Get Mystery Box with random crypto!

ሰማያዊና መንፈሳዊ “በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱ | ቃለ ዐዋዲ ዘ ተዋሕዶ

ሰማያዊና መንፈሳዊ

“በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ ።” ኤፌ. 1፡3 ።

ክርስትና በምድር ተጀምሮ በምድር የሚፈጸም አጭር ዓላማ አይደለም ። ክርስቲያንም አጭር የሕይወት ታሪክ የለውም ፣ ከሞት በኋላ ህልውናው የሚቀጥል ነው ። ክርስትና ምድራዊ አስተሳሰብ ፣ ቁሳዊ ውድድር ያለበት መድረክ አይደለም ። ክርስትና ለሰማዕትነት አማኞችን የምታሰናዳ እንጂ ለድሎትና ለምቾት የምታነቃቃ አይደለችም ። ክርስትና መስቀልን እንጂ ወርቅን የምትሰብክ አይደለችም ። ክርስቲያንም ሰማይን ግቡ አድርጎ የሚጓዝ የሩቅ አገር መንገደኛ ነው ። ብዙ ሩቅ ተጓዦች ቢኖሩም የክርስቲያን መንገድ ግን ከእነዚህ ሁሉ ረጅም ነው ። ክርስቲያን የሚያየውን ዓለም እንደማያየው ክዶ ፣ የማያየውን ዓለም በእምነት መነጽር የሚያይ ነው ። ለመማር ፣ ለማግባት ለመውለድ ብቻ ክርስቲያን የሆነ ካለ በጣም ምስኪን ነው ። “በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን ።” 1ቆሮ. 15፡19። ክርስቲያን እየተማረ ያምናል ፣ እያገባ ሰማያዊውን ኅብረት ይናፍቃል ፤ እየወለደ ብዙዎችን ለክርስቶስ ያጫል ። የሩቅ እይታው የደበዘዘ ክርስቲያን በቶሎ ተስፋ ይቆርጣል ። እንደ ቅዱሳን ሳይሆን እንደ እነ እገሌ ለመኖር ያስባል ።

ምድራዊ አስተሳሰብ ፣ ምድራዊ ምላሽ ፣ ምድራዊ ውጊያ ክርስቲያንን ከክርስቶስ ይለየዋል ። ክርስቲያን እንደ ሰው ብቻ ሳይሆን እንደ አማኒ የመኖር የወንጌል ግዳጅ አለበት ። ቁሳዊ ውድድርም ጣኦትን እንደ ማምለክ ነው ። ክርስቲያን ጉድለቱን ለመሙላት ቁሳዊ ነገርን ቢፈልግም ሌሎችን ለማናደድ ብሎ ግን ብልጽግናን የሚመኝ አይደለም ። እጆቹ ያለ መታከት ቢሠሩም በሰማያዊ ባንክ ቤት ለማስቀመጥ ይጥራል ። የክርስቲያን ኮሮጆ የድሆች ሆድ ናት ።

“በክርስቶስ” ይላል ። በአዳም አይልም ፣ በእኛም አይልም ። ሰማያዊ ርስትን ፣ መንፈሳዊ በረከትን ያገኘነው በክርስቶስ ነው ። በክርስቶስ ሰው መሆን ፣ በክርስቶስ ቤዛነት የተፈቀዱልን መንፈሳዊ መብቶች ናቸው ። ያልለፉበትን ለመውረስ ልጅ መሆን ያስፈልጋልና ክርስትና በልጅነት የሚጀምር መንፈሳዊ ምዕራፍ ነው ። “በ” የሚለው ቅጽል አድራሻን ጠቋሚ ነው ። ማግኘትን ብቻ ሳይሆን በማን እንዳገኘን መታወቅ አለበት ። “በ” የሚለው ቅጽል ድርጊትን አመልካች ነው ። በክርስቶስ ተፈጥረናል ፣ በፈጠረን እጅ መዳን እንዳለብን ምክረ ሥላሴ ወስኗል ። እኛን ለመፍጠር እነዚያ የክርስቶስ እጆች መሬት ቆፍረዋል ፣ ጭቃ አላቁጠዋል ። እኛን ለማዳንም እነዚያ እጆች ተቸንክረዋል ። በክርስቶስ መፈጠር ፣ መዳንና ርስተ መንግሥተ ሰማያትን ማግኘት ትልቅ ትምህርት ነው ። ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ይህን ማወቅና ማመን አለበት ። ተጋፍቶ ቤተ ክርስቲያን መግባት ይቻላል ፣ ተጋፍቶ መንግሥተ ሰማያት መግባት ግን አይቻልም ።

