Get Mystery Box with random crypto!

'ባለቤቴ ምጧ እንደመጣ ወደ ሆስፒታል አመራን ፣ ልጃችን እንደተወለደ ነርሷ የልጃችንን ፆታ ወንድ | ስብዕናችን #Humanity

"ባለቤቴ ምጧ እንደመጣ ወደ ሆስፒታል አመራን ፣ ልጃችን እንደተወለደ ነርሷ የልጃችንን ፆታ ወንድ ወይም ሴት ናት ብላ ልትነግረን አልፈለገችም። ከዛ በኋላ የልጃችንን ፆታ ለምን ልትነግረን እንዳልፈለገች አጥብቄ ጠየቅኳት። ነርሷም "ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሆስፒታሉ ፆታን በተመለከተ ምንም አይነት መረጃ መስጠት እንደማንችል ስልጠና ተሰጥቶናል። የልጃቸውን ፆታ ይሄ ነው ብለህ ስትነግራቸው ሆስፒታሉን እና የጤና ባለሙያዎቹን በታላቅ ቁጣ በአንድ እግራቸው የሚያቆሙ ሞገደኛ ወላጆች አሉ " ብላ መለሰችልኝ። አሁን የገባኝ ነገር የምንኖርበት አለም የዕብደት ሆኗል!"

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ የገጠማትን ጨመረች " በቅርቡ ወንድ ልጄን ስወልድ የሞላሁት የልደት ሰርተፍኬት ፎርም የፆታ ማሳወቂያ ሶስት አማራጮች ነበሩት። ወንድ_ ሴት__ እና ያልተወሰነ_.....! አስቡት የምንወልዳቸው ህፃናት በአንድ ጊዜ ወንድ ወይም ሴት ከመሆን የዘለለ ምርጫ ባይኖራቸውም ሶስተኛው አማራጭ የተተወው ህፃናቱ ሲያድጉ በራሳቸው ምርጫ ፆታቸውን እንዲመርጡ ታስቦ ነው"

እነዚህን አስተያየቶች What is a woman? ከሚለው የ Matt Walsh አስደናቂ ዘጋቢ ፊልም ስር ያስቀመጡት በሃገራቸው ስር ሰዶ በተንሰራፋው ፆታን ከመረዳት እስከ መቀየር በደረሰው ማህበረሰባዊ ጤንነታቸው ግራ የተጋቡ አሜሪካዊያን ወላጆች ናቸው።

የሶስት ሴት ልጆችና የአንድ ወንድ ልጅ አባት የሆነው ማት ዎሽ What is a Woman? ( ሴት ምንድናት?) የሚለውን ቀላል ጥያቄውን ይዞ ከአሜሪካ ጎዳናዎች አንስቶ ግዙፍ ዩኒቨርስቲዎቿን አስከሚመሩት ምሁራን " ሴት ምንድናት" እያለ ቢጠይቅም የሚያገኘው መልስ የራሱን ጤንነት እስኪጠራጠር ድረስ አስደንጋጭ ነበር።

ማት አንዲት ፆታዋን ቀይራ ወንድ ነኝ ከምትል ቆንጆ ጋር ቁጭ ብሎ "ሴት ምንድናት?" ብሎ ጠየቃት። ይህቺው ቆንጆ "እስኪ ሴቶቹን ጠይቃቸው። እኔኮ ሴት አይደለሁም" ትለዋለች። ወንዶቹም ከፆታቸው ተካክደው ሴት ሆነው ያወሩታል። ማት ለመሞገት ቢሞክርም ኋላ ቀር የዳይኖሰር ዘመን ሰው መስሎ ይታያቸዋል።

ማት በመንገድ የሚያገኛቸውን የተለያዩ ወጣቶችን ይጠይቃል " እኔ እንደምታዩኝ በእውነታው ወንድ ነኝ። እራሴን ሴት ነኝ ብዬ ብገልፅና ብቀርብ ምላሻችሁ ምንድነው?" ታዲያ ለዚህ ጥያቄ ከወጣቶቹ የሚያገኘው አብዛኛው መልስ " ምርጫህ ያንተ ነው። ሴት ነኝ ብትለኝም ችግር የለብኝም። ሁሉም ሰው ነኝ ብሎ የሚያምነውን ነው። ያን ያህል የሚያስጨንቀኝ ጉዳይ አይደለም " የሚል ነበር።

