Get Mystery Box with random crypto!

እንሂድ ያልኩት ወደሚቆረቆርለት አደራዬ ነው ወደሚለው ሰላቱ አትጨቅጭቀኝ ያለው እሱ!  እንዴት ነው | ሀበሻዊ ጥበባት

እንሂድ ያልኩት ወደሚቆረቆርለት አደራዬ ነው ወደሚለው ሰላቱ አትጨቅጭቀኝ ያለው እሱ!  እንዴት ነው በአንድ ጊዜ ሁለት ነገር የሚኮነው? ባለአደራ እንደዚህ ነው እንዴ? ባለ አደራ አደራውን አስበልቶ በል አደራህን ተው ቢሉት በተበላ አደራ እንዴት እንደዚህ ትለኛለህ እንዴት ይላል?

ንፁህ የኩሬን ውሀ አደራ ብለውት እንደሄዱት የኩሬዋ ባለአደራ መሰለኝ ንፁኋን ኩሬ አደራ ጠባቂው ሳይንከባከባት የሚሞላትም ፈጣሪዋ ሆኖ እሱ ቅንጣት ታህል ሳይጠብቃት ያም እየመጣ ሲያደፈርሳት ሲያቆሽሿት  ኖሮ ኖሮ አንድ ቀን አንድ ገዢ ብቅ ብሎ ኩሬህን በሴኩላር ይሉት አፈር ደፍኜ ፎቅ ልሰራ ነው እና ከዚሀ በኋላ እዚህ መጠበቅ አትችልም ቢለው እንዴት ነው ቀኝ አዝማቼ አካኪ ዘራፍ ያለው ባለ አደራውስ ጉዱን ያየ እንደሁ እንዴት ያዝን ያችን የቀልቡን መርጊያ ኩሬ ማቆሸሹን ዝም ቢል መድረቋንም ሞይውን ተማምኖ ቢታገስ ለማዳፈን እንዳሰፈሰፉ ቢያይ……………ማን ነው ቀኝ አዝማቼን ያናደደብኝ ሰላትህን ተው ያለው ማን ይሆን? ባለ ሴኩላሩ ነው ወይስ ውስጥ እራሱ?

መልክህ እኮ ያበደ ነው! ቆንጆ ነህ! ወንዳ ወንድ! ምንም ብታደርግ ያምርብሀል! ደግሞ በዚህ ምላስህ እትት ብትልበት… በዚህ መልክህ ብትጠቀም… ፈጂ ነበር የምትሆነው። ብለው የሀሳብ ጥንስስ ሲጠነስሱበት ለመጠንሰሻነት ሲስማማ እና አደራውን በገዛ እጁ ሲተዋት ምነው እንደዚህ አልተብሰከሰከ?

በኋላ እንሰግዳለን ይሄን moment የትም አናገኘውም ብለው በሞመንት ሲያታልሉትና አደራውን በሞመንት አጣብቀው ሲያጐርሱት ምነዋ አደራው አላነቀው? የዛኔ የበላው አደራ ዛሬ ግድ የለህም ከተውክ አይቀር ትምህርት ቤትም ተዋት ሲባል የአባቶቼ አጥንት እሾህ ሆኖ ይውጋኝ አለሳ ማን ነው ወንድሜን ያስቆጣው?


ይህንን እያምሰለሰልኩ በምን ሰዐት መስጅድ ገብቼ በምን ሰዐት ሰላት ጀምሬ ስንተኛው ረከዐ ላይ እንደሆንኩም ማስታወስ ተሳነኝ ብዙም ሳንቆይ አሰላመትን ።

ከአዝማቾቼ በላይ ተናድጄ ከመስጅድ ወጣሁ ቆይ የእኔ መምጣት ከቀኝ አዝማቼ አለመምጣት በምን በለጠ የእርሱ መቅረት አይሻልም ወይ? ማን ፈራጅ አደረገኝ የራሴን ጉድፍ ሳላጠራ ገብቶ ያልገባ ጠርቶ ያደፈ ሸቀን የወረረው ቀልብ ይዤ ለመፍረድስ ይሁን እንዴት ባለአደራ ነኝ ብዬ አደራ ልወጣ እላለሁ በዚህ ቀልብ ነው እንዴ አደራዬን እንድወጣ የተሰጠኘ?


በተንሸራተተ ሂጃብ ተጀቡኖ በተንሸራተተ ልብ ተወሽቆ በሸቀነ እና ባዳፋ ቀልብ ተሽሞንሙኖ ወደሌላ አካል መጮህ ምን የሚሉት ብሂል ነው? ቀድሞ ውስጥ ላይ መጮህ ነው ቀድሞ እሪታን ዋይታን ከራስ መጀመር ነው ዋይ ቢሉ ዋይታ የገደል ማሚቶ እንዳይሆን ቀድሞ ነው ለዋይታ ቦታ መምረጥ ዋይታው ውስጣችን ላይ ቢጀምር የዛኔ በዝምታም ቅጣት ባዘነብን ነበር!!!

አሁንም ጀሰዴ እየተነዳ ቤቱ ለመድረስ በየት በየት እንደመጣ ምን ያህል ጊዜም እንደፈጀበት አላወቅኩም ብቻ በሩን ከፍቼ ስገባ ቀኝ አዝማቼም ግራ አዝማቼም አሰላለፋቸውን እና ሁኔታቸውን እንደጠበቁ ተቀምጠዋል። በማን በምን እንደተቆጣ ባላውቅም በተቆጣ አንደበት አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ? አልኩ በመሰላቸት እሺም እምቢም ሳይሉ ለአፍታ አይናቸውን ገርበብ አድርገው አስተዋሉኝ…

ቆይ ቆይ የትኛውን ሰላት ነው አደራ የተሰጠን? የትኛውንስ ሰላት ነው የተከለከላችሁት? ማንስ ነው የከለከላችሁ? አንቺስ የትኛውን ሂጃብሽን ነው አውልቂ ያሉሽ ለይተሽዋል? ለምንስ ነው አውልቂ ያሉሽ? ከምንስ ተነስተው እንደዚሀ አሉሸ? ብዬ ስጨርስ ሁለቱም ተያይተው ምፅ ብለው አዝነውልኝ ይሁን ምን ባላውቅም አንገታቸውን ግራ እና ቀኝ አወዛውዘው ወደ ስልክ ተመስጧቸው ተመለሱ።


ጫማዬን አውልቄ ልገባ ሳኮበኩብ የግራ አዝማቼን ድምፅ ሰማሁ እህቴ ሂጃብሽ ውበትሽ እያለች ድምፇን ወደማላውቃቸው ሰዎች እየቀረፀች መሆኑ ገባኝ ። አስከትሎም ቀኝ አዝማቼ ቀጠለ ወንድሜ በሰላት ቀልድ የለም አደራችን ናት አለ። ውስጠቴም እንደዚህ አለኝ አይ ሀበሽ አንተም እኮ ሰገድኩ ብለህ ሞተሀል አልቀረብህም ብሎ ተሳለቀብኝ።

ወይ አደራ ወይ ምክነት የተንሸራተተ ልብ አንግበን በተንሸራተተ ሂጃብ ጉዞ ወዴት ይሆን?

የትኛውን ሰላት ይሆን አደራ የተባልነው? የትኛውንስ ይሆን የከለከሉን? ለምንስ ይሆን የከለከሉን?



@Habeshistan