Get Mystery Box with random crypto!

በሆሮ ጉዱሩው ጥቃት ከ55 ሰዎች በላይ ተገደሉ የአዋሽ ባንክ ቅርንጫፍ በቦምብ ጥቃት ጋይቷል | 🇪🇹 E.Z መረጃ 🇪🇹

በሆሮ ጉዱሩው ጥቃት ከ55 ሰዎች በላይ ተገደሉ

የአዋሽ ባንክ ቅርንጫፍ በቦምብ ጥቃት ጋይቷል


በኦሮሚያ ክልል ሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ አገምሳ ከተማ የታጠቁ አካላት በከፈቱት ተኩስ ቢያንስ ሲሉ የአይን እማኞች ተናገሩ፡፡የአከባቢው ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ለአንድ ዓመት ያህል አስከፊ የተባለ የፀጥታ ችግር ውስጥ በነበረበት በዚህ አከባቢ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች በመደበኛነት ተመድበው የአከባቢውን ፀጥታ ሲያስከብሩ ነበር፡፡ ይሁንና ባለፈው እሁድ ነሃሴ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. የአከባቢውን ፀጥታ ሲያስከብር የነበሩ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አባላት ከከተማዋ መነሳታቸውን ተከትሎ የተለያዩ ስያሜ ያላቸው ታጣቂዎች በከተማዋ ባለፉት ቀናት መታየታቸውን ነው የአይን እማኞች የገለጹት፡፡

አቶ ንጉሴ ባንጃ የተባሉ የአይን እማኝ “እሁድ ማታ የኦሮምያ ልዩ ኃይል ለሌላ ግዳጅ ትፈለጋላችሁ ተብለው ከተማዋን ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ መንግስት ‘ሸነ’ ያላቸው “የኦሮሞ ነጻነት ጦር” ሰኞ ጠዋቱን ገብተው ከተማዋን ተቆጣጠሩዋት፡፡”ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የአይን እማኙ «ታጣቂዎቹ በከተማዋ ውስጥ ሙሉ በሙሉ መንቀሳቀስ ከጀመሩ በኋላ ወደ 59 የጦር መሣሪያ ከማህበረሰቡ አስፈትተው በዚያው ሰኞ ቀን ከተማዋን ለቀው ወጥተዋል፡፡»ብለዋል

አቶ ንጉሴ አክለው በሰጡን አስተያየታቸው፤ “ ፋኖ ነን ያሉ የታጠቁ አካላት ወደ ከተማዋ ገብተው ከኦነግ ጋር አብራችኋል በሚል በመደዳው ከተማዋ ላይ ተኩስ በመክፈታቸው ከ15 ሺህ የማያንሱ የከተማዋ ነዋሪዎች ከተማዋን ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል” ነው ያሉት፡፡ ጥቃቱን ተከትሎ ከትናንት ማታ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ብቻ የ55 ሲቪል ዜጎች አስከሬን መቅበራቸውን የሚናገሩት እኚው አስተያየት ሰጪ “ ከማህበረሰቡ በአጠቃላይ የ87 ሰዎች ሕይወት የጠፉ በመሆኑ የ32 ሰዎች አስከሬን በየጫካውና በየገደሉ እየፈለግን ነው” ሲሉም የችግሩን ስፋት አስረድተዋል፡፡

አስተያየት ሰጪው እንደሚሉት ታጣቂዎቹ ከኪረሙ ወረዳ ሃሮ ቀበሌ የመጡ ናቸው፡፡ በትናንትናው የአገምሳ ከተማ ጥቃት ከጠፋው የሰው ህይወት በተጨማሪ በከተማዋ የሚገኝ የአዋሽ ባንክ በቦምብ ሲጋይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክን ጨምሮ በበርካታ የከተማዋ ተቋማት ላይ ዘረፋ ተፈጽሟል ብለዋል,።

አስተያየት ሰጪው ለፀጥታ ችግሩ መከሰት የመንግስት ፀጥታ ኃይሎች አከባቢውን ለቀው የመውጣት ውሳኔን ተጠያቂ ያደርጋሉ። አስቀድሞም ከአንድ ዓመት በላይ በአከባቢው በቆየው የፀጥታ ችግር በርካታ ሰው በከተማዋ ተጠልለው እንዲቆዩ እንዳስገደዳቸው በመግለጽም፤ አሁን ላይ ግን በከተማዋ ላይ ባነጣጠረው ጥቃት ነዋሪዎች ወደየጫካው ነፍሳቸውን ለማዳን መሸሻቸው ነው የተብራራው፡፡

ሌላው አስተያየታቸውን ያጋሩን የከተማዋ ነዋሪና በመምህርነት ሙያ የተሰማሩት ቢቂላ ዓለሙ፤ በጸጥታ ችግር ምክኒያት ከየገጠር ቀበሌያት የተፈናቀሉ የተለያዩ የማህበረሰብ አካላት በዚሁ “የፋኖ ታጣቂዎች” ባሏቸው በተፈጸመው ጥቃት ከተማዋን ለቀው ተሰደዋል፡፡

ኒሞና ዴሬሳ የተባሉ አስተያየታቸውን የቀጠሉ ሌላው በመምህርነት ሙያ የሚተዳደሩ ነዋሪ እንዳሉት 20 አስከሬኖችን በአይናቸው አይተው ስማቸውንም መመዝገባቸውን አስረድተዋል፡፡ የሟቾች ቁጥር ከዚህ በላይ መሆኑንም በመግለጽ፡፡

እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ከ40 በላይ ቁስለኞች መታከሚያ ቦታ እንኳ አጥተው ‘አስከፊ’ ያሉት ችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የነዋሪዎች ንብረት የሆኑ ከብቶችን ጨምሮ በርካታ ሃብት መዘረፋቸውንም አንስተዋል።

በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የአሙሩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፋንታሁን ታዬ ስለሁኔታው ማብራሪያቸውን እንዲሰጡ ከዶይቼ ቬለ ለቀረበላቸው ጥያቄ ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ ሳይሰጡ፤ ከህበረተሰቡ ጋር በውይይት ላይ መሆናቸውንና ነገ መልስ እንደሚሰጡ አስረዱ፡፡

@Ezmerejaet
@Ezmerejaet