Get Mystery Box with random crypto!

#መጋቢት_10 #ቅዱስ_ዕፀ_መስቀል መጋቢት አስር በዚች እለት የክብር ባለቤት ጌታችን አምላካችን | ፍኖተ ቅዱሳን አበው

#መጋቢት_10

#ቅዱስ_ዕፀ_መስቀል

መጋቢት አስር በዚች እለት የክብር ባለቤት ጌታችን አምላካችንና መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል የተገለጠበትና የተገኘበት ነው። የዚህም የከበረ ዕፀ መስቀል መገለጡና መገኘቱ ሁለት ጊዜ ሆኗል። መጀመሪያ የፃድቁ ንጉስ የቆስጠንጢኖስ እናት በሆነች በንግስት እሌኒ እጅ ነው።

«እርሷ ለእግዚአብሔር ተስላ ነበርና ልጇ ቆስጠንጢኖስ ወደ ክርስቲያን ሀይማኖት ቢገባ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዳ መስቀሉን እስከ አገኘችው ድረስ ልትፈልግው በኢየሩሳሌም ያሉ ቅዱሳት መካናትንና አብያተ ክርስቲያናትን ልታንፃቸው ነው።

ከዚህ በኋላ ልጇ አምኖ የክርስትና ጥምቀትን በተጠበቀ ጊዜ እሌኒ ቅድስት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች ከእረሷ ጋርም ብዙ ሰራዊት ነበር ደርሳም ስለ ከበረ መስቀል መረመረች የሚያስረዳት አላገኘችም የአይሁድ ወገን የሆነ አንድ ሽማግሌ ሰው አስራ በርሀብና በጥማት አስጨነቀችው።

በተጨነቀም ጊዜ ለንግስት እሌኒ የጉልጎታን ኮረብታ አስጠርጊ ብሎ ነገራት እርሷም ይጠርጉ ዘንድ አይሁድን አዘዘቻቸው።

ቤቱን የሚጠርግ ሰው ሁሉ ጥራጊውን በውስጡ የከበረ መስቀል በአለበት በጌታችን መቃብር ላይ እንዲጥል አይሁድ አስቀድመው አዝዘው ነበርና ንግስት እሌኒ እስከ ደረሰችበት ጊዜ ከሁለት መቶ አመት በላይ ጥራጊያቸውን ሲጥሉበት ኖሩ ኮረብታም ሆነ። አይሁድም በጠረጉ ጊዜ ሶስት መስቀሎች ተገለጡ የክብር ባለቤት ክርስቶስ የተሰቀለበት የትኛው እንደሆነ አላወቁም። የሞተ ሰውም አግኝተው አመጡ።

አንዱንም መስቀል አምጥተው በሞተው ሰው ላይ አኖሩት አልተነሳም ደግሞ ሌላውን መስቀል አምጥተው በሙቱ ላይ አኖሩ አሁንም አልተነሳም ከዚህም በኃላ ሶስተኛውን መስቀል አምጥተው በሙቱ ላይ አደረጉት ያንጊዜ የሞተው ሰው ተነሳ እሌኒም የክርስቶስ መስቀል እንደሆነ አውቃ ሰገደችለት የክርስቲያንም ወገኖች ሁሉ ሰገዱለት።

ለልጅዋ የላከችው ይህ መስቀል ነው የሚል በሌላ መፅሀፍ ይገኛል የቀረው ግን ግንዱ በውስጡ ተተክሎበት የነበረው ከእርሱም እኩሌታውን ከቅንዋቱ ጋራ ወደ ልጅዋ የላከችው ነው።

ከዚህም በኃላ ስራአታቸውና የህንፃቸው ነገር በመስከረም ወር በአስራ ሰባት ተፅፎ የሚገኝ አብያተ ክርስቲያናትንና የከበሩ ቦታዎችን አነፀች። ሁለተኛው በሮሙ ንጉስ በህርቃል ዘመን የሆነው ሲሆን የፋርስ ሰዎች በግብፅ አገር ሳሉ ወደ አገራቸው ሊመለሱ ወደዱ። ከሹማምንቶቻቸው አንዱ የጦር መኰንን ተነጥሎ ወደ ኢየሩሳሌም አልፎ ደረሰ ወደ ከበረ መስቀል ቤተ ክርስቲያንም ገባ። መስቀሉም በላዮ በተተከለበት ግንድ ፊት ታላቅ ብርሀን ሲበራ አይቶ ሊያነሳው እጁን ዘረጋ። እሳትም ወጥታ እጁን አቃጠለችው።

ከክርስቲያን በቀር ማንም ሊነካው እንደማይችል የመስቀልን የክብሩን ነገር ሰዎች ነገሩት። ሁለት ዲያቆናትንም ይዞ የከበረ መስቀልን እንዲሸከሙ አዘዛቸው ከኢየሩሳሌም ብዙ ሰዎችን ማርኮ ወደ አገሩ ተመለሰ።

የፋርስ ሰዎች ኢየሩሳሌምን እንዳጠፏት ብዙዎች ሰዎችንም እነድ ማረኩና የከበረ የክርስቶስንም መስቀሉን እንደ ወስዱ የሮም ንጉስ ህርቃል በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ። ስለርሱም እንዲፆሙ ምእመናንን አዝዞ ወደፋርስ ዘምቶ ወጋቸው ብዙዎችንም ገደላቸው የከበረ እፀ መስቀልንም እየፈለገ በሀገራቸው ሁሉ ዞረ ግን አላገኘውም።

ያ ዲያቆናቱና መስቀሉን የወሰደ መኰንን ከቦታዎች በቤቱ አነፃር ባለ በአንድ ቦታ ላይ ወስዷቸው ጥልቅ ጉድጓድ እንዲቆፍሩ አዝዞ በዚያ የከበረ መስቀልን አስቀበረ እነዚያንም ዲያቆናት ገደላቸው።

ነገር ግን ያ መኰንን የማረካት የካህናት ወገን የሆነች በእርሱ ቤት የምትኖር አንዲት ብላቴና ነበረች። እርሷም የከበረ መስቀልን ሲያስቀብርና ሁለቱን ዲያቆናት ሲገድላቸው በቤቱ ውስጥ ሁና በመስኮት ትመለከት ነበር ወደ ንጉስ ሀርቃልም ሂዳ መኰንኑ ያደረገውን ሁሉ ነገረችው።

ይህንንም ንጉስ ሰምቶ እጅግ ደስ አለው ያቺ ብላቴናም መራችው ከእርሱም ጋራ ብዙ ሰራዊት ሆኖ ኤጲስቆጶሳትና ካህናትም ነበሩ። ወደ ቦታውም እስከምታደርሳቸው ያቺን ልጅ ተከተሏት ቅፍረውም የከበረ እፀ መስቀልን አገኙት ከአዘቅቱም አወጡት ንጉሱና ሰራዊቱም ሰገዱለት።
በልብሰ መንግስቱም አጐናፀፈው ታላቀወ ክብርንም አከበረው እጅግም ደስ አለው ከሰራዊቱ ጋር። የዚህም መስቀል ሁለተኛ የተገለጠበትና የተገኘበት በዚች ቀን በመጋቢት አስር ነው፡፡ ከዚህ በኃላ ንጉሱ የከበረ እፀ መስቀልን ተሸክሞ ወደ ቁስጥንጥንያ ከተማ ወሰደው፡፡

የመድኃኒታችን የመስቀሉ በረከት ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት)