Get Mystery Box with random crypto!

“የእናት ሀቅ.. መች ይለቅ!” (እውነተኛ)-ክፍል ሁለት/መጨረሻ/ ፀሐፊ :አብዱልጀባር ፋሪስ | ⛤Ιѕℓαмιc нιѕтory⛤

“የእናት ሀቅ.. መች ይለቅ!”
(እውነተኛ)-ክፍል ሁለት/መጨረሻ/
ፀሐፊ :አብዱልጀባር ፋሪስ


ታላቅ እህት ሮጣ ወደ ቤቱ ስትደርስ እናት መሬት ላይ ተዘርራለች። አይኗን ማመን አልቻለችም። ...ይሄኔ ኡኡታዋን አቀለጠችው። የአካባቢው ሰው ወደ ቦታው አቤት ሲል ተሰበሰበ። ነገሩ ካለቀ ወዲህ ምን ይፈይድና ነው። ህዝቡ ጉድ እንዲል... ልጅ እናቱን ገድሎ ሬሳዋ ላይ ቆሟል። እህት በልቅሶ እናት ላይ ተደፍታ ታለቅሳለች። “አ... ወይኔ ሀደኮ, ሲ አጄሴ ሚቲ” እህት በኦሮምኛ እያወራች ትንሰቀሰቃለች። ህዝቡ ለቅሶና ዋይታውን አቀለጠው። በአቅራቢያ ለሚገኘ ፖሊስ ጣብያ ተደውለ። ልጅ በነብስ ግድያ ወንጀል እጅ ከፍንጅ በመያዙ ዘብጢያ ወረደ።

መንደርተኛ ለተራ ሞት እንደሚያለቅስ የታወቀ ነው። በዚች ሚስኪን እናት ሞት ደግሞ ይበልጥ ልባቸው ተሰብሯል። ሀዘናቸውን አሟሟቷ እጥፍ ድርብ አድርጎ፣ ለቅሶው እና ወሬው ሀገር አዳርሶ ነበር። መቼስ ሬሳን ተሸክመው አይቆዩና.. እናት ልትቀበር በእስልምና ስርዓት መሰረት ሰውነት ተገነዘ። በነጭ አቡጀዲ(ከፈን) ተጠቅልላ ወደ ማይቀረው ቤቷ መጓዟ ነው። በእግሯ ላትሄድ ሸክም አይቀርላትም... ይሄኔ ነው ሀገር አይቶት የማያውቅ ጉድ እንግዳ የገጠማቸው።

የእናት እሬሳ(ጀናዛ) ተገንዞ ከተከፈንበት ቦታ ንቅንቅ አልልም አለ። የሀገሩ ወጣት፣ ወጠምሻ ሊያነሳው ቢሞክር ፍንክች አልልም አለ። በተቀመጠበት ቦታ እንደ አለት ደርቆ ወደ ላይ ሚያነሳው ጠፋ። የሀገሬው ሰው ጉድ ብሎ... ምን እናድርግ ሲል፣ ከፈሎዎቹ ሼኽ ይጠራና መፍትሄ ያበጅልን ሲሉ ሀሳብ ሰጡ። በአካባቢው ለሚገኙ ሼኾች ጉዳዩ ተነግሮ ወደ ቦታው ፈጥነው ደረሱ። እነሱም ለማንሳት ቢሞክሩ እንቢ አላቸው።

ነገሩን በጥልቀት ሲጠይቁ የእናት አሟሟት ተነገራቸው። መፍትሄ ነው ብለው ያሰቡት እናትን የገደላት ልጅ ከእስር ቤት መጥቶ እንዲያነሳ ነው። ልጅ ከእስር ቤት ተጠራና በፖሊስ ታጅቦ እቦታው ደረሰ። ከአራቱ የቃሬዛው ቅርንጫፎች አንዱን ይዞ ሎሎች ሶስት ሰዎች ተጨምረው ብድግ ሲያደርጉት፤ እንቢ ብሎ የነበረው እሬሳ ተነሳ። መስጂድ ተወስዳ ተሰገደባት። ሰላቱ እንዳለቀ ከልጅ ጋር ሆነው ወደ መቀበርያ ቦታዋ ወሰዷት። ችግሩ እንዳለቀ በማሰብ ልጅ ወደ እስር ቤት እንዲመለስ ተደረገ። የቀብር ቁፋሮው እንዳለቀ... እናትን ወደ ለህድ (የሬሳ መጋደምያ) ቦታ ለማስገባት ቢሞክሩ.. ቢሉ.. እንቢ አላቸው። እናት በድጋሚ መሬት ላይ ደርቃ ቀረች። ልጅ ከእስር ቤት ተመልሶ መጥቶ እናቱን ተሸክሞ ወደ ለህድ እንዲያስገባ ሆነ።

