Get Mystery Box with random crypto!

በአንድነቱ ምንታዌ በሦስትነቱ ርባዔ በሌለበት በሥላሴ ስም ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ የ | ✟የማለዳ ፀሀይ✟

በአንድነቱ ምንታዌ በሦስትነቱ ርባዔ በሌለበት በሥላሴ ስም ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ የምሉዓ ጸጋ እስጢፋኖስን ዜና መጻፍ እጀምራለሁ


<<በመዓዛ ጽጌኪ ለዘበዐውደ ስምዕ ሰክረ ፤ ውግረተ አዕባን ይመስሎ ሐሰረ ፤ እሳትኒ ማየ ባሕር ቆሪረ>>

<<በአበባሽ (በልጅሽ) በክርስቶስ (በፍቅሩ) መዓዛ የሰከረ ሰው ፤ በሰማዕትነት አደባባይ ቢቆም እንኳን በድንጋይ መወገር ለእርሱ ገለባ ይመስለዋል ፣ እሳትም ለእርሱ እንደ ቀዝቃዛ የባሕር ውኃ ነው>> አባ ጽጌ ድንግል

ቀዳሜ ሰማዕት ወሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስ ቀድሞ ከመምህሩ ከገማልያ ትንቢት የተነገረለትን ሱባዔ የሚቆጠርለትን መሲሕ ሲሰማ አደገ በኋላም ከመጥምቀ መለኮት ከቅዱስ ዮሐንስ <<የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ >> ዮሐ 1፥19 የሚለውን የመጥምቁን ቃል በሰማ ጊዜ የቃሉን ትምህርት የእጁን ተዓምራት ለማየት የነበረውን ጉጉት እስከ ሞት ድረስ ሊታመነው ወዶ ተከተለው።
ለብሉያት አዲስ ያልነበረው መጋቤ ብሉይ እስጢፋኖስ የሐዲስ ኪዳን መግቢያ introduction ከመጥምቁ ዘልቆ የሐዲስ ኪዳን ትምህርቱንም ከሊቀ ሊቃውንት ኢየሱስ ክርስቶስ በቃልና በኑሮ ተማረ።

የመጀመሪያዎቹ ጳጳሳት ሐዋርያት የምዕመናኑን በዘርና በቋንቋ መከፋፈል ዐይተው ለዚያም ምክንያት የነበረውን የመዓድ ጉዳይ የሚያስተባብሩ መንፈስ ቅዱስ የሞላባቸው ሰባት ዲያቆናትን ሲመርጡ በምግባር በሃይማኖት ያጌጠውን በትምህርቱም ጣዕም ወደር የሌለውን አይሁድን በአፍ በመጻፍ አፍ የሚያሲዘውን እስጢፋኖስን ሊቀ ዲያቆናት አድርገው ሾሙት።

የስምንት ሺህ ምዕመናን አባት ሆኖ በአንደበቱና በሕይወቱ ወንጌልን ፤ በደግነቱ ምድራዊ መዓድን እያበላና እያጠጣ የምዕመናንን አንድነት እጅግ አጠነከረው።

ለምቀኝነት አያርፉም የተባለላቸው አይሁድ የአስጢፋኖስን የአገልግሎቱን ርቀት የአዕምሮውን ምጥቀት ተመልክተው በቅናት ተነሳሱበት ፤ የሀሰት ምስክር አቁመው በሸንጎ ፊት አቆሙት የሶስና በሀሰት ክስ ሸንጎ ፊት መቆም ሲማር ያደገው መጋቤ ብሉይ እስጢፋኖስ ለሚጠይቁት ሁሉ መልስ እያሳጣ የተነገረውን ትንቢት የተመሰለውን ምሳሌ መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ይናገር በጀመረ ጊዜ መልኩ የእግዚአብሔርን ልጅ ይመስል ነበር ይለናል ጸሐፊው ቅ/ሉቃስ እርሱም እኔን ምሰሉ ያለውን ጌታ በምግባር መስሎት እንደነበር እናስተውላለን። ሐዋ 6፥15

