Get Mystery Box with random crypto!

ዲዛይን ቢድ ቢዩልድ(Design bid build)(DBB) VS ዲዛይን ቢዩልድ(Design build) | Ethio Construction

ዲዛይን ቢድ ቢዩልድ(Design bid build)(DBB) VS ዲዛይን ቢዩልድ(Design build)(DB)
               
1, ዲዛይን ቢድ ቢዩልድ(Design bid build)(DBB)

በኮንስትራክሽን ጉዳይ በአብዛኛው በሀገራችን የሚሰራበት የፕሮጀክት አይነት ዲዛይኑን አሰሪው በራሱ መንገድ እንዲዘጋጅ ካደረገ በኃላ ግንባታውን በተቋራጭ እንዲከናወን የሚያደርግበት ነው።ይሄውም ዲዛይን ቢድ ቢዩልድ(Design bid build)(DBB) በመባል ይታወቃል፡፡በዚህ የፕሮጀክት አይነት የታቀደውን ግንባታ ዲዛይኑን አሰሪው በራሱ አርክቴክት ወይም በሌላ ሶስተኛ ወገን/ በሌላ አርክቴክት ድርጅት/ እንዲከናወን ያደርጋል፡፡
በመቀጠልም በተዘጋጀው ዲዛይን መሰረት ግንባታውን የሚያከናውን ተቋራጭ ወደመምረጥ ሂደት ይገባል፡፡የግንባታው ባለቤት የመንግስት መስሪያ ቤት የሆነ እንደሆነ ግንባታውን የሚያከናውን ተቋራጭ የመምረጡ ስራ የሚከናወነው በግዥ ህግ መሰረት ይሆናል፡፡ይሄ አይነቱ ፕሮጀክት በሀገራችን የተለመደ ነው፡፡
              

2, ዲዛይን ቢዩልድ(Design build)(DB)

በሌላ በኩል ደግሞ ተቋራጩ ዲዛይኑን እና ግንባታውን በራሱ የሚያከናውንበት የፕሮጀክት አይነትም አለ።ይሄውም ዲዛይን ቢዩልድ(Design build)(DB) ይባላል፡፡በዚህ የፕሮጀክት አይነት ተቋራጩ የታቀደውን ግንባታ ዲዛይኑን በራሱ አርክቴክት ወይም በሌላ የአርክቴክት ድርጅት አማካይነት ያከናውናል፡፡የአርክቴክት ስራው የሚያስከትለው ሀላፊነት የተቋራጩ ይሆናል፡፡ከዲዛይን ስራው ጋር የተያያዘ ችግር የሚያስከትለው ሀላፊነት አሰሪውን/የግንባታውን ባለቤት አይነካውም፡፡ሆኖም ተቋራጩ ዲዛይኑን ያሰራው በሌላ የአርክቴክት ድርጅት አማካይነት የሆነ እንደሆነ ከአርክቴክቸር ስራው ጋር በተያያዘ ተቋራጩ ለአሰሪው የሚኖርበት ሀላፊነት እንደተጠበቀ ሆኖ አርክቴክቱም ለተቋራጩ በፍትሀብሄር ህጉ ስለእውቀት ስራ ውል በተደነገገው አግባብ ሀላፊነት ይኖርበታል ማለት ነው፡፡
በዚህ አይነት ፕሮጀክት የግንባታው ባለቤት/አሰሪው ሙሉ በሙሉ የኮንስትራክሽን ስጋቶችን/risks/ ወደ ተቋራጩ ያስተላልፋል፡፡ይህ ማለት አሰሪው ውጤቱን ማለትም ግንባታውን በመጀመሪያ በቀረበለት ዲዛይን አግባብ በጥራት ተከናውኖለት ከመረከብና በውሉ የተቀመጠውን የግንባታ ዋጋ ከመክፈል ባለፈ ማናቸውም አይነት ሀላፊነት አይኖርበትም ማለት ነው፡፡ለአብነት ለመጥቀስ ያህል የኢትዮጽያ መንገዶች ባለስልጣን(ERA) ዲዛይን ቢዩልድ የመንገድ ፕሮጀክት ሲኖረው ተወዳዳሪ ተቋራጮች የሰርቨየይንግና ዲዛይን ስራዎችን በራሳቸው ከሰሩ በኋላ በዋጋ ይወዳደራሉ፡፡ተቋራጮቹ ዲዛይኑን ሲሰሩ አሮጌ ድልድዮች ካሉ እና ተጠግነው በአዲስ ድልድይ የጥራት ደረጃ መድረስ የሚችሉ ከሆነ ተቋራጮች እንደየፍላጐታቸውና ሙያዊ ምርመራቸው/ምክንያታቸው ተጠጋኝ ድልድይ እና በአዲስ የሚገነባ ድልድይ እያሉ በዝርዝር በዲዛይን አካተው የሚያቀርቡ ሲሆን ምንም ሆነ ምን በውጤት ደረጃ አሰሪው በሚፈልገው የጥራት ደረጃ/ስታንዳርድ መገንባቱ እና ይሄውም በአማካሪው መረጋገጡ ግን የግድ ነው፡፡ምናልባት ተጠግኖ በሚፈለገው የጥራት ደረጃ ይደርሳል የተባለው አሮጌ ድልድይ በጥገና ወቅት ቢፈርስ እንኳ አሰሪውን ክፍያ የመጨመር ሀላፊነት አያስከትልበትም፡፡ስለዚህ ዲዛይን ቢዩልድ ፕሮጀክት ለአሰሪዎች ሪስክ ፍሪ/ከስጋት ነጻ የሆነ የፕሮጀክት አይነት ነው፡፡
           
