Get Mystery Box with random crypto!

+ ረሀብ ስንት ቀን ይፈጃል? + 'ከረሃብ ሰይፍ ይሻላል' የሚል የአበው ብሂል ቢኖርም አሁን ሁለ | ✟የማለዳ ፀሀይ✟

+ ረሀብ ስንት ቀን ይፈጃል? +

"ከረሃብ ሰይፍ ይሻላል" የሚል የአበው ብሂል ቢኖርም አሁን ሁለቱም እሳቶች ወገናችንን እየፈጁ ነው:: ከጦርነት እሳት ያመለጠውን የረሃብ እሳት ይቀበለዋል:: ረሃብን በምን ቃል እንግለጸው? በዚህች ደቂቃ ውስጥ አንተ ይሄን ጽሑፍ ስታነብ በረሃብ አለንጋ ክፉኛ ተገርፎ እያሸለበ ያለ ብዙ ወገን አለ:: ስንፍና ሳይጫነው ከአፈር እየታገለ ልጆቹን ሲያሳድግ ኖሮ ድንገት ጦርነት አፈናቅሎት ለልመና የተዳረገ ረሃብ ልጆቹን ሲነጥቀው ቆሞ የሚያይ ወገን በሰሜን ኢትዮጵያ እጅግ ብዙ ነው:: በፖለቲካ ድንበር የተለያየው ምኑንም የማያውቀው መከረኛ ሕዝብ አሁን በረሃብ ግን አንድ ሆኖአል:: በግራና ቀኝ በኢንተርኔት ተሰልፎ የሚሰዳደበው የሩቅ ጦረኛ ቁርሱን ምሳውን ራቱን ጥርግ አድርጎ በልቶ ነው:: መሬት ላይ ግን መከረኛው ሕዝባችን አንድ ላይ እየተራበ ነው::

ረሃብን ለመግለጽ ምን ቃል አለ?? ነፍሳቸውን ይማርና ሁለቱ ዕንቁ ደራስያን ጋሽ ጸጋዬ እና ጋሽ ስብሐት እንዲህ ብለው ነበር :-

ረሃብ ቀጠሮ ይሰጣል?
ወይስ ቀን ቆጥሮ ይፈጃል?
“የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል”
ይባላል፣ ድሮም ይባላል
ይዘለዝላል ይከትፋል
ብቻ እስከሚጨርስ ድረስ ሆድ ለሆድ ጊዜ ይሰጣል?

ወተት አንጀት ነጥፎ ሲላብ
ሆድ ዕቃ ደርቆ ሆድ ሲራብ
ተሟጦ አንጀት በአንጀት ሲሳብ …

የጣር ቀጠሮው ስንት ነው?
ለሰው ልጅ ሰው ለምንለው?
ላይችል ሰጥቶ ለሚያስችለው?
ስንት ቀን ነው? ስንት ሌት ነው?
(ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን)

"የተራቡ ልጆች አባት ምሬት :-

አበላቸው እህል ከልክለህ አምስት ልጆች የሠጠኸኝ ምነው?

አምስት ልጅ ተሰብስቦ አንድ ላይ ሲውል አንዲት ሳቅ ብቅ ሳትል መምሸቱ ምነው?

ልጆቼ አንዲት ቀን እንኳን አኩኩሉ ሳይጫወቱ ማለቃቸው ምነው?

ልጆቼን በአንድ ቀን ስቀብር ዝም ብለህ ማየትህ ምነው?"

(ጋሽ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር)

በያለንበት ለምግብ በተቀመጥን ጊዜ እያንዳንዱ ጉርሻ የሆነን ሰው ዕድሜ ሊያራዝም ይችል እንደነበረ እናስብ::
ጠጥተን የምንታጠብበትን ውኃ አጥቶ በዚህች ቅጽበት የሚያሸልብ ወገናችንን አንርሳ:: ደግመን እንላለን ጦርነት ክፉ ነው:: ረሃብ ደግሞ የባሰ ነው:: ሀገራችንን ከሁለቱም ዕረፍት ትፈልጋለች:: እስከዚያው ግን ለወገኖቻችን በየአቅጣጫው እንረባረብ!

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
መስከረም 3 2014 ዓ.ም.
✥┈┈•◦●◈◎❖◎◈●◦•┈┈✥
•➢ ሼር // SHARE//SUBSCRIBE
━━━━━━━━━━━━━━━━━━━━
@Ewkete_orthodox
@Ewkete_orthodox
━━━━━━━━━━━━━━━━━━━━