Get Mystery Box with random crypto!

#አስተውሉ! ብዙ ክርስቲያኖች በዚህ ዘመን ከቅዱስ ሥጋና ደሙ የሚርቁበት አንደኛው ምክንያት 'ከቆረ | Haile Gebriel Tube

#አስተውሉ! ብዙ ክርስቲያኖች በዚህ ዘመን ከቅዱስ ሥጋና ደሙ የሚርቁበት አንደኛው ምክንያት "ከቆረብን በኋላ እንደ መነኮሳት፣ እንደ ጻድቃን፣ እንደ ቅዱሳን" መኖር አለብን ብለው የሚያስቡት የተዛባ አስተምህሮ ያለበት ትምህርት በመኖሩ ነው፡፡ ማነው እንደዚህ ያለው? ማነው ከተቆረበ በኋላ ሁሉም የሕይወት መስመር ካልተቀደሰ አይቻልም ያለው? እንዲህ ያለው ትምህርት ዲያቢሎስን የሚያግዝ ቋንቋና ጠባይ የያዘ በመሆኑ ርኩሳን መናፍስት በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ የሚኖራቸውን ሥውር የአገዛዝ ዕድሜ የሚያራዝም ሲሆን ክፋትን የሚደብቅ ለመቀደስና ለበረከት ዘመን መዝግየት የድርሻውን የሚወጣ መናፍስታዊ እሳቤ ያለበት የክርስትና ጉዞ ላይ አረንቋ የሚሆን መሰናክል ነው፡፡

እስኪ የቅዱስ ጴጥሮስን ታሪክ ተመልከቱ፡፡ አንተ ዓለት ነህ ብሎት ነበረ በዚህ በማቴዎስ 16 ላይ፡፡ ከጌታም ጋር ሲወርድ ሲወጣ የከረመው ጴጥሮስ በመጨረሻውም ወቅት ላይ ከጌታ እጅ ላይ ቆረበ፡፡ ሊቀ ካህኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ባርኮ የሰጠውን ሥጋውን ቀድሶ ያቀረበለት ደሙን ከጓደኞቹ ሐዋሪያት ጋር ሆኖ እንደበላ እንደጠጣ በማቴዎስ 26፥26 ላይ ታገኝታላችሁ፡፡ ሥጋና ደሙን የተቀበለው ጴጥሮስ በክርስቶስ ተባርኮ ውስጣዊ ሕይወቱም ተቀድሶ ጌታውን ከኋላ ኋላ እየተከተለ ሲመጣ አይሁዶች "አንተም ከእርሱ ጋር ነህ!" ሲሉት ከአንድም ሦስት ጊዜ "የምትሉትን ሰው አላውቀውም!" አለና ሸመጠጠ፡፡

የሚገርም ነው አያችሁ፡፡ በእጁ ሥጋውን በልቶ? በእጁ ደሙን ጠጥቶ አላውቀውም? እንዴት ነው ነገሩ? ጴጥሮስ ቆርቦ ካደ፡፡ የሰው ልጅ ከቆረበ በኋላ ፍጹም ሕይወትን ሊመራ እንደማይችልና ወደነበረበት ኃጢአት ሊመለስ እንደሚችል ያው እዚህ ጴጥሮስና ሐዋሪያቱ አስተማሩ፡፡ አስቀድመው ሲያቅፉት፣ ሲከተሉት፣ ድንቅ ሥራውን ሲያዩ፣ ቃሉን በአንክሮ ሲሰሙ የቆዩት ሥጋና ደሙን ከተቀበሉ በኋላ ከባዱ ጊዜ ሲመጣ ሸሹ፡፡ ወደነበሩበት ዓለም ሊመለሱ ወደኋላ ሸሹ፡፡ ዛሬ የንስሐ አባቶች፣ ካህናትና የእግዚአብሔር አገልጋይ ነን የሚሉ ሰዎች ወጣቱን ከሥጋና ደሙ ያርቁታል፡፡ "ተው ታጠፋለህ፣ ታርከሰዋለህ፣ ትቀሰፋለህ" እያሉ ትውልዱን ከሥጋና ደሙ አራቁት፡፡

