Get Mystery Box with random crypto!

Noble Truth [የከበሩ እውነታዎች] by DEMIS SEIFU  በመኖር ወዲያ ወዲህ… በመ | ስብዕናችን #Humanity

Noble Truth [የከበሩ እውነታዎች]

by DEMIS SEIFU 

በመኖር ወዲያ ወዲህ… በመክረም ገበታ… በመውጣት መግባት መስተጋብር… በፍለጋ ላይና ታች ፍኖት… መሆናቸው እርግጥ ከሚባልላቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ነው…ድቁሳት… Dukkha ይሉታል ምስራቃውያኑ… Suffering የሚለውን ቃል ፈተና ወይም ድቁሳት እያልኩ ልረዳው ወደድኩ… ስቃይ የዘለለት ቅኝት.. ፈተና የጊዜያዊነት ስሜት አለውና…

ቡድሃ “The Four Noble Truths” በተባለው የመጀመሪያ ትምህርቱ ላይ ስለ ድቁሳት /ፈተና/ አራት ቁምነገሮችን አስተምሯል…

፩. There is suffering…

የመጀመሪያው ንዑድ እውነት “ድቁሳት አለ” ይላል… በቃ መደቆስ አለ… ይህንን እውነት መካድ አይቻልም… ከኑረት ገጾች በአንደኛው ላይ መታተሙ … ካለፍ አገደም ሁሉንም ቤት መጎብኘቱ ሳይታለም የተፈታ ነው… ስለዚህም እውቅና ከመስጠት እንጀምር ይላል ቡድሃ… አይቀሬነቱን ከመቀበል… ይህም ሁኔታውን ‘ለምን እኔ ላይ ብቻ…’ ከሚል ተጨማሪ ህመም ነፃ ያደርገዋል… መደቆስ ስላለ ተደቆስን እንጂ ‘እኛ’ ስለሆንን ሆነብን አንልም ማለት ነው… ሁሉም እንደየብጤቱ ይደቆሳል… እንደ ትከሻው… What do we have in common is suffering…

፪. There is an origin of suffering…

“እያንዳንዱ ድቁሳት የራሱ ሰበበ ኑረት አለው”… እርሱም የፍላጎት እስረኝነት ነው… ልክ ያልተበጀለት ፍላጎት የስቃይ ምንጭ ይሆናል… ስለዚህም የማይረካን ፍላጎት ወግድ ማለት ደግ ነገር ነው… እርግጥ ‘ፍላጎት’ እንዲጠፋ መፈለግም ያው ‘ፍለጋ’ ነው… ቁምነገሩ ፍላጎትን የመግራት ጥበብ ካለመፈለግ አይከሰትም… ፍላጎትህ የህመም ሰበብ መሆኑን ከመረዳት እንጂ… ደግሞም መፈለግህ ብቻ አይደለም ችግር… የሚያስፈልግህን አለማወቅም እንጂ…

ቁጭ ብለህ በእግረ ሃሳብ የምትኳትነው… በውጣ ውረድ ድግግሞሽ ባትለህ የምትውለው ለኑረትህ ግድ የሆኑትን ለማግኘት አይሆን ይሆናል… በዙሪያህ ባሉ ሁኔታዎች በቀላሉ በሚቃኝ አዕምሮህ ግፊት የአግበስባሽነት ኢጎ ተጠናውቶህ ሊሆን ይችላል… ችግሩ የፈለግኸውን አግኝተህ እንኳ ባገኘኸው አትረካም… ቀዳዳ ኪስ አይሞላማ… ሌላ ጨምር ይልሃል… ቀዳዳውን ስትደፍን ግን ሙላትህን መገንዘብ ትጀምራለህ… ፍላጎትን ፈር ማስያዝ እንግዲህ ቀዳዳን መጥቀም ነው… እኔዬ በቂ ነው ማለት…

ለኑረትህ ግድ የሚባሉ ነገሮችን ማወቅ የሰላምህ ምንጭ… የሚጎድልም የሚሞላም የሌለህ መሆንህን ማወቅ ደግሞ አብርሆት ነው… ከውጭ የምታሳድደው ሁሉ የውስጥህን አይተካም… በቅርፃዊዉ ዓለም የቁሳዊነትም ሆነ የፍለጋዎች ጡዘት ግቡ “ደስታ” ነው ቢባልም በውስጥ ውስጠኛው አንተ ውስጥ ያለውን የዘለለት ሐሴትን ግን አይተካም… ስትፈልግ የኖርከው ያለህን ግን ደግሞ ያላየኸውን ነው ማለት ነው…

