Get Mystery Box with random crypto!

እንኳን ለእናታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የዕርገት በዓል አደረሳችሁ!!! #ድንግል_ሆይ የአንቺ | ፍሬ ሃይማኖት

እንኳን ለእናታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የዕርገት በዓል አደረሳችሁ!!!

#ድንግል_ሆይ የአንቺ ሥጋ ይገርመኛል ከሔዋን ተገኝቶ ከመላእክት ይልቅ ንፁህ ሆኗአልና፣ አፈር ነህ ከተባለው ከአዳም ተወልደሽ በሰማይ በአባቱ ቀኝ በተቀመጠው ንጉሥ በክርስቶስ ክቡር ሰውነት ላይ በተለየ ክብር ሆኖ በሰማያት ታይቷልና። ባለ ራዕይው ዮሐንስ ከአንቺ በነሳው ሥጋ ከተወጋው ቁስለቱ ጋር ወደ ሰማይ እንደወጣ ቢያየው እንዲሁ ይመጣል ብሎ በመፅሐፍ ነገረን። የወጉትም ሁሉ ያዩታል ተብሎ ተፃፈ። የታናሿ የአንቺ ገላ ሰማይ ለሚጠበው አምላክ ልብስ ሆነ። መሰወሪያው ከዚህ ነው የማይባለው ልዑል ሥጋሽን ለብሷልና ሥጋ ሆነ ተባለለት። ከባሕሪው እሳት የሆነውን እርሱን ሁሉ ዳሰሰው ሁሉ አቀፈው። መለኮታዊ ክብሩን በአንቺ ሥጋ ውስጥ ቢሰውረው የወደቀው ሰውም አምላክ ሆነ ተባለ። ይደንቃል።

#ደንግል_ሆይ መላእክት በቤተልሔም በአንቺ ላይ የሆነውን ቢመለከቱ ስብሐት ለእግዚአብሔር አሉ። ሌላ ምን ይባላል? የማይወርደው ከከፍታው ወርዶ ሲታይ በአድናቆት ስብሐት ነው እንጂ። ሰማይ ከክብሩ የተነሳ የምትጠበውን በአንቺ ክንድ ላይ ሲያዩት ምን ይበሉ? ኦ ማርያም በአንቺ የሆነውን ለመፃፍ የሚያስብ ቃለ ፀሐፊ ከፍቅሩ የተነሳ ብዕሩ በእንባ ስለሚርስ ስለ አንቺ እንዲህ ነው ለማለት ቃልና እቅም በማጣት ሰአሊ ለነ ብሎ ጽሑፉን ይዘጋዋል። አይችልምና።

#ልዑሉን_የወለድሽ_ልዕልት_ሆይ የአንቺ ሥጋ ከአቤል ይልቅ ተወደደ፤ ከደገኛው አብርሐም ይልቅ ከፍ አለ፤ ከንጉሱ ከዳዊት ይልቅ ሥጋሽ የተለየና የተመረጠ ሆነ ...ዳዊትም፦ ንጉስ ደም ግባትሽን ወደደ ብሎ ፃፈልሽ። ከእስራኤላውያን አባት ከያዕቆብ ድንኳን ይልቅ የአንቺ ሥጋ ተመረጠ። ሎጥ፦ መላእክትን ወደ ቤቴ ግቡ ቢላቸው በአደባባይህ እንሆናለን እንጂ አንገባም አሉት። ድንግል ሆይ የአንቺ ሥጋ ግን መላእክትን ለፈጠረ ጌታ ማደሪያ ሆነ። ለዚህ ቃል የለም ዝምታና አንክሮ እንጂ።

#ድንግል_ሆይ የአንቺን ሥጋ በመቃብር የለም በአብ ቀኝ እንጂ። አንዳንዶች ተነስታለች ለማለት ከበዳቸው። ለመሆኑ ልጅሽ አልዓዛርን ከመቃብር ያስነሳ መሆኑን አላነበቡ ይሆንን? የኢያዒሮስ ልጅን ታሪክ አልተመለከቱ ይሆን አንቺ ግን ወደ ሰማያት ከተነጠቁት ከሄኖክና ከኤልያስ ትበልጫለሽ።
የቅዱሳን ሐዋርያት አባቶቻችን በረከት የእመቤታችን ረድኤት አይለየን አሜን!!!

#ድንግል ሆይ ምልጃሽ #ኢትዮጵያን #ይታደግ። ለዓለም ምሕረት ይሁን ።