ሌላው ሁለቱም የፕሮጀክት አይነቶች ለኮንስትራክሽን ውላቸው የሚጠቀሙት ጀኔራል ኮንዲሽን የተለያየ ነው።FIDIC በዚህ ረገድ የግንባታ ውል ዝግጅትን በማቅለል ለአለማችን ትልቅ ስጦታ ነው። አለበለዚያ አሰሪና ተቋራጭ በየአንዳንዱ ውል ዝግጅት ወቅት በሁሉም የውል ሁኔታወች ላይ መደራደርን ይጠይቃቸው ነበር።ዛሬ ላይ ግን ለውሉ ጥቅም ላይ የሚውለውን ጀኔራል ኮንዲሽን አስመልክቶ FIDIC ቨርሽን መረጣ እና በስፔሻል ኮንዲሽን ኦፍ ኮንትራክት በሚካተቱ ነጥቦች ላይ ብቻ መወያየት በቂ ነው።

በተጨማሪም በዲዛይን ቢዩልድ ፕሮጀክት የኮንስትራክሽን ስጋት/ሪስክ ሙሉ በሙሉ ወደ ተቋራጩ የሚተላለፍ በመሆኑ ልዩ የዋስትና ሽፋን ያስፈልገዋል፡፡ስለዚሁም ተቋራጩ በግንባታው ዋጋ ልክ All risk insurance እንዲገባ እና ለዲዛይን ስህተት፣ለስራው ብልሽትና በተቋራጩ ባለሙያወች የስራ ስህተት ለሚከሰት ጉዳትና ኪሳራ ደግሞ professional indemenity insurance እንዲገባ FIDIC ዲዛይን ቢዩልድ ፕሮጀክት ኮምፖቴብል የሆነው ተርንኪ ጀኔራል ኮንዲሽን ግዴታ ያስቀምጣል።

በሀገራችን ዲዛይን ቢዩልድ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ብዙም የተለመደ አይደለም።ሆኖም በመንገድ ግንባታ ውሎች የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አልፎ አልፎ ይጠቀምበታል።
በአጠቃላይ በሀገራችን በኮንሰትራክሽን ዲዛይኒንግ እና የውል አስተዳደር ረገድ ሰፊ የእውቀት ክፍተት ያለ በመሆኑ እና ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና ገንዘብ የማይጠናቀቁበት ሁኔታ በሰፊው የሚስተዋል እንደመሆኑ ሙሉ የኮንስትራክሽን ሪስክ/ስጋት ወደ ተቋራጩ በማስተላለፍ  መንግስታዊ ግንባታዎችን በዲዛይን ቢዩልድ የፕሮጀክት አይነት እንዲከናወኑ ማድረግ የተሻለ አማራጭ ሊሆን እንደሚችል ለመጠቆም እወዳለሁ።
                

@ethioengineers1