እንግዲህ ይኼኔ ነው በአፍ በመጻፍ መልስ ቢያሳጣቸው ጊዜ <<እረኛውን ምታ መንጋው ይበተናል>> ልማዳቸው የሆነው አይሁድ እስከ በወዲያኛው ሊሰናበቱት ማኅበሩንም ሊበትኑ እስጢፋኖስን ከከተማ ውጪ አየጎተቱ ይዘውት ወጡ መጠን አልባ ጥላቻቸውንም የድንጋይ ማዕበል በማዝነብ ይወጡበት ጀመር እርሱ ግን ሰማያት ተከፍተው የእግዚአብሔርን ልጅ በቀኝ ቆሞ ያይ ነበር የሚያዘንቡበት የድንጋይ ዝናብ <<ይመስሎ ሐሰረ..>> እንዳለ ሊቁ እንደ ገለባ ይመስለዋል በክርስቶስ መዓዛ ፍቅር ታውዷልና ቀኑን ሙሉ ሊገደል ወደደ። ሮሜ 8፥36 ለገዳዮቹም ኦ አባ ሥረይ ሎሙ እስመ በዘኢየአምሩ ይገብሩ አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ሐዋ 7፥60 ብሎ ወዳጆቻችንን መውደድ ላቃተን ለእኛ ጠላቶቹን ወዶ አምላኩን መምሰልን አስተማረን።

ጌታ ኢየሱስም መንፈስ ቅዱስ የሞላበትን በሕይወቱ እስከ ሞቱ እርሱን የመሰለውን ፤ ከእርሱ ጋር በአንድ መቅደስ የተራዳውን ገባሬ ሰናይ ዲያቆን <<ነፍሴን ተቀበል>> ብሎ ሲጣራ በሰማ ጊዜ ከባሕርይ አባቱ ቀኝ ቆሞ ተቀበለው በሰማያዊ አክሊልም አጌጠው እስከ ሞት ድረስ በመታመን የመጀመሪያ የሆነውን (ቀዳሜ ሰማዕት) በሰማያት በሰማያዊ ማዕረግ አኖረው።


ሰኔ 21 የቤተ ክርስቲያን ልደት የሆነባት የሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በዓል ነበረች። በዚያች እለት ዲያቆኑ እስጢፋኖስ የኪዳኑን ጸሎት እንደጨረሱ ከሐዲስ ኪዳኑ ሊቀ ካህናትና ከሊቀ ሐዋርያት ጴጥሮስ ጋር ገባሬ ሰናይ ዲያቆን ሆኖ ሊቀድስ ገባ በአማናዊቷ ምስራቅ በድንግል ማርያም ፊትም ቆሞ ወደ ምስራቅ ተመልከቱ ይል ነበር።

እስጢፋኖስ ሆይ ከአማናዊቷ መቅደስ ጋራ ወደ መቅደስ በገባህ ጊዜ ምን አስተዋልክ ፤ በአማናዊቷ መንበር ላይ መስዋዕቱ ሲቀርብ ምን ምስጢር ተረዳህ ፤ ማዕጠንቱን ይዘህ ፍሕም በጨመርክባት ሰከንድ ምን ቅኔ ደረደርክ ፤ ወደ አማናዊቷ መቅደስ ወደ አማናዊቷ ታቦት ስግዱ ባልክባት ደቂቃ እንዴት አይነት ስግደት ሰገድክ። ከቅዳሴው ፍጻሜስ በኋላ ወደ እርሷ ቀርበህ ምን ምስጢር አደላደልክ ምን ቅኔ ደረደርክ ፤ አባቴ ሆይ ይህንንስ ኃጢአት ባደቀቀው ሰውነቴ ምስጢር በራቀው አዕምሮዬ ምግባር በራቀው ስብዕናዬ ልረዳው አልችልምና እንዲያው እጹብ ብዬ ልመለስ።

መጋቢያችን በዘር በቋንቋ ለተከፋፈለች የመዓድም ነገር ለጨነቃት ጉባዔ ኢትዮጵያ ትደርስላት ዘንድ ማንን ሐዋርያ ልለምን ጴጥሮስን ነው ዮሐንስን?

በከመ ጸሐፈ ጳውሎስ እንዘ ይብል ሠናየ መልእክተ፤ ናሁ ዘራዕኩ ለውዳሴከ ሕጠተ፤ እርር ሊተ እስጢፋኖስ ፍሬ ከናፍርየ ዘንተ፤ በዘርዐ ሰብእ በሥጋሁ የዐርር ሞተ፤ ወዘዘርዐ በመንፈሱ የዐርር ሕይወተ።

<<ለምንት ሊተ ኢትበል እምአፈ ኃጥእ ውዳሴ>>

ዲ/ን ዘ፲፪
ጥቅምት 16 2014
@ewkete_orthodox
@ewkete_orthodox