Get Mystery Box with random crypto!

አ.ብ.ን ያጋጠመውን ችግር በውስጥ ለመፍታት ቢሞክርም እንዳልቻለ ተነገረ የዐማራ ብሔራዊ ንቅናቄ | Arat Kilo Media - አራት ኪሎ ሚዲያ

አ.ብ.ን ያጋጠመውን ችግር በውስጥ ለመፍታት ቢሞክርም እንዳልቻለ ተነገረ

የዐማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አ.ብ.ን) ያጋጠመውን ችግር በውስጥ ለመፍታት ቢሞክርም እንዳልቻለ የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ የሱፍ ኢብራሂም አስታወቁ፡፡

አቶ የሱፍ ፓርቲው ሊያካሂደው ያሰበውን ጠቅላላ ጉባዔ አስመልክቶ በፌስቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ‹‹ … አብን የሚያካሂደውን የሪፎርም ሂደት ባስቸኳይ ግልጽ፣ አሳታፊና ዲሞክራሲያዊ ማድረግ አለበት … በተለይ ከመነሻው የሪፎርም ጥያቄ ያቀረቡ አባላቱን በመግፋትና በማግለል በምትካቸው ተቀባይ ስብስብ ለመፍጠር የሚደረግ ሙከራ ትክክል አይደለም … ይህ የህዝብ ተቋም ጉዳይ ስለሆነ ልክ እንደግለሰብ ሰርግ የተወሰኑ ባለሟሎች በድብቅ ብቻ መክረው የሚቋጩት ጉዳይ አይሆንም … ችግሩን በቀላሉ በውስጥ ለመፍታት ብንሞክርም አልተቻለም›› ብለዋል።

የፓርቲው ዋነኛ ችግር ከፖለቲካ መስመር ጋር የተገናኘ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ የሱፍ፤ ችግሩ ሳይፈታ መቆየቱንና ተባብሶ መቀጠሉንም ገልፀዋል፡፡

አቶ የሱፍ፣ ሰፊ አባላቱን ለድጋፍና ለመዋጮ ብቻ የሚፈልግ ነገር ግን የሃሳብ ልዩነቶችን የሚፈርጅና የማያስተናግድ ተቋም በህዝብ ላይ ተጨማሪ እዳ ከመሆን ያለፈ ፋይዳ ሊኖረው እንደማይችል አመልክተው፤ ‹‹ለአመታት በየቀጠናው ስንባዝን የኖርነው ለህዝባችን መብትና ክብር ብለን ነው። ህይወታችንን አደጋ ላይ ጥለንና በፕላስቲክ ድንኳን ውስጥ እያደርን የታገልነው ለዋዛ ፈዛዛ አይደለም! በየሚዲያው በር ስንኳትን የከረምነውም የዝና ፍለጋ ተግባር ለማከናወን አይደለም›› ብለዋል፡፡

ሌላው የአብን አመራር ዶ/ር ቴዎድሮስ ኃ/ማርያም በበኩላቸው፤ አብን ጠቅላላ ጉባዔ ለማካሄድ ‹‹ድምፁን አጥፍቶ ሽር ጉድ እያለ›› እንደሆነ ገልጸው፣ ‹‹በያቅጣጫው የሚሰማው የጉባኤ ዝግጅት ድራማ አስቂኝም፣ አሳፋሪም፣ አስጊም ነው›› ብለዋል።