Get Mystery Box with random crypto!

Daniel: ✞ እንኳን ለቅዱስ 'ማቴዎስ ነዳይ' እና 'ቅዱስ አውስግንዮስ አረጋዊ' ዓመታዊ የዕ | ✞ገድለ ቅዱሳን✞

Daniel:
✞ እንኳን ለቅዱስ "ማቴዎስ ነዳይ" እና "ቅዱስ አውስግንዮስ አረጋዊ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞

+*" ቅዱስ አባ ማቴዎስ "*+

=>ቅዱሱ አባት በቤተ ክርስቲያናችን ስመ ጥር ነው:: በተለይ ትርጉዋሜ ወንጌል ላይ እንደ አብነት ሲጠቀስ የተአምረ ማርያምን ሥርዓት በማዘጋጀቱ የበዓላት መቅድመ ተአምር ላይ ስሙ አለ:: ቅዱሱ ለእመቤታችን በነበረው ፍቅር ድንግል ብዙ ጊዜ ትገለጥለት ነበርና::

+ቅዱስ ማቴዎስ ግብጻዊ አባት ሲሆን የነበረው በመካከለኛው ዘመን ውስጥ (ማለትም በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን) ነው:: በቤቱም መልካም ወላጆችና ያዕቆብ የሚባል ወንድምም ነበረው::

+እንዲያውም አንዴ እናቱ ቅዱሱን ጸንሳ ሳለች የበቁ አበው ሆዷን እጅ ነስተው "ቅዱስ ፍሬ በማኅጸንሽ ውስጥ አለ" እንዳሏት ይነገራል:: ቅዱስ ማቴዎስ በልጅነቱ ወደ እግዚአብሔር ከመገስገስ: ቅዱስ ቃሉን ከመማር በዘለለ ሌላ ሃሳብ አልነበረበትም::

+ወጣት ሲሆንም ወላጆቹ ተከታትለው በማረፋቸው ከወንድሙ ያዕቆብ ጋር ለብቻቸው ቀሩ:: ብዙ የወላጆቹ ሃብት ቢኖርም ቅዱስ ማቴዎስ ስለ መካፈል አላሰበም:: ከለበሳት ጨርቅ በቀር ምንም ሳይይዝ ወደ በርሃ ገሰገሰ::

+ሊመነኩስ ወዶ የደብረ ቅዱስ አቡፋናን አበው ቢጠይቃቸው "አይሆንም" አሉት:: ምክንያቱም በጊዜው ወንድሙን ያውቁት ስለ ነበር እየመጣ እንዳያውካቸው "አስፈቅድ" ማለታቸው ነበር:: ቅዱስ ማቴዎስ ግን ወደ ሌላ ገዳም ሔዶ አለቀሰ::

+አባቶችም ወደ ወንድሙ ሔደው ስለ ማለዱት ፈቀደለት:: ስለዚህም በደብረ አቡፋና መነኮሰ:: ትንሽ ቆይቶ ግን ወንድሙ ያዕቆብ "ለወንድሜ ያልሆነች ዓለም ለእኔም አትረባኝም" ብሎ: በርሃ ገብቶ በቅቶ ዐርፏል::

+ቅዱስ ማቴዎስም በገዳሙ በፍቅርና በመታዘዝ ሲያገለግል ዜና ትጋቱ ተሰማ:: ይህንን ከሰሙት ዻዻሳት አንዱ አባ ዼጥሮስ ያለ ፈቃዱ ከገዳም አስወጥቶ በመንበረ ዽዽስናው ረዳት አደረገው:: እርሱ ግን አንገቱን አቀርቅሮ ተጋድሎውን በጾምና በጸሎት ቀጠለ::

+ነገር ግን ሰይጣን በሴቶች አድሮ ፈተነው:: በጣም አዝኖ ዻዻሱን "አሰናብተኝ" አለው:: "እንቢ" ቢለው የክብር ልብሱን (የዻዻሱን) አውጥቶ በመቀስ ብጥስጥስ አደረገውና በዻዻሱ ፊት አኖረለት::