ማት ወደ ዩኒቨርስቲዎች አምርቶ በስነ ፆታ ማህበራዊና ቤተሰባዊ ጉዳዮች ጥርሳቸውን የነቀሉ አንቱ የተባሉ ምሁራንና ባለሙያዎችን በሴት ምንነት ፣ የፆታ ክፍፍልና ብየናችን በተፈጥሮ መሰረቶችና በእውነታው መመዘን እንዳለበት ቢሞግትም የአብዛኞቹ ትንተናና አረዳድ እንደሚከተለው ነው .... 'የሰው ልጆች ፆታቸው በመራቢያ አካላቸው ማለትም በብልቶቻቸው ምክንያት ሊወሰን እንደማይችልና ፆታቸውን በውስጣቸው ከሚሰማቸው ስሜት ተነስተው መምረጥ እንደሚችሉ በምርጫቸውም ላይ የዘረመል ተዋፅኦዋቸው ያለውን የምናልባት ድርሻ በመተንተን ይህም ማለት ሴት ወይም ሴትነት ጡት ስላንጠለጠለችና Vagina ስላላት የሚገኝ እንዳልሆነ ያስረዳሉ። ለወንዶችም ወሸላ ማንጠልጠላቸው ፆታቸውን ወንድ ነው ለማለት ብቁ አይደለም። ሴትም ሆነ ወንድ ፆታቸውን ውስጣቸው እንደሚሰማቸው ስሜት መምረጥና መቀየር መብታቸው እንደሆነ የአብዛኛው ምሁራንና ባለሙያዎች አቋም ነው።

ታዲያ ይህንን ፆታን በተመለከተ የተዛባው አመለካከት ፆታን በመበየን አላቆመም። ወንዶችን እንደፍላጎታቸው ሴት ለማድረግ ሴቶችንም ወደ ወንድነት ለመቀየር ሆስፒታሎች ተቋቁመው የፆታ ቅየራ gender transplant ይሰራላቸዋል። ወንዶች ቀዳዳ ያበጃሉ ሴቶችም ያንጀለጅላሉ። ፆታ መቀየሩ የሚያስከትለውን የሆርሞን መዛባት ለማስተካከል በፋብሪካ እንደ መድሃኒት የተመረቱ ሆርሞኖች የፆታ ቅየራውን ተከትለው ጥቅም ላይ ይውላሉ። ኢንዱስትሪው በቪሊየን ዶላሮች እየዘወረ ትውልዱ ከማይቀር የማንነት ቀውስ ውስጥ ይወድቃል።

ህፃናት በጨቅላ እድሜያቸውና ባልበሰለ አዕምሯቸው በዚህ ውዝግብ ውስጥ ገብተው በየ ሆስፒታሉ ፆታቸውን ለመቀየር ላይና ታች ይቀደዳሉ። አብዛኞቹ ፆታቸውን ያስነካኩ ወይም gender transplant ያሰሩ ህፃናት
ከሚገጥማቸው የማንነት ቀውስ የሚያወጣቸው አጥተው አብዛኞቹ ራሳቸውን ያጠፋሉ።

ማት በዚሁ ዘጋቢ ፊልም እንዳሳየን ፆታቸውን ወደ ሴትነት የቀየሩ ወንዶች በተለያዩ የስፖርት ውድድሮች ከሴቶች ጋር ሴት ነን ብለው እየተወዳደሩ ውድድሮችን ያሸንፋሉ። የካዱት ተፈጥሯዊ ማንነታቸውና ፆታቸው ውድድሩን ለማሸነፍ እንደረዳቸው ቢጠየቁም ማሸነፋቸው ከስራና ከጥረት ጋር እንጂ ከፆታ ጋር እንደማይገናኝ አጥብቀው ይሞግታሉ። በነሱ አለም ሴት ነኝ ያለ ሴት ወንድ ነኝ ያለም ወንድ ነው።