በድጋሚ ልጅ መጥቶ ሬሳውን ሲያነሳው እንደ ቀልድ ብድግ ብሎ ተነሳለት። ይህንን ሁሉ ተዓምር ሀገሬው ቆሞ ይከታተላል። በድጋሚ ልጅ እናቱን ይዞ ወደ ለህድ ውስጥ ሲያስገባ... ሌላ ተዓምር ይመለከቷል። እናቱን ወደ መጋደሚያዋ እንዳስተኛት አስገራሚ ተዓምር ተከሰተ። ልጅ ጠብቶ ያደገው የእናቱ ጡት ከነበረበት መጠን ጨምሮና ረዝሞ ልጅ ላይ እንደ እባብ ተጠመጠመበት። በነገሩ ነብሱ እስክትወጣ የደነገጠው ልጅ.. ጩኸቱን አቀለጠው። ሰዉ ምን ጉድ ነው ብሎ ሲመለከት ያው ነው። የእናት ጡት እንደ ትልቅ ዘንዶ ልጅ ላይ ተጠምጥሞ ማፈናፈኚያ አሳጥቶታል።

በነገሩ በጣም ደነገጡ። የእናት ሀቅ መሆኑን ሁሉም ተገንዝቦ ነበር። ሆኖም የሞተ አይነሳና ልጅን ከእናቱ ጡት አላቅቀው ለማዳን ቢሞክሩም.. ጭራሽ እንቢ አላቸው። ይሄኔ አዋቂዎቹ የእናት ጡት ይቆረጥ ወይስ ልጅን ከነእናቱ እንድፈነው ብለው ካጤኑ በኋላ አንድ ውሳኔ ላይ ደረሱ። “የአላህ ውሳኔ እና ተዓምር ነው። ልጅን ለማላቀቅ መሞከር ከንቱ ልፋት በመሆኑ እዛው ከእናቱ ጋር ድፈኑት። ለሰዎችም አላህ ያሳየን ተዓምር ነው” ሲሉ ጉዳዩን ቋጩት። ጨካኙ ነብሰ ገዳይ ልጅ አንቆ ከገደላት እናቱ ጋር በአንድ ጉድጓድ ተቀበረ! ነገሩም በዚህ ተቋጨ።

ወዳጆቼ አሁን ላይ ልጅ እናቱን መግደል፤ አባቱን ማሰቃየት፤ ብሎም ህይወቱን ማጥፋት እየበዛ ይገኛል። ከዚህ በታች ሳይሆን አሳሳቢውም እናትና አባትን አለማክበር.. ትዕዛዛቸውን አለመፈፀምም ሌላው ትልቅ ወንጀል ነው።ወዳጆቼ! ወላጆቻችሁ የእናንተ ጌጥ ብቻ ሳይሆን መነሻችሁም ናቸው። በነሱ የሚያፍር እና መብታቸውን የማይጠብቅ ከእንደዚህ አይነቱ ውርደት እስከ መጪው አለም ቅጣት ቢጠነቀቅ ይሻለዋል። አደራችሁን በህይወት ላሉት እዝነትና ርህራሄን ሰጥተን፥ ከትዕቢትና ግልምጫ በመቆጠብ ደስተኛ እናድርጋቸው። የሞቱብንን ደግሞ በፀሎታችን ሁሌም ልንዘክራቸውና መሀርታ ልንለምንላቸው ይገባል።

ታሪኩ ፍፁም እውነትኛ ነው። እኔም ለማመን ከብዶኝ ነበር.. ነገር ግን በዘመናችን የተከሰተና ከአካባቢው ሰዎች ምስክር የተሰጠው ነው አ። መማሪያ ሚፈልግ ይህ በቂና ከበቂም በላይ ነው። እኔ የሰማሁትን ለናንተ በማካፈል ግዴታዬን ተወጣሁ። እናንተም ሼር በማድረግ ግዴታችሁን ተወጡ። ለቻናሌ ሳይሆን ለመልዕክቱ ስትሉ ለምታውቁት ሰው ሁሉ አስተላልፋ። አብራችሁኝ ስለነበራችሁ አመሰግናለሁ። አላህ ያክብርልኝ!

join & share
https://t.me/+jPQLXna9F-E3ZDQ0