+ፈጽሞ የተበሳጨው ዻዻሱም በየቀኑ 300 እንዲሰግድ: ወደ ቤት እንዳይጠለልና ሌሎች ቀኖናዎችን ቅጣት ሰጥቶ ወደ በርሃ አሳደደው:: ቅዱስ ማቴዎስም መሻቱ ይህቺው ነበረችና ደስ እያለው ሔደ::

+ለ2 ዓመታትም የቀኑ ሐሩር: የሌሊቱ ቁር እየተፈራረቀበት ቅጣቱን በመፈጸሙ የፍትሐት ደብዳቤ ተላከለት:: አንድ ቀን ግን በገዳሙ የነበረ አንድ የበቃ አባት ክብረ ማቴዎስ ተገልጦለት "የብዙዎች አባት ትሆናለህ" አለው::

+ውዳሴ ከንቱን ፈጽሞ የሚጠላት ቅዱሱ ግን አዘነ:: ሰዎች እያከበሩት ስለተቸገረም ገዳሙን ለቀቀ:: በሔደበት ገዳምም ድንቅ ነገሮቹን እያዩ ሲያከብሩት በአንድ ገዳም የማይቀመጥ ሆነ:: ከአንዱ ወደ ሌላውም ይሔድ ነበረ::

+ቅዱስ ማቴዎስ ከዻዻሱ ዘንድ እያለ ቅስናን ሹሞት ነበርና በገዳማት ይቀድሳል:: ከብቃቱም የተነሳ በቅዳሴ ሰዓት ማሕበረ መላእክትን ያያቸው ነበር:: መድኃኒታችን ክርስቶስም ሕጻን መስሎ ከፊቱ ይቀመጥ ነበር:: ስለዚህ ነገርም ዕንባው እንደ ዥረት ውሃ ይፈስ ነበር:: እየቀደሰም ተመስጦ (ተደሞ) ይመጣበት ነበር::

+ዘወትር የፈጣሪውን ጌትነት እያደነቀ ይመራመር ነበርና አንዴ ቀና ቢል 7ቱ ሰማያት ተከፈቱለት:: እግዚአብሔርንም ከጽርሐ አርያም (7ኛው ሰማይ) ከፍ ብሎ አየው:: ደንግጦ ዝቅ ቢል ደግሞ ከጥልቁ በታች ተመለከተው::

+በዚህ ጊዜ "ይህን ያሳየኸኝ ጌታየ እኔ ማነኝ!" ሲል አለቀሰ:: ሁሌ ዐርብም ሕማማተ ክርስቶስን: በተለይ መድኃኒታችን መቸንከሩን እያሰበ ረጅም ችንካርን በጉልበቱ ውስጥ ይከት ነበር:: ለቀናት ስለማያወጣውም ደሙ ፈሶ አካሉ መልኩ ይቀይር ነበር::

+እንዲህ ካሉ የቅድስናና የተጋድሎ ዓመታት በሁዋላም ሌላ ጥሪ ከፈጣሪው መጣለት:: አበው በጸሎት ላይ ሳለ መጥተው አሠሩት:: "ምን አደረኩዋችሁ አባቶቼ?" ቢላቸው የግብጽ ፓትርያርክ ነህ ከዚህ በሁዋላ" አሉት:: ቢለምናቸውም እንቢ አሉት::

+"እንግዲያውስ" ብሎ: ምላሱን አውጥቶ: በመቀስ ቆርጦ ጣላት:: መናገር የማይችል ሰው ክህነት አይሾምምና:: (እንዲህ ነበር አበው ሥልጣንን የሚሸሿት) ነገር ግን እመቤታችን ከሰማይ ወርዳ "ወዳጄ! ነገሩ የልጄ ፈቃድ ስለ ሆነ እሺ በላቸው" ብላ አዲስ ምላስን ሰጠችው::

+የግብጽ 87ኛ ሊቀ ዻዻሳት ሆኖ ሥርዓተ ሲመቱ ሲፈጸም የወንጌላዊ ቅዱስ ማርቆስ ራሱ በዚያ ነበረችና ክንፍ አውጥታ: በራ ቅዱስ ማቴዎስን ስትስመው ሁሉም አዩ:: ከሰማይም ማሕበረ መላእክት "አክዮስ-ይገባዋል" ብለው ሲጮሁ ተሰማ::

