Get Mystery Box with random crypto!

ተቋራጮችን ከመንግስት ግዢ አቅራቢዎች ዝርዝር ማገድ [Suspension from Suppliers | Ethio Construction

ተቋራጮችን ከመንግስት ግዢ አቅራቢዎች ዝርዝር ማገድ

[Suspension from Suppliers List]

በመንግስት ግዢ ወቅት በሚፈፀሙ የስነ-ስርዓት ግድፈቶች ምክንያት ጥቅሜ ተነክቶብኛል የሚል አቅራቢ ወይም ተጫራች ለግዢ ፈፃሚው የመንግስት አካል ወይም ለአቤቱታ አጣሪው ቦርድ አቤቱታ የማቅረብ መብት እንዳለው የአዋጁ አንቀፅ 70(1) እንዲሁም የመመሪያው አንቀፅ 43 ይገልፃሉ፡፡ ነገር ግን አቤቱታ የማይቀርብባቸው ጉዳዮችም እንዳሉ አንቀፅ 70(2) እና 44 በዝርዝር ያስቀምጣሉ፡፡

ነገር ግን የዚህ ፅሁፍ አላማ በግዢ ፈፃሚ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ለኤጀንሲው በሚያቀርቡት አቤቱታ ላይ ተመሰረቶ ኤጀንሲው ተቋራጮችን ከተጫራቾች ወይም ከአቅራቢዎች ዝርዝር ሊያግድ ስለሚችልበት ሁኔታዎች ለመወያየት ስለሆነ ተጫራቾች ስለሚያቀርቡት አቤቱታ እና ስለአፈታት ስርዓቱ በሌላ ፅሁፍ እመለስበታለው፡፡

የግዢ ፈፃሚ የመንግስት መስሪያ ቤት በተጫራቾች ወይም በአቅራቢዎች ሕገ-ወጥ ተግባር ወይም ሕጋዊ ጥቅሜን የሚነካ ተግባር ተፈፅሞብኛል ብሎ ሲያምን በአዋጁ አነቀፅ 12 መሰረት ለተቋቋመው የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ አቤቱታውን ማቅረብ እንደሚችል አንቀፅ 76(1) እንዲሁም የመመሪያው አንቀፅ 48(1) ይደነግጋሉ::

አንቀፅ 15(7) በዕጩ ተወዳዳሪዎችና በአውራቢዎች ላይ የመ/ቤቶች የሚያቀርቡትን አቤቱታዎች መርምሮ ውሳኔ መስጠት የኤጀንሲው አንዱ ተግባር መሆኑን ይገልፃል፡፡

በዚህም መሰረት ኢጀንሲው አቤቱታ ሲቀርብለት አቤቱታ ለቀረበበት ወይም ለተከሳሽ ዕጩ ተወዳዳሪ ወይም አቅራቢ አቤቱታ መቅረቡንና የአቤቱታዉን ይዘት የሚገልፅ ማስጠንቀቂያ በመላክ ያሳውቃል፡፡ ይህም የተከሳሽ በአስተዳደር ዉሳኔ አሰጣጥ ላይ የመሰማት መብቱን እነዲጠበቅ ይረዳል፡፡ ይህ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ የደረሰው ‹ተከሳሽም› በ5 የስራቀናት ውስጥ የፅሁፍ መልሱንና የሰነድ ማስረጃዎችን ለኤጀንሲው ማስገባት እንዳለበት ከመመሪያው አንቀፅ 48.3 ንባብ መረዳት ይቻላል፡፡

ኤጀንሲውም አቤቱታውን በተቀበለ በ15 የስራ ቀናት ውስጥ መርምሮ ውሳኔ በመስጠት ለተከራካሪዎቹ በፅሁፍ ማሳወቅ እንዳለበት የአዋጁ አንቀፅ 76(4) ከመመሪያው አንቀፅ 48.4 ጋር ይገልፃሉ፡፡ ለአቤቱታውም ሊሰጡ የሚችሉት ዉሳኔዎች አቤቱታውን ውድቅ ማድረግ፤ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ መስጠት፤ ወይም ዕጩ ተወዳዳሪውን ወይም አቅራቢውን በመንግስት ግዢ ላይ እንዳይሳተፍ ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ከተወዳዳሪነት ወይም ከአቅራቢነት ማገድ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ስለዚህ ተቋራጮች በቀረበባቸው አቤቱተታ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ በማንኛውም የመንግስት ጨረታ ላይ እንዳይወዳደሩ ሊታገዱ ይችላሉ ማለት ነው፡፡

ተጫራቾች ከማንኛውም የጨረታ ውድድር ሲታገዱ በተለምዶ በጥቁር መዝገብ ወይም “Black List” ውስጥ ገቡ ይባላል፡፡ ዋናው ነገር ደግሞ ምን ምን ዓይነት ጥፋቶች ናቸው ተጫራቾችን በጥቁር መዝገብ እንዲገቡ የሚያደርጓቸው? የሚለው ነው፡፡

