Get Mystery Box with random crypto!

#ወቅታዊ (ክፍል 1) መካሪና ሰባኪ በዝቷል። ከመገናኛ እስከ ኢኒስታግራም፤ ከዩትዩብ እስከ ድ | GOFERE BUSINESS TIPS 💰

#ወቅታዊ

(ክፍል 1)

መካሪና ሰባኪ በዝቷል። ከመገናኛ እስከ ኢኒስታግራም፤ ከዩትዩብ እስከ ድልብ መጻሕፍት፣ ከመድረክ እስከ ታክሲ...!

የሁሉም መልዕክት አንድ ነው፤ ‘የብልጽግና ባቡር ቀርባለችና ተሳፈሩ’ የሚል። በየዓመቱ መቶ ሺዎች እየተመረቁ ሥራ ያጣሉ። ‘የሥራ ፍጠሩ’ ሰባኪዎች ይቀበሏቸዋል። በስንት ደጅ ጥናት የተገኘን ሥራ ‘ጥላችሁ ውጡ’ ይላሉ። ዛሬውኑ የራሳችሁ አለቃ ሁኑ እያሉ ያስጎመዣሉ።

ከእጅ ወደ አፍ ቀርቶ፣ እንደ ወፍ- ከአፍ ወደ አፍ በሆነ የዛሬ ኑሮ፣ ‘ከቆጠባችሁ ከነገ ወዲያ ሚሊዮነር ትሆናላችሁ’ ይላል።

አነቃቂ መጻሕፍት ሕይወት ይለውጣሉ! የመድረክ ዲስኩሮች ያበለጽጋሉ? አንዳንዶች ‘አዎና! እኛን ነው ማየት!’ ይላሉ። ሌሎች ደግሞ በአነቃቂ መጻሕፍት የሚለወጥ ሕይወት ካለ የደራሲውና የዲስኩረኛው ብቻ ነው ብለው ያፌዛሉ። በሁለቱም ጎራ የካበተ ልምድ ያላቸውን አሰልፈን ጉዳዩን ብናብላላውስ?

ዶ/ር ወሮታው፡ “የአንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያንን ሕይወት ለመለወጥ እየሠራሁ ነው”

በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ግንኙነት ሦስተኛ ዲግሪ አላቸው። የእርሳቸው ሥራ ግን የሰዎችን አእምሮ ከብልጽግና ጋር ማዋደድ ነው። ወጣቶችን ወደ ሃብት ማማ ማውጣት። የትኛውንም አእምሮ በመግራት ስኬትና ልዕልናን ማጎናጸፍ ይቻላል ብለው ያምናሉ።
እንደተመረቁ የከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት ተቀጠሩ፣ ከዚያም ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ አስተማሪ ሆኑ።

ከዕለታት አንድ ቀን “ሕይወቴን የሚለውጥ አጋጣሚ ተፈጠረ” ይላሉ ዶ/ር ወሮታው። ቀንና ወሩን ሁሉ አይረሱትም። 1992 ዓ.ም. ነሐሴ ከዩኒቨርስቲው ለስልጠና ተላኩ። አሰልጣኞቹ ከጋና የመጡ ነበሩ። የሥልጠና ማዕከሉ ‘ኢንተርፕራይዝ ኢትዮጵያ’ ይባል ነበር። ሥልጠናውን ሲጨርሱ ከባድ የአስተሳሰብ ነውጥ ገጠማቸው። የአስተሳሰብ ነውጡ፣ የሕይወት ለውጥን አስከተለ።

“በዚያች ቅጽበት የራሴን ነጻነት አወጅኩ፤ ከዚያ በኋላ በጭራሽ አልተቀጠርኩም፤ በጭራሽ!” ይላሉ።

“ተቀጥሮ መሥራት አንገሽግሾዎት ስለነበር ነው ዶ/ር?"

