Get Mystery Box with random crypto!

ምክር ለወዳጅ ምክር ብትሰማ በነፃ ትማራለህ።ምክርን አልሰማ ብትል ግን በዋጋ እንደምትማር እወቀ | ስብዕናችን #Humanity

ምክር ለወዳጅ

ምክር ብትሰማ በነፃ ትማራለህ።ምክርን አልሰማ ብትል ግን በዋጋ እንደምትማር እወቀው።በዋጋ መማር ግን አድካሚ ደግሞም የሚያስመርር ነው።ብልህ ከሆንህ በሰው ከደረሰው ትማራለህ ሞኝ ከሆንህ ግን በራስህ ሲደርስ ትማራለህ።

በአመት የካብከውን በዕለት የምትንደው በቁጣህ ነውና አትቆጣ።ቁጣ አውቀህ እንዳላወቀ ለፍተህ እንዳለፋ የሚያደርግ በመልካም መሰረት ላይ የአገዳ ቤት የሚሰራ ነው።በገዛ እጅህ ዋጋህን እንዳታሳንሰው ቁጣህን ያዘው።

በወጣትነት ሁሉም ነገር ትክክል ነው ከሚል መመሪያ ውጣ።ሁሉንም ካላየሁ አላምንም አትበል።ሰምቶ ማመን ከተጎዱት መማር አስተዋይነት መሆኑን አትርሳ።የሰማንያ አመት እውቀትን ለመገብየት ግድ ሰማንያ አመት መኖር የለብህም።ሰማንያ አመት ከኖሩት በትህትና መጠየቅ ይገባሀል።

አይንህ የፊቱን ቢያይ ልብህ የኋላውን ያስብ።ነገ እንድትደርስ የትላንቱን አትርሳ።የምትሔድበት እንዳይጠፋህ የመጣህበትን አትዘንጋ።

ክፍት አይሙቅህ መልካም ነገርም ብርድ ብርድ አይበልህ።ለክፋት አቅም ካለህ ለበጎ ነገርም አቅም አለህና።ተግባርህ የምርጫህ ውጤት ነውና አስብበት።ክፋ ሰርተህ እንቅልፍ ሲወስድህ ሰይፍ ላይ መተኛትህን እወቅ።

ማግኘት ማጣት የኑሮ ተራ እንጂ አደጋ አይደለም።የተቀበልከው ያንተ ያልነበረውን ነው የተወሰደብህም ያንተ ያልሆነውን ነውና አታንጎራጉር።

ስትጠግብ የምትራብ ስትራብ የምትጠግብ አይመስልህም።ነገር ግን ሁሉም ይለወጣል።ዛሬ ያለኸው በጨለማው ከሆነ ቀጥሎ ብርሃን ነውና ደስ ይበልህ።ዛሬ ያለኸው በብርሃን ከሆነ ቀጥሎ እንዳይጨልምብህ ተጠንቅቀህ ያዘው።በመከራ ውስጥ ካለው ሰው በድሎት ውስጥ ላለው ቀጥሎ አስፈሪ መሆኑን አስብ።በእውነት ጥጋብህ እንዳለፈ ረሀብህም እንደሚያልፍ እመን።

የትላንትናውን ምሽት ስትይዝ አይነጋም ብለህ ሳይሆን ብርሃንን ተስፋ አድርገህ ነው።ከሌሊት ቀጥሎ ሌሊት አይመጣም።ከሌሊት ቀጥሎ ቀን ይሆናል።እንዲሁም ከዛሬ መከፍትህና ሀዘንህ በሀላ ታላቅ መፀጰናናት ይሆናል።

ሁሉም የራሱ ትግል አለውና እንደ እገሌ ምነው ባደረገኝ አትበል።ትዕግስት ስጠኝ ብለህ ለምን እንጂ።በዚህ አለም ላይ የሚታዘንለት እንጂ የሚቀናበት ሰው የለምና።

እገሌ ይናገርልኝ እገሌ መልስ ይስጥልኝ ከሚል ጥገኝነት ተላቀቅ።ጥቂትም ቢሆን በማታውቀው ሙያ ሰራተኞችን ተማምነህ ስራ አትጀምር።ስልጣን ሲሰጡህ መሪ እንጂ አለቃ አትሁን።ከፊት እየቀደምህ አስከትል እንጂ ከሀላ ሆነህ አትቅደም።

የመከራ ቀን ወዳጆችህን አትርሳ።የዛሬ ሰው ብቻ አትሁን።የትላንቱንም አስብ።አንገት የተፈጠረው ዞሮ ለማየት ነውና።

ታሪክን በጣም ወቃሽ አትሁን።አንተም በታሪክ ፊት ነህና ተጠንቀቅ።ያለፋት ተመልሰው መጥተው ያበላሹትን ማበጀት አይችሉም።አንተ ግን እድል አለህና እወቅበት።ታሪኬ እንዲያምር ብለህ አስመሳይ ፃድቅ አትሁን።ዛሬ በቅንነት የምትሰራው ግን ለታሪክህ ይተርፋል።ስራህን ስራ እንጂ ለስምህ አትኑር።አለም እንደ እቅድህ አይደለምና።

ሰዎች ሁሉ እንደ እኔ ካላሰቡ ብለህ አትጥላቸው።ሰው ላንተ ፈቃድ የተፈጠረ አይደለም።ደግሞም ነፃ ፈቃድ ያለው ፍጡር ነው።ነፃ ፈቃዱን እያከበርክለት ወደ እውነት ምራው።ከጠባብ ድንኳንህ ውጣ።

ዛሬ ዋሽተህ ማምለጡ ድል ይመስልሀል።የታወቀብህ ቀን ግን በውሸትህ ያመነህ ሰው በእውነትህ ግን አያምንህምና አትዋሽ።ውሸታምና አመንዝራ ተለውጠው እንኳ ቶሎ የሚያምናቸው አያገኙምና ከውሸት እራቅ።

እጅግ ግልፅነት እብድ ያደርጋል።እጅግ ዝምታም ወዳጅ ያሳጣልና ንግግርህና ዝምታህ በቦታው ሲሆን ውበት ይሆናል።

የእኔ መናገር ምን ይለውጣል?ብለህም ስህተትን አትለፍ።የእኔ አስተዋጵኦ ምን ይጠቅማል?ብለህም ስጦታህን አትጠፍ።

አሸናፊ መኮንን

ውብ አዳር

@EthioHumanity
@EthioHumanity

@EthioHumanitybot