Get Mystery Box with random crypto!

አፍርሰህ አትገነባም. የሄደ ነገር ተመልሶ ይመጣል። ሰብረህ ያጠፍኸው የመሰለህ ነገር ይዘገይ ይሆ | ስብዕናችን #Humanity

አፍርሰህ አትገነባም.

የሄደ ነገር ተመልሶ ይመጣል። ሰብረህ ያጠፍኸው የመሰለህ ነገር ይዘገይ ይሆናል እንጂ አይቀርምና አፀፍውን መልሶ ሊያስታቅፍህ ምንአልባትም እጥፍ ድርብ አድርጎ ደጃፍህ ላይ ቆሞ በርህን ያንኳኳል። ኃላፊነት በንግግር፣ ተግባርና ሁሉም መስክ ላይ እንዲንፀባረቅ የተገባው በእዚህና መሰል ምክንያቶች ነው።

እርግጥ ነው ኃላፊነትን በፀጋ መቀበል እና ሳይሸራርፉ በተጨባጭ መወጣት ፈታኝ ነው። አስተዋይ አእምሮ እና ቅን ልቦና በምርጫና መንገድህ ካልተለየህ ግን በድል ትወጣዋለህ። ድሉም ከበደል የፃዳ ይሆናል። ድሉ ከራስህ አልፎ አለምን ስለሚጠቅም መልካሙ ስርህ ሄዶ ዞሮ ሲመለስ በጎ ምላሽ ማግኘትህ አይቀሬ ነው። ወርቅ ለሰጠ ወርቅ እና ጠጠርም ለሰጠ ጠጠር ማግኘት ተፈጥሯዊ ህግና የህይወት ነባራዊ እውነታ ነውና።

መልካምነት ከማንም በላይ ላራስ ነው ጥቅምና ፍይዳው። ቅን ሀሳብ አሳቢውን ይባርካል። ሴራ፣ ተንኮል እና ክፍት ህሊናና ልብህን ከሞላው ግን ሌላው ይቅርና መልካም እንቅልፍ እንኳ ብርቅ እና ሩቅ እንደሚሆኑብህ ልነግርህ እችላለሁ።

አዳርህ በመባነን እና መበርገግ ይሞላል። ቀን ያሳደድከው በህልምህ መግቢያና መሸሸጊያ ጥግ ያሳጣሀል። ቀን ከሌት የዘራሀቸው ክፋቶች ሌሎችን ብቻ ሳይሆን የአንተን የገዛ ራስህንም ገላም ይቧጥጣሉ። ከአንተ የመነጨና ተንደርድሮ የተተኮሰ ኃይል በእኩል መጠን እና ልክ አጥፊ እንደሆነ ራስህንም ያጠፍል፤ አልሚ ከአደረከው ደግሞ ቅድሚያ አንተን እና የእኔ የምትለውን ሁሉ ባርኮ ለሌሎች ይተርፋል።

ይህ የህይወት ሀቅ ከፊዚክስ action/reaction ተፈጥሮአዊ ህግ ጋር ይመሳሰላል። አፍርሰህ አትቆምም። ጠልተህ ፍቅርን አታተርፍም። ወደህ ላትከበር፣ ትህትናን ሰጥተህ ልትናቅ፣ አሳቢና አስታዋሽ ሆነህ ሳለ ልትረሳ አትችልም። ምክንያቱ ደግሞ ምዕራባዊያን እንደሚሉት የሄደ ነገር ተመልሶ ይመጣልና ነው (what goes around comes around)። አበውም አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል፣ የሰው ፈላጊ የራሱን ያጣል፤ በቆፈሩት ጉድጒድ መቀበር አይቀርም ወዘተረፈ ብለውናል።

ነጋሽ አበበ

ሰናይ ምሽት ይሁንልን

@EthioHumanity
@EthioHumanity

@EthioHumanityBot