Get Mystery Box with random crypto!

ብንችል እናበረታታቸው! 1) ልዩነት አለባቸው ብሎ የሚወቅሳቸው ሰው፣ ይህን ሲመለከት ደስ ሊለው | Fano Media Network

ብንችል እናበረታታቸው!

1) ልዩነት አለባቸው ብሎ የሚወቅሳቸው ሰው፣ ይህን ሲመለከት ደስ ሊለው ይገባል። መነጋገር መፍትሄ ያመጣል። "አትስማሙም" እያለ እየወቀሰ ያሉ ችግሮችን እንፈታለን ብለው ሲመጡ በአሉታዊ መልኩ መቀበል ሳይሆን ማበርታት፣ በተግባርም አሳዩን ብሎ መፈተን ነው የሚሻለው።

2) ሌሎች ጉልህ ልዩነት ያሏቸው ቡድኖች ጋር "አብሮ መስራት ያስፈልጋል" ብለው የሚመክሩ የወንድሞቻቸውን መሰባሰብ በአሉታዊነት ከመቀበል ማገዝ የተሻለ ነው።

3) ህዝብን የሚያጠቃን የተለያየ ኃይል ገና በግምት "አንድ ሆነ ፣ የእኛው ግን እንደተበተነ ነው" ብለን እየወቀስን ተስማማን ሲሉ ከማናናቅ ማበርታት ነው የሚሻለው።

4) ሁላችንም ልዩነትን እንጠላለን እንላለን፣ ልዩነትን የሚያጠብ ጉዳይ ሲገኝ "ደግ አደረጋችሁ" ማለት ያስፈልጋል።

5) የአብን ወንድሞችና እህቶች ልዩነታቸው ህዝብ ውስጥ ይገባል። በፌስቡክ የሚፃፈው ከፋፋይ አጀንዳ መቅረቱ እንኳን ጥቅም አለው። ሲሆን የተሻለ ያግዛሉ፣ ባይሆን እንኳ አሉታዊ ስሜት የሚቀርፍ እርምጃዎች ሲኖሩ ማበርታት ያስፈልጋል።

6) በፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ልዩነት ይኖራል። ልዩነት የሌለበት ድርጅት የለም። ሊፈርስ ተንገዳግዶ የተረፈው ብዙ ነው። የፓርቲ ብቻ ሳይሆን በቅዱስ መፅሐፍ መርህ የተደራጁ የእምነት ተቋማት ውስጥ ችግር ያልገጠመው ያለ አይመስልም። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተንጧል። በዚህ ያልተጎዳ ተቋም የለም። አሁን ያን ችግር ለመቅረፍ ሲሰራ ማበርታት ነው የሚሻለው።

7) በተለይ በተለይ አንዱን ደግፎ አንደኛውን ተቃውሞ፣ አንዱን አወድሶ፣ ሌላኛውን አንቋሽሾ ችግሮችን ማባባስ መቆም አለብን።  ፌስቡክ ላይ ያለነው ከእነዚህ ወንድሞቻችን የተሻለ ቅርበት ሊኖረን አይችልም።  ነገ ስልጣን ቢይዙ ደግሞ አብረው ነው የሚወስኑልን፣ አብረው ነው የሚወስኑብን።

8/ ብዙው በበጎም በመጥፎም የሚወራው የምንሰማውን ያህል አይደለም። አናታችን ላይ ሳናወጣም፣ ጭቃ ላይ ሳንጥላቸውም ማገዝ የተሻለ ነው። ጭልጥ አድርጎ የመደገፍና የመጥላት አባዜ ከፖለቲካው ጋር የሚሄድ አይደለም። አብዛኛውን ጉዳይ ቀርበን ብናየው የምንሳሳትባቸው ግምቶች ይበዛሉ። የሰማናቸው መልካምም መጥፎም ነገሮችን የምንታዘብበት እውነትን እናገኛለን። የምንደግፈው እንደሚያወድሱልን፣ የምንጠላው በክፉ ብቻ እንደነገሩን መጠን የማይሆንበት እድል ሰፊ ነው።

የውጭ አገር ተቋማት እንዲጮሁልን እየጠበቅን የእኛን ወንድሞች ልዩነት በማስፋት የምናመጣው ክስረትን ነው። ስንተቻቸውም ቢሆን ለከት ቢኖር ያዋጣል። የህዝብ ጉዳይ እንደመሆኑ የምንፅፈው፣ የምንናገረው ህይዎታቸው ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው። እኛ እያጠቃናቸው ከትግሉ ይልቅ ራሳቸውን ወደ መከላከል ያተኩራሉ። አንዳንዶቹ ጉዳዶች የአካል ጥቃት ጭምር የሚያመጡባቸው ናቸው። ከዚህ ለመትረፍ ሰው ናቸውና ራሳቸውን ለማዳን፣ በየቀኑ የሚደርሰውን ብሽሽቅ በተቃራኒ ሊቆሙ እንደሚችሉ ጭምር መታሰብ አለበት። ህዝባችን የሚያጠቃ ኃይል ጋር ሳይቀር ሰላም ካልወረደ እየተባለ፣ በድሮን የተደባደቡ እየታረቁ የአንድ ፓርቲ ሰዎች ችግር ይፈታል ሲባል በመልካም ማየት፣ ብንችል ማበርታት አለብን።

9) ዋጋ የከፈሉ ብዙዎች በችግሩ ተስፋ መቁረጥና መበሳጨት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። ነገም ልዩነት ተፈትቶ የተሻለ መስራት ካልተቻለ ችግሩ ይብሳል እንጅ ሊቀረፍ አይችልም። ስለሆነም ብንችል እንደግፋቸው። ልዩነት ካለ የመግለጫ መንገዶች አሉ። ቀጣዩ ጊዜ ደግሞ የከፋ ነው።

10) ህዝብን የሚያጠቁ አካላት የእኛው ወገን ላይ አንዳች ማንነት መዝዘው ጠላት እያበዙልን፣ እኛም ከሌላው አካል ጋር መወዳጀትን እየፈለግን የራሳችን ወንድሞች በሆነ ባልሆነው ማራቅ ለገጠመን ችግር የሚሆን መፍትሄ አይደለም። በዚህ ወቅት ደግሞ የሌላውንም ውግንና የምንፈልግበት ወቅት ነው። የራስ ወገን በታሰበው መልኩ ባያግዝ እንኳ እንቅፋት እንዳይሆን ማድረግ ትግሉ የሚጠይቀው መሰረታዊ ነገር ነው። የግል ብሽሽቅ፣ ሀሜትና የከረመው ዘመቻ ለገጠመን ችግር መፍትሄ አይሆንም። ያልተወገዘ፣ ሀሰት ያልተነዛበት የለም። ያን ሁሉ ማረም ግድ የሚልበት ወቅት ላይ ነን።

ጌታቸው ሽፈራው

@FanoNetwork