Get Mystery Box with random crypto!

✞ ✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞ ✞ ❖ እንኳን አደረሳች | ✞ገድለ ቅዱሳን✞

✞ ✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞ ✞

❖ እንኳን አደረሳችሁ ❖

❖ የካቲት 8 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

+ " በዓለ ስምዖን " +

=>ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን ጌታ በተወለደ በ40 ቀኑ ራሱ የሠራውን ሕግ ይፈፅም ዘንድ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቷል::
እንደ ሥርዓቱም እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምና
አገልጋዩዋ ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ የርግብ ግልገሎችና
ዋኖስ አቅርበዋል::

+ለ284 ዓመታት የአዳኙን (የመሢሁን) መምጣት
ይጠብቅ የነበረው አረጋዊው ስምዖን በዚህች ዕለት
ስላየውና ስለታቀፈው
ዕለቱ በዓለ ስምዖን ይባላል:: (ሉቃ. 2:22) ከዘጠኙ
የጌታ ንዑሳን በዓላት አንዱ ነው::

+ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

+ከዓለም ፍጥረት በ5,200 ዓመታት (ማለትም
ከክርስቶስ ልደት 300 ዓመታት በፊት) በጥሊሞስ
የሚሉት ንጉሥ በግሪክ
ነገሠ::

+በጊዜውም በኃይለኝነቱ ሁሉን አስገብሮት ነበርና
"ዓለሙን እንደ ሰም አቅልጬ: እንደ ገል ቀጥቅጬ
ገዛሁት:: ምን
የቀረኝ ነገር አለ?" ሲል ተናገረ:: ባሮቹም "አንድ ነገር
ቀርቶሃል:: በምድረ እሥራኤል ጥበብን የተሞሉ 46
መጻሕፍት
አሉ:: እነርሱን አስተርጉም" አሉት::

+ያን ጊዜ እሥራኤላውያንን አስገብሯቸው ነበርና 46ቱን
የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ከ72 ምሑራን (ተርጉዋሚዎች)
ጋር
እንዲያመጡለት አዛዦቹን ላከ:: እነርሱም 46ቱን
መጻሕፍተ ብሉይ ኪዳን ከ72 ምሑራን ጋር አመጡለት::

+አይሁድ ክፋተኞች መሆናቸውን ሰምቷልና 36 ድንኩዋን
አዘጋጅቶ: ጥንድ ጥንድ ሆነው እንዲሠሩ: ሲተረጉሙ
እንዳይመካከሩ
36 ጠባቂዎችን ሾመባቸው:: ይህ ነገር ለጊዜው ከንጉሡ
ቢመስልም ጥበቡ ግን ከእግዚአብሔር ነው::

+ምንያቱም በጊዜ ሒደት መጻሕፍተ ብሉያት በአደጋ
እንደሚጠፉ ያውቃልና ሳይበረዙ ለሐዲስ ኪዳን
ክርስቲያኖች ለእኛ
እንዲደርሱ ነው:: ስለዚህም ከክርስቶስ ልደት 284 ዓመት
በፊት 46ቱም ሁሉም መጻሕፍት (ብሉያት) ከእብራይስጥ
ወደ
ጽርዕ ልሳን በ70ው ሊቃናት አማካኝነት ተተረጐሙ::
(በእርግጥ ከዚያ አስቀድሞ መጻሕፍት (ብሉያት) ወደ
ሃገራችን መምጣቸውና ወደ ግዕዝ ልሳን መተርጐማቸውን
ሳንዘነጋ ማለት ነው)

+ወደ ዋናው ጉዳያችን ስንመለስ ከ70ው ሊቃናት
መካከል በእድሜው አረጋዊ የሆነ (እንደ ትውፊቱ ከሆነ
216 ዓመት
የሆነው) ስምዖን የሚሉት ምሑረ ኦሪት ነበር:: በፈቃደ
እግዚአብሔር ለእርሱ መጽሐፈ ትንቢተ ኢሳይያስ ደርሶት
እየተረጐመ
ምዕራፍ 7 ላይ ደረሰ::

+ቁጥር 7 ላይ ሲደርስ ግን "ናሁ ድንግል ትጸንስ:
ወትወልድ ወልደ" የሚል አይቶ "አሁን እንኳን የአሕዛብ
ንጉሥ
የእሥራኤልስ ቢሆን ድንግል በድንግልና ጸንሳ ትወልዳለች
ብለው እንዴት ያምነኛል!" ሲል አሰበ:: "በዚያውስ ላይ
ኢሳይያስ በምናሴ የተገደለው ስለዚህ አይደል!" ብሎ
ቃሉን ሊለውጠው ወሰነ::

+አመሻሽ ላይም 'ድንግል' የሚለውን 'ወለት-ሴት ልጅ'
ብሎ ቀየረው:: እርሱ ሲያንቀላፋ ቅዱስ መልአክ ወርዶ
'ድንግል'
ብሎ አስተካከለው:: ከእንቅልፉ ሲነቃ ግራ ተጋብቶ እንደ
ገና ፍቆ ቀየረው::

