Get Mystery Box with random crypto!

የደመራ ዓመት መስቀል የከበረው ትናንት መስሏቸው ያዩ ተገረሙ ክብሩ አስደንቋቸው ትናንትና አይደ | ✟የማለዳ ፀሀይ✟

የደመራ ዓመት

መስቀል የከበረው ትናንት መስሏቸው
ያዩ ተገረሙ ክብሩ አስደንቋቸው
ትናንትና አይደለም የበራው ደመራ
ዘንድሮ ዓመት ፈጀ የመስቀሉ ሥራ

ስንት አይሁድ ተነሥተው መስቀሉን ቀበሩ?
ስንትስ እሌኒዎች ሊያወጡት ቆፈሩ?
ጅጅጋ ሲዳማ ውጡ ተናገሩ

ቤተ ክርስቲያን ልክ እንደ ደመራ
በእሳት ተለኩሳ ደምቃ ስታበራ
ካህናት ምእመናን እንደ ችቦ ነድደው
ስንቴ አከበሩት ለመስቀሉ ታርደው?

ስንት ጊዜ አፏጨ ዲያቢሎስ ተቆጣ
ስንት ሟርት ተሰማ ስንት ቁጣ መጣ?
በዕጣን ያልተገኘ ጌታ ያልሞተበት
ቅርፁ መስቀል ሆኖ መዳን የሌለበት
የወንበዴው መስቀል መስቀሉ መስሏቸው
ስንቶች ትተው ሔዱ ከእሌኒ እናታቸው?

ዓለም የዳነበት መስቀሉን ጨብጦ
ስለዘር የሚሰብክ እጅግ ተመስጦ
የተቃጠለውን መቅደስዋን እያየ
"ራስሽን አድኝ" ሲል ሲስቅ የታየ
ዘንድሮ አይደለም ወይ አይሁዱ የለየ?

ዘንድሮ ከበረ ለአንድ ዓመት ደመራ
በማያቆም ጥቃት በማያቆም ሴራ
ቅድስት ተዋሕዶ በጭንቅ ተወጥራ
አባቶችዋን ከፊት እንደ ጦር ሰድራ
በልጆችዋ ጩኸት በገና ደርድራ

በሰማዕታትዋ ደም ተረጭታና ርሳ
በየአደባባዩ ምሕላን አድርሳ
በፓትርያርክዋ ዓይን በምሬት አልቅሳ
እንደ ራሔል ለአምላክ ዕንባዋን አፍስሳ

ለመስቀሉ ቀን ግን ነጭ ልብስዋን ለብሳ
እንደ ቆስጠንጢኖስ በድል ልትነሣ
አምላክዋን ከፍ አድርጋ ኀዘንዋን ልትረሳ
ተስፋ ያደረገችው በመስቀል ታድሳ

ዘንድሮ ነው በዓል ዘንድሮ ደመራ
በዚህ ዓመት ተገኘን ከመስቀሉ ሥፍራ!!