Get Mystery Box with random crypto!

ንስሐ በቅዱስ ኤፍሬም ተወዳጆች ሆይ ኑ አባቶቼና ወንድሞቼ እግዚአብሔር ለርስቱ ለመንግሥቱ የለያ | ✟የማለዳ ፀሀይ✟

ንስሐ
በቅዱስ ኤፍሬም

ተወዳጆች ሆይ ኑ አባቶቼና ወንድሞቼ እግዚአብሔር ለርስቱ ለመንግሥቱ የለያችሁ ምእመናን ሆይ ኑ፡፡ የልጅነትን ማኅተም ያለባችሁ የክርስቶስ ወታደሮች ሆይ ኑ፡፡ ልጆቼ ይኽን ለነፍሳችን ድኅነት እግዚአብሔር ያዘጋጀውን ትምህርት ትማሩ ዘንድ ኑ፤ ጊዜ ሳለልን እንመካከር ዘንድ ኑ፡፡ ኑ ዘለዓለማዊ ሕይወትን ገንዘብ እናድርግ፡፡ ነፍሳችንን እንገዛት ዘንድ እንቻኮል፡፡

ዓይነ ልቡናችን ብሩህ ይኾን ዘንድ ኑ በዕንባ እንታጠብ (እናልቅስ)፡፡ ባለጸጋዉም ድኻዉም፣ ልዑላንም ሕዝቦችም፣ ወጣቶችም ጐረምሶችም፣ ሽማግሎችም ሕፃናትም፣ በአጣቃላይ ጣዕመ መንግሥተ ሰማያትን መውረስ ከምረረ ገሃነም መዳን የምትሹ ሁላችሁም ኑ፡፡

ከክቡር ዳዊት ጋር ሆነን ምሕረቱ የበዛ ባለጸጋውን እግዚአብሔርን “ነጽረኒ ወስምዓኒ እግዚኦ አምላኪየ" አቤቱ ፈጣሪዬ ልመናዬን ሰምተኽ በዓይነ ምሕረትህ እየኝ፤ ተመልከተኝ፡፡ "አብርሆን ለአዕይንትየ ከመ ኢኑማ ለመዊት" የሞት እንቅልፍ እንዳያንቀላፉ ዓይኖቼን አብራቸው” ብለን እንለምነው /መዝ.13፥3-4/፡፡ ከመንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን እንደነበረው እንደ ዓይነ ስዉሩ ሰውም፡- “ተሣሃለኒ ኢየሱስ ወልደ ዳዊት" የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ ማረኝ” ብለን እንጩኽ/ማር.10፥48/፡፡ ዝም እንል ዘንድ የሚቈጡን ቢኖሩም እንደ በርጠሜዎስ ልጅ እንደ ጠሜዎስ ዓይነ ልቡናችንን እስኪያበራልን ድረስ አብዝተን ወደ ብርሃን ክርስቶስ እንጩኽ፡፡ ስለዚኽ ወደ ክርስቶስ እንቅረብ፤ ብሩህ ልቡናንም ገንዘብ እናድርግ፡፡ ገጻችንም ከቶ አያፍርም፡፡ ኑ! ሃይማኖትንና ምግባርን አንድም ልጅነትን መንግሥተ ሰማያትን ለመያዝ እንሩጥ። ይኽን ያደረግን እንደኾነም የዚህ ዓለም ነገር ከንቱ ሆኖ ይታየናል፡፡ ስለዚህ ራሳችንን ንቁ እናድርግ፤ በዐሥራ አንደኛው ሰዓት ላይ ብንመጣም አይዘጋብንምና ኑ እንፍጠን፡፡ ምሽቱ ቀርቧል፤ ለኹሉም እንደየሥራው የሚከፍለው ልዑለ ባሕርይ ኢየሱስ ክርስቶስም ሊመጣ ነው፡፡
@ewkete_orthodox
@ewkete_orthodox