Get Mystery Box with random crypto!

በመስዋዕትነቱ ልክ ብስለት ያስፈልጋል! ባለፈው አንድ አመት ገዥዎቹ አማራውን በሀሰት በክፉ ጎን | Getachew shiferaw

በመስዋዕትነቱ ልክ ብስለት ያስፈልጋል!

ባለፈው አንድ አመት ገዥዎቹ አማራውን በሀሰት በክፉ ጎን ለማሳየትና ለመድፈቅ ያደረጉት ጥረት እንዳይሳካላቸው የተደረገውን ያህል በሂደቱ በርካታ መስዋዕትነት ተከፍሏል። አገዛዙ በጥላቻ በርካታ ሕዝብ ጨፍጭፏል። በርካቶች ተሰውተዋል። የምናውቃቸው የፋኖ አመራሮች፣ ቤተሰቦቻቸውና ጓዶቻቸውን ገብረውበታል። ሕዝባችን በርካታ ውጣ ውረድ አይቷል። በአማራው ላይ የተፈፀመው ወረራና የአማራው ተቃውሞ በብልሃት ከተኼደበት ለሌሎች ተስፋ በርካታ ጊዜ ታይቷል። ይህ የሚሆነው ግን ትግሉ በዋጋው ልክ ስሌት የደረገበት ሲሆን ነው።

1) ትግሉ የህልውና እንደመሆኑ መረር ያለ ግምገማ ያስፈልገዋል። አፍኖ ቆይቶ ግለሰቦች ወይ ቡድኖች ላይ መዝመት አያዋጣም። የሚያዋጣው አጠቃላይ አካሄድን መገምገም ነው። ለአብነት ያህል ብልፅግና ህዝብ ላይ ከሚያደርሰው ጥቃት ባለፈ ፕሮፖጋንዳው ላይ በርትቷል። የሚጠላውን ሕዝብ እየሰበሰበ ነው። ከአማራ ክልል አልፎ ለይምሰልም ይሁን በተግባር በውጭ አገር ጭምር ስብሰባ እያደረገ ነው። እንዴት? ለምን? ተብሎ መጠየቅ አለበት። በፖለቲካ "ይታወቃልኮ"፣ "ምንም አያመጣም" ወዘተ የሚሉ ማቃለያዎች፣ ጥቅል ፍረጃዎች ትግልን ገዳይ ናቸው። ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ ብቻ ማሳበብም የእለት ማስተንፈሻ ነው። ትግል እንደ አጠቃላይ በየጊዜው ይገመገማል። ግምገማ የኢህአዴግም፣ የብልፅግናም አይደለም። የትግል ማከሚያ ስልት ነው!

2) መሬት ላይ ያሉትን አንድ ካልሆኑ እያለ የሚጨነቀው፣ የሚወቅሰው የማህበራዊም ሆነ የሌላው ሚዲያ አካል ራሱ ዕዝ ሊኖረው ይገባል። መሳሪያ ከያዙት፣ ውጊያ ላይ ከሚውሉት፣ ብዙ የመነጋገር እድል ከሌላቸው ይልቅ ሚዲያ ላይ ያለው የመነጋገር እድልም አቅምም አለው። ለየራሱ ሰበር ዜና፣ ለየራሱ አጀንዳ ያልተናበበ አካሄድን እየመረጠ፣ በግምትና ባልተሰላ መንገድ እየሄደ መሬት ላይ ያሉት አብረው ቢሰሩ እንኳን ትግሉን የሚያበላሸው የሚዲያ ትርምስ ነው።

3) ትግሉ የህልውና ነው ካልን፣ ስለ አራት ኪሎ ካሰብን የከበደ ነገር የሚገጥመን ጠላት ካልነው ኃይል ብቻ አይደለም። የመጀመሪያው ፈተና ለዛ አላማ ብቁ ለመሆን ራስን መግዛት ነው። በዛ አላማ ልክ ራስን ማስተካከል ነው። ባለፉት ወራት የተወሰኑ ምክሮችን ፅፌ ነበር። ትግል ላይ ያሉ አካላት አማራ ውስጥ ያሉትን ኃይሎች ለመያዝ ዋጋ መክፈል ካልቻሉ እንቅፋት የከበደ ይሆናል። ለአብነት ያህል የሀይማኖት አባቶች ጋር ያለው አንዱ ነው። ሚሊሻ ሌላኛው ችግር ሆኗል። እነዚህ አካላት ጋር ተቃርኖ በጨመረ ቁጥር ብልፅግና ቦታ ያገኛል። ጦርነት ነውና የግዳቸውን ወገን ይፈልጋሉ።