በአልማዝና በከበሩ እንቁዎች የተሞላ ሳጥን ላይ ቁጭ ብሎ እርጥባን እንደመልቀም መሆኑ ነው…

፫. There is the cessation of suffering…

ድቁሳት ምን ቢከብድ… ፈተና ምን ቢረቅ… የሆነ ጊዜ ያበቃል… ይተናል… ይበናል… የ Impermanence ህግ እንዲህ ይላል… “All that is subject to arising is subject to ceasing.” ስለዚህ ድቁሳትን በመሸሽ አታመልጠውም… ለተፈጥሮአዊ ሞቱ ትተወዋለህ እንጂ…

የድቁሳትህ ምንጮች ‘መጥፎ’ የምትላቸው ነገሮች ብቻ አይደሉም… ‘ጥሩ’ ነገሮችህም ሁነኛ ማደሪያ ናቸው… ድቁሳት ከነገሩ ተፈጥሮ ይልቅ ለጉዳዩ ካለን ጥልቅ ዝማሜ ግዘፍ ይነሳል…

ሁሌም ቢሆን ከሁነቶች ጋር የመቋጠር ቅኝት አለን… ቅርፃውያን ስለሆንን ከደስታችን ቅዥትና ከሃዘናችን ጥላ ጋር ‘የዘላለሜነሽ’ ሕብረ ዜማ እናረግዳለን… Attachment (ከነገሮች ጋር መጣመር) ክፉ ነገር ነው… ከሚያልፍ ነገር መቋለፍ ደግሞ የበለጠ አደገኛ … በውድቀት ስኬት ከፍ ዝቅ መኳተንና በወዲያ ወዲህ ፔንዱለማዊ ስሌት መዋለል የመቋለፍ ውጤት ነው… ነገሮችን እንደአመጣጣቸው ተቀብሎ የሚሸኝ ግና በጊዜያዊ ደስታ ከመስከርና በሚያልፍ ሃዘን ከመሰበር ይድናል… የወንዙን አወራረድ ለማየት ሁነኛው ቦታ የወንዙ አፋፍ ነው… እዚያ ነው የ’ሁሉም ያልፋል’ ጥበብ የሚወለደው…

ለስሜት ስብራት የሚገፉኝን ሁኔታዎች በትኩረት መመልከት ስጀምር የሚገባኝ አሃዱ የትስስሬ ጥልቀት ነው… ድብርት ውስጥ ስገኝ… ብቻነት ሲሰማኝ… እጦት ሲያንገበግበኝ… ዕድሜ ከሌላቸው ነገሮች ጋር አዕምሮዬ እንደታበተ አስተውላለሁ… ለጊዜው ካበረህ ጋር ለሁልጊዜ በፍቅር መውደቅ ክፉ እርግማን ነው… ሟችን ለሞቱ ተወው…

፬. The way out of Suffering

በድቁሳት መኖር ላይ ተግባባን… ምንጭ እንዳለውም ገባን… ተፈጥሮአዊ ሞት እንደሚሞትም እንዲሁ… ከድቁሳት ነፃ መውጣትስ አይቻል ይሆን?… ይሄ የሰው ልጅ ሁሉ ጥያቄ ይመስለኛል… ቡድሐም አብርሆት ከተቀዳጀባት ዛፍ /Bodhi Tree/ የዚህን ጥያቄ መልስ ሳያገኝ አልተነሳም… አዎን ከድቁሳት ነፃ መውጣት ይቻላል… እንዴት?

ቡድሐ ‘The eightfold path’ በማለት የሰየማቸው ስምንት ‘ቀናዎች’ አሉ… ለቀናዎቹ መቅናት ከድቁሳት ነፃ ያወጣል…

RightView,
Right Intention,
Right Speech,
Right Action,
Right Livelihood,
Right Effort,
Right Mindfulness and
Right Concentration ናቸው…

ከዚህ በኋላ ደቆስቆስ የሚያደርጉህ ነገሮች ሲበረክቱ ከኒህ ስምንት ቀናዎች የትኛውን እንዳጎደልክ መርምር…

ፍቅርን ከመስጠት በላይ ዕዳ
አይኑርባችሁ!!

ምርጫችሁ ስለሆንን ስናመሰግኖት ከልብ ነው !!!
@EthioHumanity @EthioHumanity

@EthioHumanitybot