Get Mystery Box with random crypto!

ይህ ወቅት ድንቅ ነው። የተማከሩ ይመስል በርካታ ጸሐፊያንና ሊቃውንት የመጻሕፍት አበርክቶአቸውን በ | ሀሁ መጻሕፍት /Hahu books

ይህ ወቅት ድንቅ ነው። የተማከሩ ይመስል በርካታ ጸሐፊያንና ሊቃውንት የመጻሕፍት አበርክቶአቸውን በተመሳሳይ ጊዜ የዘከሩበት ነው። በእርግጥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቤተክርስቲያናችን የንባብም የመፃፍም ልማድ የተነቃቃበት ጊዜ ነው ማለት ይቻላል። ይህ መነቃቃት ግን የቅርቡን መቶዎች ዓመታትን የጽሕፈትና፣ የምዕመናንን የንባብ ባሕል ያነጻጸረ እንደሆነ ግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ መረዳት ያስፈልጋል። ይህ መነቃቃት በወግ ከተያዘና በአገባብ ከተመራ ፍሬው የሚንዠረገግበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።

እኔም በአቅሜ ወቅታዊ መስሎ በተሰማኝ አንድ ርዕስ ላይ ጥቂት ነገር ለመጫር መረጃዎች ሰብስቤ፣ አቀናጅቼና አብረው ሊቀርቡ የሚችሉ ሌሎች ጽሑፎችን አጠናቅሬ አፈፃፀሙ ላይ ሳተኩር የተለያዩ የመጻሕፍት ጅረቶች ከልዩ ልዩ አፍላጋት በዙሪያዬ ይጎርፉ ጀመር። የደብተራ በአማን "ተኀሥሦ"፣ የዲያቆን ሄኖክ "የብርሃን እናት"፣ የመጋቤ ብሉይ ወ ሐዲስ አባ ገብረ ኪዳን "መጽሐፈ ምዕዳን" በተለያዩ ኅብረ ቀለማት ሚዲያውን ሲያጥለቀልቁት ከመደነቅ በተሻገረ ጉጉት እየተናጥሁ ተመለከትሁ።

ጉጉቴ ይዘታቸውን ምንጫቸው እንደሚወስነው ስለተረዳሁ ይመስለኛል። ጥቂት ቀደም ብለው ለንባብ የበቁት እንደ "የልቡና ችሎት"፣ "ሳብራ"፣ "ኦርቶዶክሳዊ አዕምሮ"፣ "መንገደ ብርሃን" "ሚተራሊዮን" ... መጣሁ መጣሁ የሚሉት የመምሕር ፋንታሁን ዋቄ "ኦርቶዶክሳዊነትና የሠይጣን መንግሥት" እና "ሥዝም ሰብአዊነት" የኢዮብ ቱሉ "ንጥቂያ" ... መካከል አንድ አነስ ያለች ሥራ ይዤ መቀላቀሌ መሰለኝ። ነገሩን ያየሁት ለአንድ ታላቅ በዓል ዝግጅት ከአንድ ታላቅ ገበያ ዶሮ ገዝቼ የበግ ጠቦትና የፍየል ሙክት፣ ወይፈንና ሰንጋ ከሚነዱ ሰዎች መካከል ኩስ ኩስ እያልኩ እንደሆነ ነው። ያም ሆኖ ከንባብ የሚያጎድል የለምና ምንም ታናሽ ብትሆን ይህችን መጽሐፍ ለአንባቢያን አበርክቻለሁ።

በመጽሐፏ ውስጥ የታሪክ ምሑራንን ያህል ጥልቅ ባይሆንም በአንድ ታሪካዊ ሙግት ላይ መከራከሪያዬን አቅርቤያለሁ። ጥቂት ስብከታዊ ጽሑፎችና ምልከታዎችም ተካተዋል። የእቅበተ እምነት ጽሑፎችም አሉበት። ለማዋዛት ያህል ውስን ገጠመኞቼንም የመጽሐፌ አካል አድርጌያቸዋለሁ። ይህች "ጩጬ" መጽሐፍ በማንኩሳ ማተሚያ ቤት ስትዋብና ስትኳል ከርማ በነገው ዕለት ወደ ብርሃን ትወጣለች። ከነገ በስቲያም ጀምሮ በዋና አከፋፋዩ ሀሁ መጻሕፍት ቤት አማካኝነት ወደየመጻሕፍቱ መደብርና ወደ አንባቢዎቿ እጅ ትደርሳለች።

መጽሐፏ ውስጥ በተጠቀሰ አድራሻ አስተያየታችሁን እንደምታኖሩ ተሥፋ አደርጋለሁ። እርማት፣ ምክር፣ ትችት፣ ተግሳፅና ነቀፋ.. ሁሉንም ዓይነት አስተያየት እቀበላለሁ። የልብና የአንደበት ቅድስናችሁን እንዳያጎድፍ እሠጋለሁ እንጂ የፈለገ ሰው ሊሰድበኝና ሊረግመኝም ይችላል። ሁሉን በአኮቴት እቀበላለሁ። የትኛውም አስተያየት አንዳች ነገር ያመላክተኛል። ጌታ ቢፈቅድ በቀጣይ ለሚኖረኝ ዳጎስና ጠብሰቅ ላለ ሥራዬ ከአቀራረብ እስከ ይዘት ሁለንተናዊ ግብዐት ይሆነኛልና ስለ ሁሉም አመስጋኝ ነኝ።

ክብረት ይስጥልኝ...!
ማርያማዊት ገብረ መድን
ዋና አከፋፋይ ሀሁ መጻሕፍት
አድራሻ፦ ቁ.1 አ.አ ስታድየም ናሽናል ታዎር
ቁ.2 ሜክሲኮ ደብረ ወርቅ ህንፃ
ስ.ቁ. 0911006705