Get Mystery Box with random crypto!

ብር ዘገኔ ዕድሜ 'ማያክላት ዘመን 'ማይችላት ካንቺ ወዲያ ፥ የተረሳች ማትፈጠር የተዘነጋች ማ | ግጥም እና የ Jo ደብዳቤዎች

ብር ዘገኔ


ዕድሜ 'ማያክላት
ዘመን 'ማይችላት
ካንቺ ወዲያ ፥
የተረሳች ማትፈጠር
የተዘነጋች ማትቆጠር
ማኒቷ ናት ብርዘገኔ ?

ሕይወት ነበረች በዚያ
ጉራማይሌ የተወቀረች
ኹኝ ሲላት
ብርዘገን የተባለች ።

እሷ
ልጅት ፣
ንጽሕት ኮረዳ ፥
ኣፍላ ዝልስ ቀዘባ
ሽው እልም
እምር ዘንጠፍ ዘና
እምትል ወለባ ።

ፈክረህ ታውቅ እንደኹ
የኑባሬን ኣንድምታ
ባክህ ኣንት ኹለንታ
ወዲህ ብትላት ፥ ምን ነበር ?
መላ እንኳን ብትመታ ።

እንዳልችለው ቻል ሲለኝ
ውሏን መያዝ ተስኖኝ
( እንደ ረጂም ሌሊት )
ውድቅቷ ዝንታለም ሆኖኝ
ቀትሯን ፥ በዳፍንት እየተቀጣኹ
ከገዛ ኣንድ 'ራሴ ፥ እየተጣጣኹ
ኣሽቀንጥሮ የጣለኝን
ኣስችሎኝ ላልጋደረው
በቀት ለጠመደው ፥ ፍጥርጥሬን ላላማርረው
በዚህ ግባ
በዚህ ውጣ ፣
እያልኩት ላልቃጠረው
ቀቢጸን ደቅድቆት ፥ በቁም ሲያቆረቁዘው
ሰቀቀን ሆኖኝ ዕድሜ ጉዱ
እንዴት ብዬ
የዘርፏን ኣንደኛ ጽንፍ ልያዘው ?

ኣነበንባለኹ
"በቀን ጠሐይ መስኮት"
ገጸ - ስጋሽን
በኣይነ ህሊናዬን ፥ እስለዋለኹ ።

ኣንቺስ ለመሆኑ
ኣስተዋልሻት
ኣስታወሻት ፣
ያቺን የኔን እናት
ሀርሜ ኪይያ ፥ ቢዴና ጠፍጣፊቷን
ሽልጦዋን ስገምጠው
ማመዛዘን የሚሳነኝን ፥ የገዛ ፈሴን ቅርናት
ኣስታወሻት
ኣስተዋልሻት
መቼም እንዳንቺ መክፋት
እንደኔ እንደኔ መጥፋት
ቋንቋ ነበርሽ ለሰሞናት
ግን ?
ኣቻሽ ምኒቷ ናት ።

ኣዎ
ላንቺ - ለዘመናት ምጤ
በእሮሮ ግት ለወለድኩሽ
ቀለም ለጠለቅሽኝ ፥ የኪነት ቅምጤ
ጣር ነበረ ልቤ
እንባ ነበር በእርምጥምጤ
ግን
ምንሽ ነው የሰረቀኝ
ከኣፍላነት ትኩሳቴ ፥ ትኩስ ልምምጤ ?

ሕይወት
ምርቱን ከግርዱ ላንለየው
የወሰደሽን መንገድ ነገር ፥
እህ ብዬ
ከኣንድ እራሴ በቀር
ለማን ነው ? ለምን ነው ማዋየው ።

እንዳልደርስብሽ ርቀሻል
እንዳልዳስስሽ ረቀሻል
ብቻ
ሳስብሽ ሌቱ ይነጋል
ሳልምሽ ቀኑ ይመሻል ።

እና ምን ይዋጠኝ
መድረሻሽን ባወቅኩት
ምን ነበር በተከተልኩት
እንዲህ እንባ ከመሰለቅ
ወይ በየመንገዱ ከምቀር ፥
ወይ በኃሠሣ ከማለቅ
ምን ነበር ?
ምን ነበር ?

ኣንዴ
ከዕድሜ ማለዳ ላይ
ትኩሳትሽ ከሩቅ ጠርቶኝ
የሴት ወጉ ፣ ማዕረጉ
ወዳለሽበት ስርፋ መርቶኝ
ንፍጤን በቅጡ ሳልጥል
ቂጤን በወጉ ሳልጠርግ
በየሸጡ ስዳክር
ፍጥረትሽን
በጨረቋ ቀልቤ ፥ እያማጥኩት ስፈክር
ማን ኣየልኝ ? የልቤን ከቀልቤ ሳመሳክር
ማን ሰማልኝ ? የኣፌን ከእዝኔ ሳፎካክር !

ኣዎ
ቡሃቃ እያገለባበጥኩኝ
ጥራጊ ዓለሙን ሳዋስጥ
በየመጋዣው ፊንጥጣ ስር ፥ ጉልምስናዬን ሳሯሩጥ
ኣለሽበት ስርፋ ከመድረሴ
እንደ ልቤ ሳልፋንን ፥
"ቤት ፈረሰ
ዳቦ ተቆረሰ"

ግን
ለስንቱ ኣልሜሽ ማማጤን
በየቆቃው ስር ተለጥፌ ፥
ጨለማሽን መለማመጤን
ከገዛ ኣንድ ራሴ በቀር
ማን አየልኝ?
እዚህ ድረስ መርመጥመጤን።

ወትሮ
መንገድሽን ተከትዬ
ስንዝር ላልደርስበት
እንደ ዘላን ገላ፣
እንደ መናፍስቱን ፥ ዕድሜ ያልተሰፈረበት
ዘሐዓለም ዓለም ነው ፥ ወዲያ ያለሽበት

እና
በምኔ ልንፏቀቅ
እንዴትስ ልጠጋሽ?
ልቤን ለጭዳሽ ጣልኩት
ጉልበቴን ብጨርሰው
ግን.... ግን.....
ሞት አውላላውን ሲፎክር፥
የአምላክ ህላዌን ሊካሰሰው
መቃብሩ መሀል ቤት - እንደሚምሰው
አዎን
እንዳመልክሽ ተፈርዶብኛል
ልክ እንደገመምተኛ ለው።

እንግዲህ እወቂ
አንቺን መከተል ደክሞኛል
እፎይ ልበል
የእረፍት ንሥሀ ያስፈልገኛል።

እፎ.....................ይ!


አናንያ ተሾመ

http://t.me/sufafel