“አይደለም፤ በዚያች ቅጽበት የምኖርለትን ሕልሜን ስላገኘሁ ነው።”

"የሚኖሩለት ሕልም ምንድን ነበር?"

“ማሰልጠን፤ ባለጸጎችን ለኢትዮጵያ ማፍራት።”

“የምር ይሳካል ብለው ያምናሉ?”

“ያለጥርጥር! አንድ ሚሊዮን ባለጸጎችን ለኢትዮጵያ እናፈራለን።”

“መቼ ነው ይህን ሁሉ ሰው ባለጸጋ የሚያደርጉት?”

“የዛሬ 20 ዓመት፤ በነሐሴ 2023 ዓ.ም።”

ዶ/ር ወሮታው ይህን የሚሉበት እርግጠኝነት የእምነታቸውን ጥንካሬ ያሳብቃል። እንዴት ያለ ሥልጠና ቢሆን ነው?

“...በዚያ ሥልጠና ወሮታው ላይ ሳቅኩበት፤ ወሮታውን ነጻ አወጣሁት። ለሕልሜ ታማኝ እንድሆን፣ ሃብቴ አስተሳሰቤ እንደሆነ፣ የማምንበትን እየሠራሁ እንድኖር ያደረገኝ አጋጣሚ ነበር።”

የእሳቸው ሕይወት በአንድ ሥልጠና ከተለወጠ የሌሎች ሕይወት ለምን አይለወጥም?

ናትናኤል ፋንታ፡ “የሞቲቬሽን ሥልጠና በብድር መደሰት ማለት ነው”

‘ናትናኤል ሜሞሪ’ በሚለው የንግድ ስሙ ድፍን በርካቶች ያውቀው ይሆናል። የሕይወቱን እኩሌታ በአእምሮ ሥልጠና ላይ አሳልፏል። ናትናኤል በተለይ በማስታወስ ጥበቡ በ90ዎቹ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ እየቀረበ ብዙ ሰዎችን ሲያስደምም አንዳንዶች ዛሬም ድረስ ያስታውሱታል።

ናትናኤል ከማስታወስ ጥበብ በኋላ በቀጥታ ወደ ‘ሞቲቬሽን’ [ማነቃቃት] ተሸጋገረ። ብቻ በጥቅሉ ባለፉት በ21 ዓመታት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ከአእምሮ ጋር በተያያዘ አሰልጥኗል።

የእሱን ልብ አንጠልጣይ ‘ሞቲቬሽን’ ቃል ለመስማት ብዙዎች 22 አካባቢ ደጅ ጠንተዋል።

እሱም ያንን ዘመን በመለስተኛ ፀፀት እያስታወሰ፣ “...ሙሉ ጉባኤ ቁጭ ብድግ አስደርግ ነበር” ይላል።

አሁን ግን ፍጹም በተቃራኒው ቆሟል። የአነቃቂ ንግግሮች አድናቂ አይደለም። እንዲያውም ‘ሞቲቬሽን’ አይሠራም ሲል አውጇል።

“ከዚህ ሁሉ ዘመን በኋላ ያረጋገጥኩት አንድ ነገር ቢኖር የሰዎችን ሕይወት ለመለወጥ ትክክለኛው መንገድ ያ እንዳልነበረ ነው” ይላል።

ለምን? በ21 ዓመት ውስጥ ምን ተፈጠረ? ትክክለኛው መንገድ ያ ካልሆነ ታዲያ የቱ ነው?
በዓመታት ጥናት ደረስኩበት የሚለውን ይነግረናል።

የአነቃቂ መጻሕፍት አጭር የሕይወት ታሪክ

ራስ አገዝ መጻሕፍት፣ የይቻላል ዲስኩሮችና መሰሎቻቸው በጅምላው ‘ሰልፍ ዴቨሎፕመንት ኢንዱስትሪ’ ውስጥ ይከተታሉ። በአሜሪካ በአንድ ወቅት ከሙዚቃ ኢንዱስትሪው ቀጥሎ ሚሊዮን ዶላር የሚያንቀሳቅስ ዘርፍ ነበር። በተለይ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ወዲህ።

