Get Mystery Box with random crypto!

በቅርቡ በሞት ያጣናቸው ደራሲና ጋዜጠኛ እያሱ በካፋ 'የእያሱ በካፋ ወጎች' በሚለው መጽሐፋቸው ላይ | ኢንፎክን የመጻሕፍት እና የመረጃ ማዕከል

በቅርቡ በሞት ያጣናቸው ደራሲና ጋዜጠኛ እያሱ በካፋ 'የእያሱ በካፋ ወጎች' በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ስለ እናት እና እናትነት የሚከተለውን አስፍረዋል።
===
ሁላችን እናቶች አሉን። ሁላችንም በእናቶቻችን ማህፀን ተፀንስን፣ ከምግባቸው ምግባቸውን፣ ከትንፋሽ ትንፋሻቸውን፣ ከደማቸው ደማቸውን፣ ከስጋው ስጋቸውን፣ ከነፍሳቸው ነፍሳቸውን ስጥተውን ዘጠኝ ወር በሙሉ ረቂቅ በሆነ የተፈጥሮ መስተጋብር ውስጥ አልፈን ተወልደናል።

ብዙዎቻችን እናቶቻችንን እማማ፣ እምዬ፣ እናታለም፣ ማሚ እያልን እንጠራለን። በአለም ውስጥ ካለው ሁሉ ነገር እንደ እናት ማን ከበረ? እናትነት ነፍስን ማካፈል ነው። እናትነት የማይደበዝዝ ዘላለማዊ ፍቅር መስጠት ነው። እናትነት ከራስ ህልውና ይበልጥ ለልጅ ማሰብ ነው። እናትነት ፍፁም ወረት አልባ መሆን ነው። እናት ለልጇ ያላት ፍቅር አይነጥፍም፣ አይለወጥም። ለእናት ልጇ ሁሌም ልጇ ነው።

የድሃ ልጅ እናት፣ የከበርቴ ሰው እናት፣ የወረዳ ገዥ እናት፣ የቀበሌ አስተዳዳሪ እናት፣ የአብዮት ጥበቃ እናት፣ የደንብ አስከባሪ እናት፣ የሊስትሮ እናት፣ የቤት እመቤት እናት፣ የዘበኛ እናት፣ የቤት ሠራተኛ እናት፣ የገዳይ እናት፣ የተገዳይ እናት፣ የአሳሪ እናት፣ የታሳሪ እናት፣ የገራፊ እናት፣ የተገራፊ እናት፤ የጨቋኝ እናት፣ የተጨቋኝ እናት የሞሶሎኒ እናት፣ የሂትለር እናት፣ የአንስታይን እናት፣ የጠንቋይ እናት፣ የካህን እናት፤ የሼክ እናት፤ የሁሉ እናት እናቶች ሁሉም አንድ አይነት ናቸው።

ልጆቻቸው ሲያድጉ ሲጠግቡ፤ ሲለብሱ ይፈድቃሉ እናቶች፡፡ ልጆቻቸው ሲራቡ፣ ሲጠወልጉ፣ ሲገረፉ፣ ሲማስኑ ደግሞ ስቅስቅ ብለው ያለቅሳሉ፡፡ ገራፊው ልጃቸው ወይም ጨቋኝ ልጃቸው በአድራጎቱ ሕዝብ ሁሉ ሲጠላቸው 'ለምን ልጄን ጠሉብኝ' ብለው አሁንም እናቶች ስቅስቅ ብለው ያለቅሳሉ። እናቶች እንዲህ ናቸው፣ ዘመን የማይሽረው ሁኔታ የማይለውጠው ፍቅር የእናት ፍቅር ነው፡፡

እናት ለልጇ ያላት ፍቅር ገደብ የለውም፡፡ ልጆችም ሁልጊዜ ከምንም በላይ የሚያፈቅሩት እናታቸውን ነው። ለዚህ ነው በብዙ የታሪክ ክስተቶች እናቶች አማላጅ የሚሆኑት ልጅ ምን ጨካኝ ቢሆን እናቱ ስትመክረው፣ ስታማልደው፣ ስትጠይቀው፣ ሆዱ መራራቱ አይቀርም። በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ መናገር ይቻላል። እናት የንፁህ ፍቅር ምሳሌ ናት። ብዙ ሃይማኖቶች ሰውን ሁሉ እንድናፈቅር ይሰብካሉ፣ ያስተምራሉ። በዚህ ምክንያት ይመስለኛል እግዚአብሔር በእናት በኩል በሴት በኩል እኛን ለማዳን የመጣው።

የእያሱ በካፉ ወጎች ቅፅ ፩

መልካም የእናቶች ቀን!

#INFOKEN_BOOKS_AND_INFORMATION_CENTER
Join us @infokenamu