ፆታቸውን ያስቀየሩ ወይም ሴት ነን ብለው የሚያምኑ ወንዶች የሴቶች ሽንት ቤት ካልተጠቀምን ፣ ሴቶች የሚጠቀሙበት ስፓ ውስጥ ገብተን ካልታሸን በሚል የአደባባይ አንባጓሮ ይፈጥራሉ። አስቡት... ልብም በሉ አንድ ወንድ ወሸላውን እንጠልጥሎ ከሴቶች ጋር ካልሸናው ከሴቶች ጋር ካልታጠብኩ ይላል። በዚሁ ፆታቸውን በቀየሩ ሰዎች የሽንት ቤት አጠቃቀም ዙሪያ ከማት ጠንከር ያለ ጥያቄና ክርክር የገጠማቸው የኮንግረስ አባል ጥያቄውን ለመመለስ ከመጨነቃቸው የተነሳ ከፍተኛ ፍርሃት እየተነበባቸው ቃለ መጠይቁን እስከማቋረጥ ደርሰዋል። ከምሁራኑ እስከፖለቲከኞቹ የሚያስፈራቸው አንዳች ሃይል ምን እንደሆነ ግራ ያጋባል።

በዚህና መሰል ጉዳዮች ላይ ለተቃውሞ መንቀሳቀስና አጥብቆ መጠየቅ በኋላ ቀርነት አስፈርጆ የዳይኖሰር ዘመን ሰው ያስብላል። ሚዲያውም ሆነ ምሁራኑ በግላቸው ያመኑበት አቋም እንዳለ ሆኖ በጉዳዩ ላይ የሰላ ትችትን ማቅረብ ይፈራሉ።

በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ Hollywood Netflix እና ግዙፍ የፊልም ኢንዱስትሪዎች ፆታን መርጦ ስለመቀየርና የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻን በተመለከተ በፊልሞቻቸው ይሰብካሉ። በአሜሪካ ተደማጭነት ያላቸው ፖለቲከኞችና የህዝብ ተወካይ ሴናተሮች ወገባቸውን አስረው ፆታን መርጦ ስለመቀየር ያልተገደቡ መብቶች ይሞግታሉ።

ማት ቢጨንቀውና ሃገሩን አሜሪካን ቢጠራጠር ሴት ምንድናት የሚለውን ጥያቄውን ይዞ የኬንያ የገጠር መንደሮች ውስጥ ተገኘ። የማሳይ ጎሳ አባላትን አጊንቶ ሴት ምንድናት አላቸው? ማሳዮች የጠራ ተፈጥሮአዊ መልስ ነበራቸው "ሴት የምትወልድ ናት ፣ ሴት ጡት ያላት ፣ ሴት የመራቢያ አካል ያላት ወልዳ የምታጠባ ናት። ሴትና ወንድን ለመለየት አንቸገርም" አሉት። ማት ለማሳይ ጎሳ አባላት በሃገሩ ያለውን ፆታን የመረዳትና የመቀየር ዝብርቅርቅ አስረዳቸው። ማሳዮች ሳቁ ተገረሙም። ማት ወደ ማሳይ ሄደ እንጂ ወደ ሃገሬ ኢትዮጵያ ቢመጣ በመስቀለኛ ማማተብን ይለምድ ነበር።

ማት በስተመጨረሻ "ሴት ምንድናት?" ብሎ ጥያቄ ያቀረበላቸው ምሁር በትዕቢት ተሞልተው "ሚስትህን ጠይቃት" ባሉት መሰረት አለምን የዞረበትን ጥያቄ ይዞ ወደ ሚስቱ ተመልሷል።

ሚስቱ ምን ትመልስለት ይሆን ?

ዘጋቢ ፊልሙን ከማየት ብዙ መረዳትና መልሶች ያገኛሉ!

ሙሉቃል ቃል

@Ethiohumanity
@Ethiohumanity