Get Mystery Box with random crypto!

የአሳ ፍቅር አንድ ወጣት የሰራውን አሳ በችኮላና በጉጉት እያጣጣመ ሲበላ አንድ አዛውንት፣ “ለምን | The True Love Family

የአሳ ፍቅር

አንድ ወጣት የሰራውን አሳ በችኮላና በጉጉት እያጣጣመ ሲበላ አንድ አዛውንት፣ “ለምንድን ነው ይህንን አሳ እንደዚህ በጉጉት የምትበላው?” አሉት፡፡

ወጣቱም በመመለስ ፣ “አሳ በጣም ስለምወድ ነዋ” አለ፡፡

አዛውንቱም፣ “ኦ አሳ ትወዳለህ? ለዚህ ነው ከሚኖርበት ከውኃው ውስጥ አጥምደህ፣ አውጥተህና ትንፋሽ አሳጥተህ እንዲሞት በመተው የቀቀልከውና የበላኸው? እባክህን፣ አሳ እንደምትወድ አትንገረኝ፡፡ የምትወደው ራስህን ነው፡፡ አሳው ስለሚጥምህ፣ ስለሚያረካህና ስለሚጠቅምህ ከውኃ ውስጥ አውጥተህ ቀቀልከውና በላኸው፡፡ የወደድከውና የጠቀምከው ራስህን እንጂ አሳውን አይደለም”፡፡

እኝህ አዛውንት በዚህ ገጠመኛቸው ላይ በመመርኮዝ ትምህርት ሲሰጡ እንዲህ ይላሉ፣ “አብዛኛው ፍቅር ብለን የምንጠራው ነገር በሌላ መጠሪያው “የአሳ ፍቅር” ነው ሊባል የሚገባው፡፡

እውነተኛ ፍቅር የሚለካው በምንቀበለው ነገርና በምናገኘው ጥቅም ሳይሆን በምንሰጠውና ሌላውን በምንጠቅመው ነገር ነው፡፡

የምንወደውን ሰው እንሰጠዋለን፡፡ ስንሰጠው ደግሞ የመነሻ ሃሳባችን ወሳኝ ነው፡፡ በሁለት ንጽጽራዊ ምሳሌዎች እናብራራው፡፡

እቤታችን ያለውን በግ እንወደዋለን ስለዚህም ምግብ እንሰጠዋለን፡፡ ይህ በግ በሰጠነውና ባበላነው ቁጥር የማይደልብ ቢሆንና እንዲያው በሆነ ምክንያት ለምግብነት አይሆንም ብንባል ግን ለበጉ ምግብ መስጠታችንንና መቀለባችንን እናቆማለን ወይም እንቀንሳለን፡፡ ለምን? ፍቅራችን “የአሳ ፍቅር”፣ ፍቅራችን እኛ ከምናገኘው ጥቅም አንጻር ስለሆነ፡፡

በተቃናኒው እቤታች ያለውን ልጃችንን እንወደዋለን ስለዚህም ምግብ እንሰጠዋለን፡፡ ይህ ልጃችን ባበላነው ቁጥር ቢከሳና ህመምተኛ ቢሆን መመገብን አናቆምም፡፡ እንዲያውም ለእሱ ያለን ኃዘንና ፍቅር ይብስበታል፡፡ ለምን? የፍቅራችን መነሻ ልክ እንደ አሳው ፍቅር ከእኛ ጥቅም ሳይሆን ከእሱ ጥቅም ስለሆነ ነው፡፡

ማንኛውንም የቀላል ጓደኝነት፣ የፍቅር፣ የትዳርም ሆነ የስራ ቅርበታቸሁንና “ፍቅራችሁን” ተመልከቱት፡፡ እነዚያ ሰዎች እናንተን እስከጠቀሙ ድረስ የምትወዷቸው፣ የማይጠቅሙበት ሁኔታ ሲከሰት ወይም የነበራቸው ሁኔታ ሲቃወስባቸው ዘወር የምትሉ ከሆነ ፍቅራችሁ “የአሳ ፍቅር” ይባላል፡፡

አንድ ሰው ስለሚጠቅመንና ስለሚያግዘን መውደዳችንና መንከባከባችን በራሱ ችግር ባይኖረውም ይህንን ሰው ከጥቅማችን አንጻር ብቻ መውደዳችንና የማይጠቅመን እንደመሰለን ስንጥለው ግን የወረደው የፍቅር ደረጃ ላይ ይመድበናል፡፡

ቄስ ወልደጊዮርጊስ 2003 አ.ም