+አሁንም መልአኩ 'ድንግል' ሲል ቀየረበት:: 3 ጊዜ
እንዲህ ከሆነ በኋላ ግን መልአኩ ተገልጦ ገሰጸው::
በዚያውም ላይ
"ይህችን ድንግልና መሲሑን ልጇን ሳታየውና ሳትታቀፈው
ሞትን አታይም" ብሎት ተሰወረው:: አረጋዊ ስምዖን
ከዚያች ዕለት
በኋላ የመድኅን ክርስቶስን መምጣት ሲጠብቅ ለ284
ዓመታት የአልጋ ቁራኛ ሁኖ ኖረ:: አካሉም አለቀ::

+ለስም አጠራሩ ስግደት የሚገባው አምላካችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ሰው በሆነበት በዚያ ሰሞን እመቤታችን ቅድስት
ድንግል
ማርያምና ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ::

+ሕግን የሠራ ጌታ እርሱ 'ፈጻሜ ሕግ' ይባል ዘንድ
የርግብ ግልገሎችን (ዋኖሶችን) ይዘው በተወለደ በ40
ቀኑ ወደ ቤተ
መቅደስ አስገቡት:: በዚህች ቀንም ቅዱስ መልአክ
መጥቶ ቅዱስ ስምዖንን ከአልጋው ቀሰቀሰው:: ተስፋ
የሚያደርገው አዳኙ
(መሲሑ) እንደ መጣም ነገረው::

+ይህን ጊዜ አረጋዊው አካሉ ታድሶ እንደ 30 ዓመት
ወጣት እመር ብሎ ከአልጋው ተነሳ:: እንደ በቅሎ
እየሠገረም ወደ
መቅደስ ወጣ:: በዚያ መሲሑን (ፈጣሪውን) ሲመለከት
እንደ እንቦሳ ዘለለ:: ቀረብ ብሎም ሕጻን ጌታን ከድንግል
እናቱ እጅ ተቀበለው::

+ከደስታው ብዛት የተነሳም "ይእዜ ትስዕሮ ለገብርከ:
በሰላም እግዚኦ በከመ አዘዝከ-አቤቱ ባሪያህን እንደ
ቃልህ በሰላም
አሰናብተው" ሲል ጸለየ:: ትንቢትንም ተናገረ:: በዚያችው
ዕለትም ዐርፎ ተቀበረ::

+"+ ሐና ነቢይት +"+

+ዳግመኛ በዚህች ቀን አረጋዊቷን ነቢይት ቅድስት ሐናን
እናስባለን:: ይህች ቅድስት ትውልዷ ከነገደ አሴር ሲሆን
አባቷ
ፋኑኤል ይባላል:: በትውፊት ትምሕርት ሐና የተዳረችው
በልጅነቷ (በ12 /15/ ዓመቷ) ነው:: ለ7 ዓመታት ከልጅነት ባሏ
ጋር
ኖራ ዕድሜዋ 19 (22) ሲደርስ ሞተባት::

+እንደ እሥራኤል ልማድ ሌላ እንድታገባ ብትጠየቅም
'እንቢ' ብላ መበለት ሆነች:: ራሷንም ለእግዚአብሔር
አሳልፋ
ሰጠች:: በቤተ መቅደስም ለ84 ዓመታት ለፈጣሪዋ
ተገዛች:: ፈጽማ ትጸልይና ትጾም ነበርና በእነዚህ ሁሉ
ዓመታት ውጪውን
አልተመለከተችም::

+ለእርሷ 103 (106) ዓመት ሲሆን መድኃኒታችን ተወለደ::
በዚህች ቀን ወደ ቤተ መቅደስ ሲገባ ተመልክታም ጌታን
ባረከች::
ደስ እያላትም ትንቢትን ተናገረች:: ወደ ቤቷ ገብታም
ነፍሷን ሰጠች:: (ሉቃ. 2:36-38)

❖ቸሩ መድኃኒታችን ተርፎ ከሚቀረው ዘመን ዕድሜ
ለንስሃ: ዘመን ለፍሥሐ አይንሳን:: ከቅዱሳኑ በረከትም
አይለየን::

✞የካቲት 8 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ስምዖን አረጋዊ
2.ቅድስት ሐና ነቢይት (የፋኑኤል ልጅ)
3.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ እግዝእት
4.አባ ኤልያስ ገዳማዊ (በትህትና ያጌጠ ቅዱስ ሰው)

❖አረጋዊ ስምዖንን ከድካም አልጋ ያነሳ አምላከ ቅዱሳን
እኛንም ድካመ ነፍስን ከሚያመጣ የበደል ምኝታ በቸርነቱ
ያንሳን::

++"+ እንደ ሕጉ ልማድ ያደርጉለት ዘንድ ሕጻኑን ጌታ
ኢየሱስን በአስገቡት ጊዜ እርሱ ደግሞ ተቀብሎ
አቀፈው::
እግዚአብሔርንም እየባረከ እንዲህ አለ:-
'ጌታ ሆይ! አሁን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም
ታሰናብተዋለህ:: ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን
ማዳንህን
አይተዋልና:: ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን:
ለሕዝብሕም ለእስራኤል ክብር ነው::'
ዮሴፍና እናቱም ስለ እርሱ በተባለው ነገር ይደነቁ ነበር::
+"+ (ሉቃ. 2:27)

✞ ✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞ ✞