የአነቃቂ መጻሕት አባት የሚባለው ቻርልስ ሃናል ነው። ኋላ የመጡት ገናናዎች የእርሱ ደቀ መዛሙርት ናቸው። በዘመኑ የጻፈው ነገር አእምሮን የሚያሸፍት ነበር። “…ኋላ ላይ እንዲያውም ቤተ ክርስቲያን መጽሐፎቹን ለቅማ አቃጥላበታለች” ይላል ናትናኤል።
ከእርሱ በኋላ አብረሃም ማስሎው መጣ። “አእምሮን በመግራት ማንም ሰው ምንም መሆን ይችላል” ብሎ ተነሳ። ቀስ በቀስ ሞቲቬሽን ከቤትና ከቢሮ ወጥቶ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ሰተት ብሎ ገባ። የይቻላል መንፈስ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንቀጾች ጋር ስምም ሆኖ በሰባኪዎች አንደበት ተነገረ። ሚሊዮኖች በተስፋ ራሳቸውን ሳቱ። ያለስስት ጥሪታቸውን ለሰባኪያን ሸለሙ። ከአፋቸው ማር ጠብ የሚልልላቸው ሰባኪየን መቅደስ ጠበባቸው። በቲቪ መስኮት መጡ። ‘ቴሌቫንጀሊስቶች’ ተወለዱ። በስብከት ጉባኤ መዋጮ የግል ጄት ገዙ። ምዕመናን የታክሲ እያጡ፣ እየነጡ መጡ። ካፒታሊዝም ፋፋ። የገበያ ትንቅንቅ ተፈጠረ። ‘ሞቲቬሽን’ ሽያጭን የሚያስመነድግ ሁነኛ መሣሪያ እንደሆነ ተደረሰበት። ሰዎች የስቶክ ማርኬት የድርሻ ገበያ እንዲገዙ ማሳመን ፈተና ሆኖ ነበር። ለዚያም ነው በሞቲቬሽን አእምሯቸውን ማጦዝ፣ በተስፋ ካውያ ማጋል አስፈላጊ ሆኖ የተገኘው። እንዲህ እንዲያ እያለ በ80ዎቹ እና በ90ዎቹ የሞቲቬሽን ኢንዱስትሪ ጣሪያ ነካ። ደራሲያን ሚሊዮን ቅጂ መሸጥ ጀመሩ። በእኛም አገር ‘ኔትዎርክ ማርኬቲንግ’ በስፋት ዘልቆ ገባ።

የ’ጎልድ ኩዌስት’ ዘመን፣ የፒራሚድ ገበያን ለማሳለጥ ሁነኛ የ’ሴልስ’ ስትራቴጂ ኾኖ አገለገለ። ሐኪሞች ሆስፒታልን፣ መምህራን አስኳላን ጥለው ወጡ፤ ወደ ሀብት ይወስዳል የተባለው አውራ ጎዳና በሕዝብ ታመቀ፣ተጨነቀ። ብዙዎች “አይቤን ማን ወሰደው”ን እያነበቡ አይባቸውን ፍለጋ ባዘኑ። አንዳንዶች አገኙት። ብዙዎች አጡት።
ናትናኤል ያን ዘመን የነበረውን አስደማሚ መነቃቃት ሲያስታውስ፣ “አዳራሽ ውስጥ ‘I believe I can fly’ የሚል ሙዚቃ ተከፍቶ ሰዎች በተስፋ ብቻ ሲያለቅሱ አይቻለሁ’ ይላል። ይህን ነው እሱ “የብድር ደስታ” የሚለው። ምን ማለቱ እንደሆነ ቆየት ብሎ ያስረዳናል።

(ይቀጥላል...)

#investorscafe #investors #investment #ethiopia #ethioinvestors

@investorscafethiopia