እነዚህም ነጥቦች በመመሪያው አንቀፅ 48.5.1 እና 48.5.2 ላይ በዝርዝር ተቀምተጠዋል፡፡ በአንቀፅ 48.5.1 እንደተዘረዘሩትም የጨረታ ግምገማውን ውጤት ለማበላሸት ወይም ለመለወጥ አስበው ለግዢ ሰራተኞች ሙስና መስጠት፤ የውሸት ወይም ተቀባይነት የሌላቸውን መረጃዎች በማቅረብ ማጭበርበር፤ የኤጀንሲው እግድ እያለባቸው በግዢ ላይ መሳተፍ/መወዳደር እንዲሁም ተጫራቾች ወይም አቀራቢዎች በዉሉ ከተገለፀው ጥራት የወረደ ዕቃ፤ ስራ፤ ወይም አገልግሎት በማጭበርበር ወይም ከገዢ ሰራተኞች/ባለስልጣናት ጋር በመመሳጠር ያቀረቡ እንደሆነ ኤጀነሲው ከሁለት ዓመት ጀምሮ እስካልተወሰነ ጊዜ ድረስ በማንኛውም የመንግስት ግዢ ላይ እንዳይሳተፉ ሊያግዳቸው ይችላል::

ከእነዚህም ምክንያቶች በተጨማሪ ተጫራቾች ፍትሃዊ የዋጋ ወድድር ጥቅምን ለማሳጣት ከተወሰኑ ተጫራቾች ጋር በመመሳጠር የዋጋ ተመን ካወጡ/ከጣሉ፤ የግዢ ባለሙያዎች ወይም የግዢ ፈፃሚ መንግስት መ/ቤት ሰራተኞች ላይ የአካል ጉዳት ለማድረስ የዛተ/ያስፈራራ ወይም ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ ወይም በኤጀነሲው የተጣለበት እግድ ከተነሳበት ቀን ጀምሮ በሁለት ዓመታት ዉስጥ ሌላ ማንኛውም ከአቅራቢዎች ዝርዝር ሊያሳግድ የሚችል ጥፋት የፈፀመ እንደሆነ በተመሳሳይ ከሁለት ዓመት ጀምሮ እስካልተወሰነ ጊዜ ድረስ ሊታገድ ይችላል ማለት ነው፡፡

በአጭሩ ሙስና፣ ማጭበርበር፣ መመሳጠር፣ ወይም ዕግድን ጥሶ በጨረታ ላይ መወዳደር ተጫራቾችን/አቅራቢዎችን ከአቅራቢነት ዝርዝር ሊያሳግዳቸው ይችላል ማለት ነው፡፡

በሌላ በኩለ ደግሞ አንቀፅ 48.5.2 ላይ እንደተገለፁት ከመንግስት ጋር የግዢ ውል የተዋዋለው አቅራቢ በዉሉ የተገለፁትን ዕቃዎች፡ ስራዎች ወይም አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ ባለማቅረቡ ምክንያት የግዢ ፈፃሚው መ/ቤት ቀጥተኛ ወይም ተዘዋዋሪ ጉዳት [Direct or Consequential Loss] ያጋጠመው እንደሆነ ወይም የመ/ቤቱን ስራ ያጓተተ ወይም ያፋለሰ እንደሆነ አቅራቢው ከአቀራቢዎች መዝገብ ላይ ከስድስት ወር እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ሊታገድ ይችላል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የጨረታ ውድድር እንዳሸነፈ በመ/ቤቱ የተገለፀለት አቅራቢ ውሉን ለመዋዋል ባለመቻሉ ወይም እምቢተኛ በመሆኑ ምክንያት መ/ቤቱ በዉሉ የተገለፀውን ዕቃ፣ ስራ ወይም አገልግሎት ከሌላ አቅራቢዎች ለመግዛት ሲል ጉዳት ያጋጠመዉ ወይም ስራዉን ያጓተተ ወይም ያፋለሰ እንደሆነ እነዲሁም የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው አቀራቢ በሶስት ዓመት ውስጥ ሌላ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ሊያስጥ የሚችል ጥፋት ፈፅሞ ከተገኘ ኤጀንሲው አቅራቢውን ከአቀራቢዎች መዝገብ ላይ ከስድስት ወር እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ሊያግደው ይችላል፡፡

ከአቀራቢዎች ዝርዝር መዝገብ ላይ ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ መታገድ ውጤቱም በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ተጫራቹ ወይም አቅራቢው በማንኛውም የመንግስት ግዢ ላይ መወዳደር አይችልም፡፡ እነዚህ በኤጀንሲው የሚጣሉት የዕግድም ይሁን የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ቅጣቶች ግዢ ፈፃሚውን የመንግስት መ/ቤት በአቅራቢው ወይም በተጫራቹ ምክንያት የደረሰበትን የገንዘብ ኪሳራ ከመጠየቅ አያግደውም፡፡Written By: Girum Getu----Assistant Lecturer @ Wolkite University; School of Law
LL.M Candidate in Construction Law and Dispute Resolution @ Bahir Dar University School of Law

https://t.me/ethioengineers1