Get Mystery Box with random crypto!

ከአማራ ክልል ውጭ ይህን ጥያቄ ማን ሊያቀርብ ይችላል? የትሕነግ ቃል አቀባይ ሰሞኑን በሰጠው ቃ | Getachew shiferaw

ከአማራ ክልል ውጭ ይህን ጥያቄ ማን ሊያቀርብ ይችላል?


የትሕነግ ቃል አቀባይ ሰሞኑን በሰጠው ቃለመጠይቅ ስለወልቃይት ሴቲት ሁመራ የአማራ ክልል መንግስት ምን ያገባዋል ሲል ተደምጧል። ይህን የተናገረው ካለማወቅ ሳይሆን እውነታ ለመካድ ከመፈለግ እንጅ። እውነታው ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ሴቲት ሁመራ፣ ጠጋዴ፣ ራያ አለማጣ፣ ራያ ባላ፣ ራያ ወፍላ፣ አለማጣ፣ ከፊል አበርገሌ ወደ ትግራይ ክልል (በወቅቱ ክልል 1) የተካለሉት በሃይል ከመሆኑም በላይ የሽሽግግር መንግስቱን አዋጅ 7/1984 እንዲሁም የኢፌዲሪ ሕገመንግስት ስለክልሎች አወቃቀር አስመልክቶ አንቀጽ 46 (2) የተደነገገውን መርህ በጣሰ መንገድ በመሆኑ ነው።


ትህነግ ሕገወጥ ይዞታውን ለመጽናት ብዙዎች ገሏል፤ የዘር ማጽዳት ፈጽሟል፣ የሕዝብ ስብጥር ለመቀየር (demography reengineering) የሰፈራ ፕሮግራም አካሄዷል። የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት በአንቀጽ 46 (2) በግልጽ እንዳስቀመጠው ‘ክልሎች የሚዋቀሩት ‘በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነት እና ፈቃድ ላይ በመመስረት' ነው።


ሆኖም ግን እነዚህ አካባቢዎች ወደ ትግራይ የተካለሉትበት መንገድ (ሕገመንግስቱ ከመጽደቁ በፊት በሃይል መሆኑ የማይካድ ቢሆንም) በአንቀጽ 46 (2) የተቀመጠውን ሕገመንግስታዊ መስፈርት በጣሰ መንገድ ነው። ይህ ሕገመንግስታዊ መስፈርት ባይጣስ ኖሮ እነዚህ አካባቢዎች በአማራ ክልል ይካለሉ ነበር። በአጭሩ እነዚህ አካባቢዎች ወደ ትግራይ ተካለው የነበሩበት መንገድ የሕገመንግስቱን አንቀጽ 46 (2) የጣሰ ነው (የሕገመንግስቱ አንቀጽ 46 የሽግግር መንግስቱን በአዋጅ 7/ 84 መርህ እንዳለ ነው ያስቀመጠው))።

እናም የአማራ ክልል መንግስት እያለ ያለው እነዚህ አካባቢዎች በአማራ ክልል መካለለ ሲገባቸው በትግራይ ክልል መካለላቸው ኢሕገመንግስታዊ ስለሆነ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እነዚህ አካባቢዎች ወደ አማራ ክልል እንዲካለሉ በማድረግ ትህነግ በወቅቱ የነበረውን የሃይል የበላይነት ተጠቅሞ የፈጸመውን የሕገመንግስት ጥሰት ሊያርም ይገባል የሚል ነው። ታዲያ ይህን ጥያቄ ከአማራ ክልል መንግስት ውጭ ማን ሊያቀርብ ይችላል? ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ውጭ ይህ ጥያቄ ለማን ሊቀርብ ይችላል (ለነገሩ ትህነግ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እውቅና አልሰጥም ብሏል)።

(ዶ/ር ዮናስ ተስፋ)