Get Mystery Box with random crypto!

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከህዳር 22 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በአሮጌው የብር ኖት መገበያየት እን | Habesha news🇪🇹🇪🇹🇪🇹🇪🇹

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከህዳር 22 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በአሮጌው የብር ኖት መገበያየት እንደማይቻል ገልጿል፡፡
በባሕር ዳር ከተማ ግብይት እንዴት እየተፈፀመ እንደሚገኝ አብመድ ቅኝት አድርጓል፡፡
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 22/2013 ዓ.ም (አብመድ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከህዳር 22 ጀምሮ በነባሩ የብር ኖት መገበያየት እንደማይቻል አስታውቋል፡፡
የብር ኖቶቹ በባንክ ቤት እንዲቀየሩ መመሪያ ቢያስተላልፍም ጥቂት የማይባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተገበያዩበት መሆኑን አብመድ ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ገበያ ባደረገው ቅኝት መታዘብ ችሏል።
በባሕር ዳር ከተማ አዲሱ የብር ኖት በአብዛኛው በግብይት ላይ እየዋለ ቢገኝም በግብይት ላይ እንዳይውል መከልከል በጀመረበት በዛሬው ዕለት ግን አሮጌው የብር ኖትም ሥራ ላይ እየዋለ ነው፡፡
አቶ ሰርጉ አክሊሉ የሚተዳደሩት በንግድ ሥራ ዘርፍ ነው፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ነባሩ የብር ኖት በገበያ ላይ እንደማይውል መረጃ ቢኖራቸውም ደምበኞቻቸውን ላለማስከፋት ብለው ሲቀበሉ መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡
የተሰጠው የቀን ገደብ ከመጠናቀቁ በፊት ነባሩን የብር ኖቶች መቀየር ስለሚችሉ ከደንበኞቻቸው እየተቀበሉ መሆኑን ነው አቶ ሰርጉ የተናገሩት፡፡ ደንበኞች በድጋሜ ሲመጡ አዲሱን የብር ኖት ብቻ ይዘው እንዲመጡ እየመከሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ሲገበያዩ ካገኘናቸው ውስጥ ወጣት ትዕግስት አለነ እንደተናገረችው "ከዛሬ ጀምሮ በአሮጌው ብር መገበያየት እንደማይችል መረጃው አለኝ፤ ለዚህም ነው አዲሱን የብር ኖት ለግብይት ይዤ ወደ ገበያ የወጣሁት" ብላለች፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባሕር ዳር ተወካይ ጥናትና ምርምር ባለሙያ አቶ አንተነህ ገረመው ኅብረተሰቡ የቀሩት ቀናት ውስን ስለሆኑ ሳይዘናጋ አሮጌውን የብር ኖት ወደ ባንክ በማምራት እንዲለውጥ አሳስበዋል፡፡
አሮጌውን የብር ኖት በአዲሱ የብር ኖት ለመቀየር መንግሥት ሦስት ወራትን የሰጠ መሆኑ ያስታወሱት ተወካዩ ከዛሬ ጀምሮ ኅብረተሰቡ በነባሩ ብር ግብይት መፈጸም ሳይሆን ወደ ባንክ ቤት ሄዶ መቀየር እንደሚገባውም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