እስኪ ልቁረብ ሲል ማነው "ቆይ፤ ገና ነህ፤ ትሰናከላለህ" የሚል መልስ ከሰዎች የማይሰጠው? ጫት ሲበላ ተው የሚል የለም፡፡ መጠጥ ሲጠጣ ተው የሚል የለም፡፡ ሥጋና ደሙን ልውሰድ ሲል ግን ብዙዎች ያንጎራጉራሉ፡፡ ለምን? ለምን ከሥጋና ደሙን ርቀን ሌሎችንም እናርቃለን? ጴጥሮስ ቆርቦ ሦስቴ ቢክድም የዶሮዋ ጩኸት አነቃው፡፡ ወደ ጌታም ቢመለከት ጊዜ፤ ዓይኖቹ ውስጥ በቀል የለም፡፡ ቁጣ የለም፡፡ ብስጭት የለም፡፡ ይልቁኑ በፍቅር መልሶ ያየዋል፡፡ ያኔ ጴጥሮስ ውስጡ ቢናወጥበት ግዜ፤ ትሕትናው ከአቅሙ በላይ ሲሆንበት ጊዜ፤ የዋህነቱ መሸከም ከሚችለው በላይ ሲሆንበት ጊዜ፤ ራሱን አሳለፈና ሰጠው፡፡ ተሽሽጎ አለቀሰና "አባት ሆይ ይቅርታ አድርግልኝ!" ሲል ምሕረትን ለመነ፡፡ ንስሐ ገባ ማለት ነው በቃ፡፡

ከዚያ ጴጥሮስ ምን ሆነ? የዮሐንስ ወንጌል ምዕ.21 ላይ የሚከተለውን ቃል ታገኛላችሁ፡፡ 15፤ ምሳ ከበሉ በኋላም ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን? አለው። አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ግልገሎቼን አሰማራ አለው። 16፤ ደግሞ ሁለተኛ። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። 17፤ ጠቦቶቼን ጠብቅ አለው። ሦስተኛ ጊዜ። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። ሦስተኛ። ትወደኛለህን? ስላለው ጴጥሮስ አዘነና። ጌታ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ኢየሱስም። በጎቼን አሰማራ።

ከአንድም በሁለትም በሦስተኛውም አስቀድሞ ደጋግሞ ከድቶ የነበረውን ቅዱስ ጴጥሮሰ፤ ቂም የማያውቀው ጌታ
"ትወደኛለህን?" አለው፡፡ ከዚህ በፊት በአስቸጋሪው ወቅት አላውቀውም ሲል የነበረው አገልጋይ፤ እዚህ ከንስሐ
በኋላ ቋንቋው ተቀየረና "እንድወድህ አንተ ታውቃለህ" ይለው ጀመረ። ፍቅሩንም ሕይወቱንም አሳልፎ ሰጠው፡፡ በቃ "አንተ ታውቃለህ አባት ሆይ" አለው፡፡ ሁለተኛም ጊዜ ትወደኛለህን? ሲለው እንድወድህ ታውቃለህ እያለ ፍቅሩን እያረጋገጠ መመለስ ጀመረ፡፡ ሦስተኛው ላይ "ትወደኛለህን?" ቢለው፤ የተጠራጠረው መሰለውና አዝኖ
"ጌታ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ ፍቅሬንም ታውቀዋለህ" አለው፡፡ ሁሉን የሚያውቅ ብሎ አዶናይነቱን እዚህ መሰከረ፡፡

በቀያፋ ግቢ ሦስት ጊዜ "አላውቀውም!" ሲል የቆየው ሐዋሪያ አሁን ሦስት ጊዜ "እንድወድህ ታውቃለህ" ማለት ጀመረ፡፡ ቆርበንም ብንከዳው በይቅርታ እጁ የሚስብ አምላክ ነው ኢየሱስ ክርስቶስ፡፡ ቆርቦ የካደው ጴጥሮስ ዳግም በንስሐ ተመልሶ "እንድወድህ ታውቃለህ" ላለው ጌታ እውን እስከ ነፍሱ መጨረሻ ታምኖ ስለ ስሙ ተንገላቶ፤ ስለ ስሙ መከራን ተቀብሎ፤ ስለ ስሙ ወጥቶ ወርዶ፤ አእላፎችን በስሙ አጥምቆ፤ በአንድ ቀን ስብከት ሦስት ሺህ ሰዎችን መልሶ፤ አእላፍ ደቀመዛሙርትን አፍርቶ፤ ስለ ስሙ ተገድሎ እውነትም የቤተክርስቲያን የዓለት መሠረት ሆኖ ርዕሰ ሐዋሪያት ቅዱስ ሆኖ አለፈ፡፡

ስለዚህ የክርስቶስ ሥጋና ደም ኃጢአትን የሚያስተሠርይ ነው እንጂ ፍጹም የሚያደርግ አይደለም፡፡ አስተውሉ ውድ ቤተሰቦቼ።

#ጸባኦት_ይከተላችሁ!!

NatnaelSolomon

@haile_gebriel_tube_bot
@haile_gebriel_2021