Get Mystery Box with random crypto!

'ለኢትዮጵያ ቡና የፈረምኩት ራሴን በትልቅ ደረጃ ላይ ማየት ስለፈለግኩኝ ነው' ሄኖክ ደልቢ /ኢት | ኢትዮጵያ ቡና የሸገር አርማ

"ለኢትዮጵያ ቡና የፈረምኩት ራሴን በትልቅ ደረጃ ላይ ማየት ስለፈለግኩኝ ነው"

ሄኖክ ደልቢ /ኢትዮጵያ ቡና/

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ ቡና ለመጫወት በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ፊርማውን አኑሯል፤ ተወልዶ ያደገው በሐዋሳ ከተማ ውስጥ ነው፤ ሄኖክ ደልቢ ይባላል፤ በእዛም የውልደት እና የእድገት ቆይታው ለሐዋሳ ከተማ ክለብ ተጫውቶ ካሳለፈ በኋላ ነው ወደ ኢትዮጵያ ቡና ያመራው። ኢትዮጵያ ቡናን በመቀላቀሉ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማው የሚናገረው የአማካይ ስፍራ ተጨዋቹ ከሊግ ስፖርት ጋዜጠኛው መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ቆይታን አድርጓል።

ሄኖክ ለሊግ ስፖርት የሰጠው ቃለ-ምልልስም በሚከተለው መልኩም ቀርቧል፤ ተከታተሉት።

ሊግ፦ በቅድሚያ ለቃለ-ምልልሱ ፈቃደኛ ስለሆንክ ከልብ እናመሰግናለን?

ሄኖክ፦ እኔም የጋዜጣችሁ አምድ እንግዳ አድርጋችሁኝ ስለጋበዛችሁኝ ከልብ አመሰግናችኋለሁ።

ሊግ፦ በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ከሐዋሳ ከተማ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ዝውውርን አድርገሃል፤ የተሰማህ ስሜት ምን ይመስላል?

ሄኖክ፦ ኢትዮጵያ ቡና ትልቅ ቡድን ነው፤ በብዙዎቹ ዘንድም የሚወደድ ነው። ወደዚህ ቡድን በመምጣቴ የተሰማኝ ስሜት የተለየ ነው። ምክንያቱም ብዙ ደጋፊ ባለው ክለብ ውስጥ መጫወት መቻል መታደል ስለሆነና ከእዛም ባሻገር በኳሱም ራስህን አንድ ደረጃ ከፍ ወደምታደርግበት ቡድን ስትመጣና ብዙም ያላሳካካቸውን ድሎችንም ለማግኘት የምትመኘው ቡድንም ስለሆነ ወደ ቡና በመምጣቴ በጣም ደስተኛ ነኝ።

ሊግ፦ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በሐዋሳ ከተማ ክለብ ውስጥ ነው ቆይታን ያደረግከው፤ በእስካሁኑ የቡድንህ ጉዞ ስኬታማ ነበርኩ ማለት ትችላለህ?

ሄኖክ፦ በፍፁም፤ ያም ሆኖ ግን እንደ አንድ ቤቱ ውስጥ ከስር እንዳደገ ተጨዋች ደግሞ ጉዞዬ በዋንጫ ድሎች ባይታጀብም ጥሩ ቆይታ ነበረኝ። ቆይታዬ ጥሩ ቢሆንም የሊጉን ዋንጫ ባለማንሳታችን ደግሞ በጣም ነው የሚቆጨኝ።

ሊግ፦ ለወጣት ቡድኑ ስትጫወት ደግሞ ቆይታህ በዋንጫ የታጀበ ነበር?

ሄኖክ፦ አዎን፤ ያኔ ጠንካራና ምርጥ ቡድን ነበረን። የእኛ ቡድን ደግሞ ወጣቶች ላይ ብዙ ጊዜም ነው ውጤታማም የሚሆነው።

ሊግ፦ ወደ ኢትዮጵያ ቡና የተዛወርክበት መንገድ ምን ይመስላል? ከሌሎች ክለቦችስ ጥያቄ አልቀረበልህም?

ሄኖክ፦ ቀርቦልኛል፤ ያም ሆኖ ግን ጥያቄን ካቀረቡልኝ ቡድኖች ውስጥ የእኔ ምርጫ የሀገሪቱ ትልቅ ክለብ የሆነው ኢትዮጵያ ቡና ነው። ኢትዮጵያ ቡና ሁሌም ልጫወትለት የምመኘው ቡድን ነው ከእዛም ውጪ የሚመጡብኝን ፈተናዎችንም በእዚሁ ክለብ ውስጥ መጋፈጥን ስለፈለግኩና ነገም ላይ ራሴን በትልቅ ደረጃ ላይ ማየትንሞ ስለፈለግኩኝም ነው በምንም ነገር ወደ ኋላ ሳልል ጥያቄያቸውን ተቀብዬ ልፈርምላቸው የቻልኩት።

ሊግ፦ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ከማምራትህ በፊት ስለ ክለቡ ምን አይነት እውቀቱና ግንዛቤው አለህ?

ሄኖክ፦ ብዙም ግንዛቤውና እውቀቱ ባይኖረኝም ክለቡ ከእኔ አጨዋወት ጋር ይሄዳል የሚለውን ነገር ግን በሚገባ ተመልክቼበታለሁ።

ሊግ፦ ኢትዮጵያ ቡናን በተቃራኒነት የተፋለምክባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ?

ሄኖክ፦ አዎን፤ ከእነሱም ጋር ሆነ ከቅ/ጊዮርጊሶች ጋር ተቃራኒ ሆነህ ስትጫወት በኢትዮጵያ ውስጥ የምንገኝ አጠቃላይ ተጨዋቾች ሁለቱ ቡድኖች ብዙ ደጋፊዎች ያላቸው ስለሆኑና ትልቅም ቡድን ስለሆኑ ራሳችንን በደምብ ለማሳየትና ያለንንም አቅም አውጥተን ለመጫወት ወደ ሜዳም ስለምንገባም እኔም ቡናን በተቃራኒነት በገጠምንበት ጨዋታዎች ላይ ደስ ብሎኝና ጥሩም ሆኜ የተጫወትኩባቸው ጊዜያቶች ነበሩ።