገበያ መንገድ ወጥቶ ተመለከተ:: በአህያ ላይ ልጁንና ስንቁን (ዳቦ) ጭኖ የሚሔድ ሽማግሌ ነበርና ዳቦውን አንስቶ ወስዶ ለእነ አባ አውሎግ ሰጣቸው::

ከድንጋጤ የተነሳም ሕጻኑ ሙቶ ነበርና ሽማግሌ አባቱ አዘነ:: አንበሳው ግን ሕጻኑንም ወደ ቅዱሳኑ ወስዶ አስረከበ:: ቅዱሳኑም ከሕብስቱ በመጠናቸው በልተው ቢባርኩት እንዳልተበላ ሆነ:: ሕጻኑንም ከሞት በጸሎታቸው አስነስተው ለአንበሳው ሰጥተውታል::

አንበሳውም ስንቁንና ልጁን ለአረጋዊው ሰጥቶት በደስታ ወደ ሃገሩ ተመልሷል:: ቅዱስ አባ አውሎግና መምህሩ አውሎጊን ከ90 ዓመታት በላይ በዘለቀ ተጋድሏቸው አጋንንትን ያሳፍሩ ዘንድ : ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ንጹሕ መስዋዕት ይሆኑለት ዘንድ በትጋት ኑረዋል::

¤ብዙ ተአምራትን ሠርተው ፈጣሪያቸውን አክብረዋል::
¤እንደ ሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ባሕር ከፍለዋል::
¤እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ሙት አንስተዋል:: ድውያንን ፈውሰዋል::
¤እንደ ቅዱስ ዳንኤል አናብስትን ገዝተዋል::
¤ይህች ቀን ዕለተ ዕረፍታቸው ናት::

†††  ቅዱስ በላትያኖስ †††

††† ይህ ቅዱስ ሐዋርያዊ ዻዻስ የቀድሞዋ ሮም ሊቀ ዻዻሳት ሲሆን ቸር : ትጉህና በጐ እረኛ ነበር:: መናፍቃንን ሲያርም : ምዕመናንን ሲመክር : ስለ መንጋው እንቅልፍ አጥቶ ኑሯል:: በፍጻሜውም በዚህች ቀን የሮም ንጉሥ ለ1 ዓመት አሰቃይቶ ገድሎታል:: ዕሴተ ኖሎትን (የእረኝነት ዋጋንም) ከጌታችን ተቀብሏል::

††† አምላከ አበው ቅዱሳን በመጽናታቸው ያጽናን:: ከበረከታቸውም ያድለን::

††† የካቲት 11 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አባ አውሎግ አንበሳዊ
2.አባ አውሎጊን ጻድቅ (የአባ አውሎግ መምሕር)
3.አባ በትራ (የጻድቁ አባ ስልዋኖስ ደቀ መዝሙር)
4.አባ በላትያኖስ ሰማዕት (የሮም ሊቀ ዻዻሳት የነበረ)
5.አባ አብርሃም ኤዺስ ቆዾስ
6.አባ መቃቢስ
7.አባ ኮንቲ

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ያሬድ ካህን
2.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት
3.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
4.ብፁዐን ኢያቄም እና ሐና
5.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ

††† "በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን ለምናምንም ከኁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንደሆነ ታውቁ ዘንድ ነው::" †††
(ኤፌ. 1:19)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††