Get Mystery Box with random crypto!

ስለምወድሽ ነው! (ፉአድ ሙና) . ረመዳን ሊደርስ ፣ የቀሩትን ቀናት ወደታች ‘ሚቆጥር፣ ከመስጂዱ | Fuad Muna (Fuya)

ስለምወድሽ ነው!
(ፉአድ ሙና)
.
ረመዳን ሊደርስ ፣ የቀሩትን ቀናት ወደታች ‘ሚቆጥር፣
ከመስጂዱ ቅጥር ተለጥፎ ካለው ፣ ሆድ የሚያስብስ ቁጥር፣
ከፊት ተገትሬ ፣ በቦዘዘ አይኔ ከገፄ ‘ምስልሽ፣
ትካዜ ‘ሚገባኝ ፣ በጥልቀት ሳስበው የስርቆቴ እንደሆንሽ፣
ልቤ ፍርሀት ወርሶት ፣ ሀዘን ‘ሚተኩሰው፣
ስለምወድድድሽ ነው!!
.
ላንቺ ያለኝ ፍቅር ፣ በይሁንታሽ ብርታት በድፍረት አብቦ፣
የጌታዬን ትዕዛዝ ፣ የጣሰው ያስጣሰሽ ፣ በወንጀል ተከቦ፣
በትዳር ሊያነፃሽ ፣ አቅም ቢደቁሰው ፣ እድሜ ቢሸብበው፣
ስህተቱን እያየ ፣የገባው ከጥፋት ፣አንቺን ከብዶት መተው፣
ለሌላ እኮ አይደለም
ስለሚወድድድሽ ነው።
.
ከመስጂዱ ቅጥር ፣ ቁጥሩ ላይ አፍጥጬ፣
ስለ‘ኔ እና አንቺ ፣ ወሰንኩኝ ቆርጬ።
ረመዳን ደርሶ ፣ መስፈሪያ ሲቀየር ፣ ስትታይ ጨረቃ፣
ኢድ እስከሚበሰር ፣ በተክቢር ተጠምቀን ፣ ፆሙ እስኪያበቃ፣
አይንሽን አላይም ፣ ድምፄን አትሰሚም ፣ መልዕክቴም አይደርስሽ፣
ወሩን ክበሪበት ፣ ከጌታሽ ታረቂ ፣ ይበተን ወንጀልሽ።
.
አዎን ታረቂበት!
የሺ ወራት ምንዳ በሚታደልበት፣
የወንጀል ቅጣቱም ከፍፍፍ በሚልበት፣
ህዝቡ ተሰብስቦ በእጥፍ ሲከፈለው ፣ ለሞከራት ስራ፣
በባዶ እንዳትወጪ፣ ከሳሪ እንዳትሆኚ ፣ ቀርበሽ ለመከራ፣
ባዳ ወንድ በማየት ፣ ወንጀልሽ እንዳይገዝፍ ፣ በልጦ ከተራራ፣
በተራውሂ ሰበብ ፣ወጥተሽ አታግኚኝ፣ አትደውዪ አደራ!
ልብሽ ክፉ አያስብ ፣ ሀሳቤን ተረጂ፣
ለነገ እጣፈንታሽ ፣ ብጠላ አይጨንቀኝም፣ ባፈቅር ነው እንጂ።
አማኝ በአንድነት ከትቶ ከመስጂዱ ፣ ሲዘረገፍ እንባ፣
የአላህ ቃል ሲነበብ ፣ እዝነቱ ሲንቧቧ፣
ምንዳ እንካችሁ ሲባል ፣ ያለ አንዳች ገደብ ፣ያለ ምንም ኮታ፣
አምልኮሽ ላይ በርቺ ፣ ስርዓቱን ጥሰሽ አታግኚኝ ማታ።
ከባሪያው መጠማት ፣ መራብ ግድ ከሌለው ፣ ከአንድዬ ተጋፍተን፣
በባዶ ሆዳችን ፣ ከአምልኮ ተናጥበን ፣ አንገናኝም ቀን፣
አደራ እንዳትረሺ!
አፈቀርኩኝ ያለ ፍቅሩን አይበድልም ፣ በልጦበት ጥማቱ፣
የእርሷ መደሰት ነው ፣ የሷ ደህንነት ነው ፣ የዘወትር ጭንቀቱ።
አፈቀርኩ ብያለሁ ፣ አንቺው ነሽ ስስቴ፣
ከአንቺ የነገ አለም ፣ አይበልጥም ስሜቴ።
መቼም አልረሳሽም ፣ ነገም ሌላ ቀን ነው፣
ይህን የምለው ግን፣ አደራ እንዳትረሺ
ስለምወድድድሽ ነው።
.
ታዲያ ግን የኔ አለም ፣ በፆም ዝለሽ ውለሽ ፣ ማታ ስታፈጥሪ፣
እጅሽን ከፍፍፍ አ‘ርገሽ ፣በእንባሽ እየታጠብሽ ፣ ስማችንን ጥሪ።
እባክህን በይው
በእዝነትህ በይው
የከበደን ትዳር ደርሶ እንዲገራ ፣ እንድትሆኝ ሀላሌ፣
ያ ረብ ፣ ያ ረብ በይ ፣ እንዳትረሺው ሁሌ።
ይህን ግን የምለው
አደራ አስታውሺ ፣ ስለምወድድድሽ ነው።
.
@fuadmu
@fuadmu
ለአስተያየትዎ
@fuadmubot