የሰፈርህን ሚሊሻ ሳታሳምን የብሔር ድርጅቶች ጋር ተስማምተህ አገር ልትመራ አትችልም። ሚሊሻ ጓዶቻችን ስለገደለ፣ ስለሚጠቁም ወዘተ በብስጭት ካየነው ሌላ ጉዳይ ነው። የሌላ ብሔር የመከላከያ አባላት መርሯቸው መሳሪያ ሸጠው እየጠፉ ሰው በሰው የምታውቀው፣ ሰፈሩ የሚደበደበው፣ ራሱም ደጋፊ ነህ ተብሎ ሲገረፍ የከረመው፣ ክብር የማይሰጡትን ሚሊሻ ጋር የሚኖረውን ነገር ቁጭ ብሎ ማጤን ያስፈልጋል። አራት ኪሎን የሚመለከት ሚሊሻ የሚባልን እንቅፋት ማለፍ ካልቻለ ለአገዛዙ ምቹ መሆኑ ነው። እርስ በእርስ እያታኮሰ፣ የማህበረሰብ ደም እያቃባ ጊዜ ይገዛል። ትግሉን አራት ኪሎ ድረስ ያደረገ ሌላ አዋጭ አማራጭ መፈለግ አለበት። ዝርዝር ግምገማ ያስፈልገዋል።

በገጠር ያስቸገረን ባላንጣ አንድ አድርጌው ቤቴም ይፈርሳታል ብሎ የሚወስን አለ። የግል ጠብ ሲሆን ነው። ይህኛው አላማ ግን ቤት የመስራት ነው። ስርዓት የመስራት ነው። ይህን ለማድረግ የተነሳ አካል አካሄዱን ማጤን አለበት። የአማራን ጥያቄ ለሚሊሻው አስረድተን፣ ጥያቄውን ካልተረዳም ከእኛ ጋር የሚሆንበትን መንገድ ካልቀየስን፣ ካልሆነም የከፋው ጠላቱ ሌላ መሆኑን ማሳየት ካልቻልን ትግሉ ትርምስ ውስጥ ይገባል። ሚሊሻው በርካታ ቁጥር ያለው ነው። ከፋኖ አባላት ጨምሮ ዘመዶች አሉት። ከአርሶ አደሩ በክፉም በበጎም ይቀርባል። እጅግ አደገኛው ደግሞ አንዳንዴ በሚሊሻውና መሳሪያ በያዘው አርሶ አደር መካከል ያለው ድንበርም ቀጭን መስመር ይሆናል። በዚህ በኩል አንዳንድ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች እየታዩ ነው። ባለፈው ጦርነት ሚሊሻ ተብሎ የዘመተ አርሶ አደር፣ አገዛዙ መሳሪያውን እንዳይቀማው ስብሰባ የሚሄድም ሆነ ሌላው እና ዋናው ሚሊሻ ጋር ያለው ልዩነትንና ድንበር የሚጠፉበት ሁኔታ ይኖራል። ከዚህ ሁሉ አንፃር ከትግሉ ዋጋና አስፈላጊነት አንፃር መረር ያለች ግምገማ፣ ጥናት፣ ምክክር ያስፈልጋል። ከእርስ በእርስ ጭቅጭቅና መፈራረጅ ይልቅ የውስጥ ኃይል አሰላለፍ ላይ ሰከን ብሎ፣ ከብስጭት ወጥቶ ማሰብ ያስፈልጋል። ሕዝብ ሲወደውና ሲያደንቀው የነበረው ኢሕአፓ በተወሰኑ አባላቱ፣ ከዕዝ ባፈነገጠ መንገድ፣ በብስጭት እርምጃዎች፣ በመሰላቸት፣ ፍረጃ ወዘተ ሕዝብ ጋር ተቃርኖ መግባቱን መተለያዩ ሰነዶች አንብበናል። ከቆየውም ከአሁኑ ተጨባጭ ሁኔታም መማር ያስፈልጋል።

መስዋዕትነት ብቻ ድል አያመጣም፣ ጀግንነት ብቻውን አሸናፊ አይደለም፣ ብልጠት፣ ብስለት፣ ጊዜውን የዋጀ ግምገማ፣ የውስጥ ኃይልን ማሰባሰብ፣ ጠላትን መቀነስ ለድል ያበቃል። ጀብዱ ብቻውን አላማን አያሳካም። ከብስጭት ያለፈ አካሄድ ግድ ይላል። ትግሉ የተከፈለበትን ዋጋ ያህል ብልጥነትና ብልሃት፣ ጥንቃቄም ያስፈልገዋል።