Get Mystery Box with random crypto!

አንድ ዜና! በርካታ አጀንዳዎች! አጀንዳ 1፦ የትግራይ ርሃብን ጉዳይ ለማጣጣል ብልፅግና ከፍ አ | Getachew shiferaw

አንድ ዜና! በርካታ አጀንዳዎች!

አጀንዳ 1፦

የትግራይ ርሃብን ጉዳይ ለማጣጣል ብልፅግና ከፍ አድርጌ ሰቀልኩት ያለው አጀንዳ ነው። "እርዳታ እየላክን ነው። ከእርዳታ አልፎ የልማት ስራ ላይ ተሰማርተናል። እንደ ሌሎች ክልሎች ትግራይ የገበታ ለሀገር ..ተጠቃሚ ሆናለች" እያሏቸው ነው።

አጀንዳ 2፦

ጌታቸው ረዳ ሲያጣጥለው የነበረውን "ገበታ ለሀገር" ወዘተ ደስ ብሎት ሊያስተዋውቅ አይችልም። ጉብኝት ብለው የተገኙት መከላከያ ሚኒስትሩና ደህንነት ሚኒስትሩ ናቸው። ሬድዋን የደቡብ አፍሪካው ስምምነት ለትህነግ/ህወሓት በሚጠቅም መልኩ እንዲተገበር ሲሰራ የቆየ ሰው ነው። ጌታቸው ረዳ ደግሞ ከስምምነቱ ውጭ ራያና ወልቃይትን እንሰጣችኋለን ተብሎ የተገባለት ቃል ስለዘገየ በትግራይ ፖለቲካ እየተንገበገበ ነው። ጌታቸው ረዳን "ሎጅ እንጎብኝ ብለን እናውራ" ብለውታል። በየቦታው የሚከተለው ደብረፅዮን ሳይሰማ ያደረጉት ነው። ጌታቸው ወደ አዲስ አበባ መጥቶ በቀጥታ ከአዲስ አበባ የተደረገ ጉዞ ነው። የደህንነት ሚኒስትሩ፣ መከላከያ ሚኒስትሩ ሎጅ ሲጎበኙ የሎጅ ዜና ብቻ እንዲመስል ፈልገው ነው። ጌታቸው ረዳ ለእነ ደብረፅዮን "ራያና ወልቃይትን አሳልፈው ሊሰጡን ነው" ብሎ ሪፖርት ያደርጋል። ደብረፅዮን በእሱ ላይም እንደሚያወሩ ቢገባውም ለጌታቸው ሰበቡ በቂ ነው።

አጀንዳ 3፦

በሎጅ ስም ስለራያና ወልቃይት ብቻ አይወራም። የትህነግ/ህወሓት የውስጥ ጉዳይም አለበት። ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የተገኘው ደብረፅዮን ቀርቶ ጌታቸው ረዳና አብርሃም በላይ ከፊት የሆኑበት መቀሌ ላይ ሲታኘክ እንደሚውል ግልፅ ነው።

አጀንዳ 4፦

በርሃብ ሰው ሞተብኝ፣ እርዳታ የለም እያለ መግለጫ ሲሰጥ የከረመው ጌታቸው ረዳ ነው። የሎጅ ስራንም ተራ ማጭበርበሪያ ሲል ከርሟል። ስብሃት ነጋ "የሲ አይ ኤ ወኪል ነው" እያለ የወረፈው ጌታቸው ረዳ "አሜሪካ" የሚል ቲሸርት ለብሶ የአብይን ፕሮጀክት በማስተዋወቁ ቤተ መንግስት አካባቢ "ከፊት አድርገን የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አስተዋዋቂ አደረግነው" ሲባል ይውላል። ወደ ትግራይ ይህን አጀንዳ ይዞ መሄድ የሚችለው ጌታቸው ረዳ ነው።

አጀንዳ 5፦

የአገራትና የተቋማት መሪዎች "የሰላም ስምምነቱ እየተተገበረ አይደለም። ወደ ግጭት ልትገቡ ነው" እያሉ ስጋት እየገለፁ ነው። ሰሞነኛ መግለጫዎች በአሜሪካና ሌሎች ዘንድ "ስጋት" ተብሎ ይገለፃል። ወደ መቀሌ ሲመላለሱ የከረሙት ዲፕሎማቶች በሙሉ ስጋት ይገልፃሉ። እነ አብይ ደግሞ "እጅና ጓንት ሆነን ልማት እየሰራን" ይሏቸዋል።

አጀንዳ 6፦

ትህነግ/ህወሓት ትግራይ በጦርነት ወደመች የሚለው ብልፅግና እኔ ተጠያቂ አይደለሁም ባይ ነው። ትግራይን የማውደም አላማ ቢኖረኝ ጦርነት እንደቆመ ሎጅ አልሰራልህም ነበር ይለዋል። በጦርነቱ ተፈፀመ ስለሚባለው ምርመራ እንዲደረግ ቢባልም አብይና ህወሓት በስምምነት አስቁመውታል። ይች ደግሞ መቀሌን እንደ በሻሻ አድርገናታል ለሚለው ማርከሻ ሆና በየጊዜው ዜና ትሆናለች።

አጀንዳ 7፦

ሀይማኖታዊ አጀንዳ አለው። እነ አብይ ለኦርቶዶክስ ሰራን ስለሚሉት ወይንስ ከእነ አብይ ጀርባ ያለው ወደ ትግራይ መግቢያ ጥሩ ፕሮጀክት ነው ስለማለታቸው ልፃፍ? ሰፊ ነው። ሌላ ቀን እመለስበታለሁ።

የደህንነት መስሪያ ቤቱ ኃላፊ፣ የመከላከያ ኃላፊ እንደ ቱሪዝም መስሪያ ቤት ኃላፊ "ሎጅ ጎበኙ" ተብሎ የተሰራው አንድ ዜና ቢሆንም በርካታ አጀንዳ ያለው ነው። ቁማሩ ብዙ ነው።