Get Mystery Box with random crypto!

ቀናት አዲስ የሚሆኑት በእግዚአብሔር በኩል ነው እነሆ አዳዲስ 'የሚመስሉንን' ቀናት ለመጀመ | ✟የማለዳ ፀሀይ✟

ቀናት አዲስ የሚሆኑት በእግዚአብሔር በኩል ነው

እነሆ አዳዲስ "የሚመስሉንን" ቀናት ለመጀመር አንድ ልንል ነው፡፡ በእርግጥ በጊዜ አቆጣጠር ሥርዓታችን መሠረት አዲስ ዘመን መጥቷል፡፡ ከዘመነ ማቴዎስ ወደ ዘመነ ማርቆስ ተሻግረናል (ተመስገን!)፡፡ እንዴት ነው ታዲያ ኑሮአችንስ? አዲስ ዓመት ላይ አዲስ ይሆናል?

አዲስ ዓመት ሲመጣ አዲስ ተስፋ፣ አዲስ እቅድ፣ አዲስ አኗኗር አብሮ ይመጣል እያልን መልካም ምኞት እንሰንቃለን፤ እንደዛም እናስባለን፡፡ ግን እንደ እውነቱ ደግሞ፤ እንኳን እኛ መስከረም አንድም ለራሱ አዲስ አይደለም፡፡ እንደ ኢትየጵያ የዘመን አቆጣጠር ስሌት ሁለት ሺህ ዐሥራ አራት መስረከም አንዶች ተቆጥረዋል፡፡ ያ ማለት ፪ሺ፬ ጊዜ መስከረም አንድ ተመልሶ መጣ እንጂ፤ አዲስ መስከረም አንድ እስከ አሁን አልተገኘም፡፡

ዝምብለን ስናስተውል ዞሮ ራሱን የሚደግመው ዘመኑ ብቻ አይደለም፡፡ በክብ ዛቢያ ላይ እንደሚሽከረከር አካል ተመሳሳይ ዓመታትን በተመሳሳይ አስተሳሰብ፣ በተመሳሳይ ፍላጎት፣ በተመሳሳይ ጠባይ፣ በተመሳሳይ ማንነት ጀምረን የምንጨርስ ብዙዎች ነን፡፡ አንዳንዴ ከአምናው ዘንድሮ ምንም ያልተለወጠ ሕይወት ስለምንመራ፤ ዓለም በምትባል ሰፊ ክፍል ውስጥ ተቆልፈን የምንመላለስ እስረኞች እንደሆንን ይሰማናል፡፡

ሰዎች ዓመቱ ገና ሲጀምር የአዲስነት ስሜት በበዓል ወከባው ምክንያት ይሰማቸውና፤ የቀኑ ሽር ጉድ ሲያልፍ አዲስነቱም በዛው ያልፋል፡፡ ስለዚህ ጳጉሜ አምስት ያቋረጡትን ለቅሶ መስከረም ሁለት ይቀጥላሉ፡፡ የነሐሴ ስሕተቶች ጥቅምት ላይ ለመታየት ይዘጋጃሉ፡፡

"ሁሉን አዲስ የሚያደርገው" እግዚአብሔር ከሕይወታችን
ስፍራ ውስጥ ቦታ የሚይዝበት ዕድል ሲጠፋ፤ የኑሮ ትርጉምና እውነተኛ ጣዕምም ይጠፋል፡፡ እናም በአዲሱ ዘመን ላይ ነባር ችግሮቻችን ነባራዊ ተጨማሪ ችግሮችን እያስከተሉብን ስንባዝን ለመገኘት እንገደዳለን፡፡ (የዮሐንስ ራእይ 21፥5) እስኪ ሁላችንም ውስጣችንን፣ ቤታችንን፣ ኑሮአችንን እና ራእያችንን እንመልከተው፡፡ እውነት አዲስ ወደ መሆን የሚሄድ አይነት ነው?

በሐዲስ ኪዳኑ ዘመን ቃል ሥጋ ሲሆን፤ 'ዓመት' የአባቱን ስም ከ'ፍዳ' ወደ 'ምሕረት' ቀይሮ "ዓመተ ምሕረት" ሲባል፤ እግዚአብሔር አብ አንድያ ልጁን ልኮ ሲያፈቅረን፤ እግዚአብሔር ወልድ የመለኮቱን ሚስጢር በሥጋና ደሙ በኩል ሲያካፍለን፤ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የሕይወት ምሪት ሆኖን ሲባርከን፤ በእርግጥም ዓመተ ምሕረቶችን በስስት ብንቆጥራቸው ትክክል ነው፡፡

ሆኖም እኛ መንፈሳዊነት እንደ ወግ አጥባቂነት እየታየን፤ ለገንዘብ እና ለሥጋ ድሎት ብቻ ዘወትር እየለፋን፤ የተሰጠንን ዓመተ ምሕረት ትተን የተለወጠልንን ዓመተ ፍዳን "አዲስ ነው" እያልን እንቆጥራለን፡፡

ከሕይወት ውስጥ እግዚአብሔር እንዲገኝ ክፋት፣ ምቀኝነት፤ ስግብግብነት፣ ተንኮለኝነት፣ ጎጠኝነት፣ ምቾት አሳዳጅነት፣ የሰየጠነ ዘመናዊነት ወጥተው፤ በንስሐ በኩል ያለፉ የዕለት ተዕለት አምልኮት ስግደትና የዘወትር ጸሎት ተተክተው፤ ባበላሸነው ዓመታት ውስጥ ተደላድሎ የቆየውን ክፋትና ኃይሉን የምንቃወምበት የጽደቅ ኑሮ ካልጀመርን፤ አዲስ የሚያደርገን ዓመት ገና አልመጣልንም፡፡

"እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን።"

(ወደ ሮሜ ሰዎች 6፥4)

በነገራችን ላይ በእግዚአብሔር ላሉት ዘመኑ ወደ ከፍታ የሚወጣበትን ዕድሜ ጨምሯል፡፡ የቅድስተ ቅዱሳኑን መቅደስ እያየነው ነው፡፡ ከዛም ውስጥ የሚፈልቀው ውኃ እየበዛ እየበዛ ሄዶ ማንም የማይሻገረው ወንዝ ይሆናል!

መልካም አዲስ የምትሆኑበት አዲስ ዓመት
@Ewkete_orthodox