Get Mystery Box with random crypto!

መዝራትና ማጨድ “እያንዳንዱ ቀንህን መመዘን ያለብህ በሰበሰብከው ፍሬ ሳይሆን በዘራኸውና በተከልከ | ስብዕናችን #Humanity

መዝራትና ማጨድ

“እያንዳንዱ ቀንህን መመዘን ያለብህ በሰበሰብከው ፍሬ ሳይሆን በዘራኸውና በተከልከው ዘር ነው” - Robert Louis Stevenson

ሁሉም ነገር የሚፈጠረው ሁለት ጊዜ ነው፣ በመጀመሪያ በሃሳብ መልክ፣ ከዚያም በገሃዱ ዓለም፡፡ ዛሬ በሃሳብ፣ በንግግርም ሆነ በተግባር የሚዘራው ዘር የነገውን እውነታ እንደሚፈጥርበት የማያስተውል ግለሰብም ሆነ ሕብረተሰብ ጥበብ እንደጎደለው ማሰብ አያስቸግርም፡፡ ይህንን የመዝራትና የማጨድ ሕግ ያልተገነዘበና ስርአት የሌለው ሕብረተሰብ በውጤቱ ለአመለካከቱና ለራሱ የሚገባውንና የሚመጥነውን አለም ይፈጥራል፡፡

የምትኖርበት ሕብረተሰብ ያለበትን የወቅቱን ሁኔታ ተመልከት፡፡ ይህ ሕብረተሰብህ ያንን ሁኔታ ማንም አልፈጠረበትም፤ ቢፈጥርበትም ያንን ተቀብሎ የመኖርን ደካማነት ማንም አላስታቀፈውም፡፡ ይህ ሕብረተሰብ ትናንት የዘራውን ዘር ፍሬ ዛሬ እየበላ ነው፡፡ ይህ እውነታ ደግሞ በዙሪያችንም ሆነ በግል ሕይወታችን የምናያቸውን መልካምም ሆነ ክፉ ሁኔታዎች የሚወክል የማይለወጥ እውነታ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ፣ እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ማሕበረሰብ የምንኖርበትን ዓለም የምንፈጥረው እኛው ራሳችን ነን፡፡    

አንድ ሕብረተሰብ ከጥበብ ጎዳና ሲርቅ፣ ትናንት ያቆሸሸው አካባቢ ዛሬ በስብሶ ነገ በሽታን እንደሚሰጠው ማሰብ ያቅተዋል፡፡ ይህ አይነቱ ህብረተሰብ ባለበት ሲርመሰመስና የራሱን ቁስል በራሱ ምርጫና ውሳኔ ሲፈጥር አመታትን ያሳልፋል፡፡ ዛሬ በራስ ወዳድነት፣ በእኔ እበልጣለሁ ስሜትና በስግብግብነት የጎዳው የሕብረተሰብ ክፍል ነገ መልሶ ያንኑ ዛሬ እርሱ የዘራውን ዘር ፍሬ ጨምቆ መራራ ጽዋ እንደሚያስጎነጨው አያስተውለውም፡፡ በከፍታ ዘመኑ ለሰዎች ግድ-የለሽነት የዘራ ጥበብ-የለሽ ሰው፣ የእርሱ ዘመን አልፎ የሌላው ዘመን ሲመጣ ከእርሱ የባሱ ግድ-የለሾች እንዲፈጠሩ የሚያደርገው እርሱው ራሱ መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡

የዛሬ ጉልበተኛ፣ ነገ ከእርሱ በኋላ የሚነሳው የዘመኑ ጉልበተኛ እንዲረግጠው የሚያደርግን ዓለም የሚፈጥረው ራሱው ነው፡፡ ይህንን ሕብረተሰቡ ከዘመን ወደ ዘመን ሲርመሰመስ የሚኖርበትን ኡደት ግን ለመስበር አቅም ያለው ሰው የጥበብን መንገድ ለማስተዋል ራሱን የሰጠ ሰው ብቻ ነው፡፡  

በጤንነት ዘመንህ ጊዜ ያልዘራኸውን በሕመም ጊዜ አታገኘውም፣ ያልተዘራው አይበቅልምና! በወጣትነት ጊዜ ያልዘራኸውን በሽምግልናህ ዘመን አታገኘውም፣ በሽምግልና ዘመን የሚበላው በወጣትነት ዘመን የተዘራው ዘር ነውና፡፡፡ በብዙ ወዳጅ በተከበብክና በተወዳጅነትህ ጊዜ ያልዘራኸውን በብቸኝነት ጊዜ አታገኘውም፡፡ በአመራር ከፍታ ዘመንህ ያልዘራኸውን የአመራር ዘመንህ ሲያልፍ (ማለፉ አይቀርምና) አታገኘውም፡፡  ከዚህ ውጪ ስሌት የለም፡፡ 

በሚገባ ስናስበው ምርጫችን እጅግ ውስን ነው፡፡ አንዱ ምርጫችን ጤና-ቢሱን ዘር ዘርተን ጤና-ቢሱን ፍሬ ሲበሉ መኖር፡፡ ሌላኛው ምርጫችን፣ የነገን በማሰብ ዛሬ መልካም ዘርን በመዝራት የነገውን ፍሬያችንን በቁጥጥር ስር ማዋል ነው፡፡ ከእነዚህ ከላይ ከተጠቀሱት ምርጫዎች ለየት ያለውን ምርጫ የሚከተሉ ብዙ ሰዎች፣ በጠማማ መንገድ ረጅም ርቀት ከተጓዙና በመጨረሻ ሁሉን ነገር ካጡ በኋላ ትክክለኛውን ነገር ፍለጋ ወደኋላ ይመለሳሉ፡፡ በንግግራቸውና በተግባራቸው የማይሆንን ዘር ሲዘሩ ከርመው አረምን ሲለቅሙ የመኖር ሞኝነት፡፡

መፍትሄው አጭርና ግልጽ ነው፡፡ የምትበላውን ፍሬ ካልወደድከው፣ የዘራኸውን ዘር አስተውልና ቀይረው፡፡ ዘርህ ሲቀየር ፍሬውም ከዚያው ጋር ይለወጣል፡፡ ዛሬ  በምትወስነው ውሳኔህ፣ በምትመርጠው ምርጫህና በምትዘራው ዘርህ የነገህን በትክክል መተንበይ ትችላለህ፡፡

ውብ ቅዳሜ!

@EthioHumanity
@EthioHumanity

@EthioHumanityBot