+ቅዱስ ማቴዎስ ምንም ፓትርያርክ ቢሆንም ለትምሕርት: ለቅዳሴና መሰል ነገሮች ካልሆነ ከበዓቱ አይወጣም ነበር:: ገንዘብ የሌለው: ጥሩ ልብስ የማይለብስ ነበርና "ነዳዩ" እየተባለ እስካሁን ይጠራል::

+በዘመነ ዽዽስናው ብዙ ተግባራትን ሲከውን ዋኖቹ ግን የእመቤታችን ተአምር በሥርዓት እንዲነበብ ማድረጉ ቀድሞ ይጠቀሳል:: በተረፈም የጌታችን ግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮዽያ እንዲመጣም ትልቅ አስተዋጽኦን አድርጉዋል::

+በተሰጠው የትንቢት ሃብትም ወደ ፊት የሚፈጸሙ ነገሮችን ተመልክቷል:: የተናገራቸውም ሁሉ ተፈጽመዋል:: በመጨረሻው ግን ያሰቃየው የነበረው የወቅቱ የግብጽ ከሊፋ (ክፉ ሰው) አስጠርቶ አካሉ እስኪደቅ ድረስ ገረፈው::

+ቅዱስ ማቴዎስም ወደ እመቤታችን ጮኸ:: ድንግልም ወርዳ አጽናናችውና "አሳርፍሃለሁ" አለችው:: ሕዝቡን ተሰናብቶም በዚህች ቀን ዐርፏል::

+*" ቅዱስ አውስግንዮስ አረጋዊ "*+

=>ይህ ቅዱስ ሽማግሌ በሃይማኖቱ ጽናት: በምግባሩ ብዛት ለወጣቶች አብነት መሆን የቻለ አባት ነው:: በብዛት የሚታወቀው በሰማዕትነቱ ቢሆንም በቅዱስ ሰውነቱ በርካታ መልካም ነገሮችን ሠርቷል::

+በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን መነሻ አካባቢ (ዘመነ ሰማዕታት ሊጠናቀቅ ሲል ማለት ነው) የቅዱስ ቆስጠንጢኖስ (የንጉሡ) ወታደር ሁኖ ተቀጠረ:: ንጉሡ ወደ መክስምያኖስ ለጦርነት ሲሔድ በሰማይ ላይ መስቀልና "ኒኮስጣጣን" የሚል ጽሑፍን ተመልክቷል::

+ሁሉም ሰው ለመተርጐም ሲፈራ ወጣቱ አውስግንዮስ ግን በድፍረት ለንጉሡ ክብረ መስቀልንና ትርጉሙን አስረዳ:: በቅዱሱ ንጉሥ ሥርም በወታደርነት ለ20 ዓመታት አገለገለ::

+ከዚያም ሥጋዊ ተግባሩን ትቶ በጾምና በጸሎት: ሰዎችንም በማስታረቅ: በማስተማርም ተወሰነ:: ፈጣሪ ጸጋውን አብዝቶለትም ዕድሜው 110 ዓመት ደረሰ::

+በጊዜውም የነበረው ከሃዲው ዑልያኖስ "ሰዎችን አስታርቀሃልና ክርስቶስን አምልከሃል" በሚል በዚህች ቀን አንገቱን አሰይፎታል:: ዑልያኖስን ደግሞ ቅዱስ መርቆሬዎስ ተበቅሎታል::

=>አምላከ ቅዱሳን ስለ አባቶቻችን ሲል ይማረን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::

=>ጥር 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አባ ማቴዎስ
2.ቅዱስ አውስግንዮስ አረጋዊ (ሰማዕት)
3.ቅድስት እስክንድርያ
4.ቅድስት አውስያ ሰማዕት

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
2.ቅዱስ ዻውሎስ ብርሃነ ዓለም
3.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
4.ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮዽያዊ
5.ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ
6.ቅድስት አውጋንያ (ሰማዕትና ጻድቅ)