“በሰማያዊ ስፍራ” ይላል ። ይህ ቦታን አመልካች ነው ። አዲስ ኪዳን ስለ ነፍስ በረከት የሚናገር ኪዳን ነው ። ስለ ምድራዊ ነገር የሚያወራ ፣ “ብዙ ተባዙ” የሚል ኪዳነ አዳም አይደለም ። “ከብርና ከወርቅም ጋር አወጣቸው” እንዲል ኪዳነ እስራኤል አይደለም ። ከዚያ ላቅ ያለ ከምድርና ከከነዓን በላይ የሆነ ሰማያዊና መንፈሳዊ በረከት ያለበት ነው ።

ሐዋርያው ሰማያዊ ስፍራን ያነሣል ። ክርስቶስ ራስ ፣ ምእመን ደግሞ አካል ናት ። ራስ ባለበት አካል ይኖራል ። ክርስቶስ ባለበት በየማነ አብ ቤተ ክርስቲያን አለች ። ይህ ትልቅ በረከታችን ነው ። የአዲስ ኪዳን በረከት ስፍራው ሰማያዊ ነው ። ዓይነቱን መንፈሳዊ ነው ። ምድራዊና ቁሳዊ በረከትን ተስፋ ማድረግ ከወንጌል ዓላማ ሊያደናቅፍ ይችላል ። የበረከት በረከትም ከክርስቶስ ጋር መሆን ነው ። የሥጋ አድራሻችን ምድራዊ ቢሆንም ሰማያዊ አድራሻችን ግን ከክርስቶስ ጋር ነው ።

ካለፉት ዘመናት ይልቅ ቤተ ክርስቲያን በምድራዊነትና በቁሳዊነትን ፈተና ውስጥ እየገባች ነው ። በየዓመቱ ያለው ውድድር በአሥራት ገንዘብ እንጂ በዳኑት ነፍሶች አለመሆኑ ምድራዊነት በጣም እየተስፋፋ መሆኑን ያሳያል ። ስለ ግንባታ እንጂ ስለ መንግሥተ ሰማያት ማሰብ አለመቻል ፣ ክርክሮቻችን ነገረ ድኅነትን ያማከሉ ሳይሆኑ ጥቃቅን ነገሮች መሆናቸው ምድራዊነትን የሚያመለክት ነው ። አገሬ በሰማይ ነው ማለትን ተጠይፈን ይህ የእኛ አገር ነው በማለት መመካት ፣ ሌሎችን ባይተዋር ማድረግ ካለበት ይህ ምድራዊነት ነው ። እንደ ምድራውያን በሥጋዊ ኃይል ለመከለል መከጀል ፣ ለትምህርት ያልፈለግነውን ወጣት ለሞት መፈለግ ይህ ምድራዊነት ነው ። ቁሳዊነት የዛሬውን ዘመን ክርስትና እየጎዳ ነው ። በልቶ ስለመጥፋት እንጂ ስለማብላት የማያስብ አገልጋይ ከፈጠርን ፣ ጉቦ በመንፈሳዊ ዓለም እንደ ጽድቅ ከታየ ፣ ቤተ እግዚአብሔር ድሆችን ገፍታ ባለጠጎችን የምታቅፍ ከሆነች ቁሳዊነት ነግሦአል ማለት ነው ። የተባረክንበትን ሰማያዊ በረከት ችላ ብለን በምድራዊ ነገር ከተጋደልን ፣ መንፈሳዊው በረከት አንሶብን ቁሳዊ ነገርን የአንቱታ ምንጭ ካደረግን ከክርስቶስ ጸጋ እየጎደልን ነው ።

የኤፌሶን መልእክት ትርጓሜ /5

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 3 ቀን 2014 ዓ.ም.