Get Mystery Box with random crypto!

#ኸሚስ_አመሻሹ_ላይ! ዳርና ድንበር የሌለው የፍቅሩ ጥናት በሰይዱና ጃዕፈሩ ጦያር እጅጉን አይሏል | Ethio Neshida & Menzuma

#ኸሚስ_አመሻሹ_ላይ!

ዳርና ድንበር የሌለው የፍቅሩ ጥናት በሰይዱና ጃዕፈሩ ጦያር እጅጉን አይሏል። "ጃዕፈሬዋ መልክህም ባህሪህም እኔን መሰለ‘ኮ" ተብለው ተለክፈዋል። እንደ ልጃገረድ ብሎም እንደ ኮረዳ በነቢ ፊት ዘልለው ጨፍረዋል። በደስታ ተፍነክንከዋል። ለዚህም ነው ማዲሁ "ጃዕፈሩ ጦያር ነው ሀድራን የጀመረው" ሲሉ ያሞካሿቸው። ደግሞም በሀድራ መዘንበሉን ሱና ብለው በሰነድ ከእርሳቸው ቀድተዋል።

የኢስላምን ባንዲራ በዘመቻ አንግበዋል። በነብዬ ትዕዛዝ የዱንያን ጣዕም ቆርጠዋል። ጀነትን ናፍቀው ተሰደዋል። እለቱን ፆመኛ ሆነው በነብዩ ትዕዛዝ ባንዲራ አንግበው ፍልሚያ ወጥተዋል። የቻሉትን ያህል ጠላት ቀልተዋል። ወደ ፊት ገስግሰዋል። ወደ ኋላ አልዞሩም። በዚህ ጀግንነታቸው ሆነው ቀኝ እጃቸውን አጡ። ባንዲራው ከእጃቸው ሲወድቅ ወዲያውኑ በግራ እጃቸው ያዙት። አሁንም የግራ እጃቸውን ቆርጠው በባንዲራው መውደቅ የኢስላምን መጥፋት ሊያውጁ ዋጁ። ግና ሰይዲ ጃዕፈር የነቢ ትዕዛዝ "ጃዕፈር ፅና!" እያለ በጆሯቸው ሲንቆረቆር በረቱ። የጀግንነት ውሏቸውን በሽንፈት ማስፃፍ አልከጀሉም ፣ ነብዬም ጋር እንዲህ ባለው ሀል መወሳት አልሻቱምና በተቆረጡ እጆቻቸው ባንዲራውን አነገቡ። ወደፊት ቀጠሉ። 80 ቀስት እና ጦር በደረታቸው አስተደናገዱ። ይህ ሲሆን ጊዜ መሬት ላይ ወድቀው ባልደረቦቻቸው መጡ። ውሃ አቀረቡላቸው ግና ፆመኛ መሆናቸውን ገለፁ። በዚያው እለት ወደ አኼራ ሐጀሩ። ነብዬን ተሰናብተው ተጉዘው በዚያው ቀሩ።

ግና አፍታም አልቆዩም። ናፍቆት በረታባቸውና ከመላኢካዎች ጋር ሆነው ወደ ነብዬ ተጓዙ። ከሀገር ወደ ሀገር ሳይሆን ከበርዘኽ ወደ ዱንያ አመሩ። ከማይታሰበው ዓለም በሩሀቸው ወደ ናፈቋቸው ነብይ አቀኑ። በጀነት ያለውን ኒዕማ ሁሉ ሲያዩ ነብዬ ቢታወሷቸው ነው‘ኮ! ነብዬ ቀና ብለው ወደ ዳመናው "የጌታዬ ሰላም በእናንተም ላይ ይሁን" አሉ። ሶሀባዎች ግራ ገባቸው እና ጠየቁ። እርሳቸውም "ይህ ጃዕፈር ኢብኑ አቡጧሊብ ነው። ከተወሰኑ መላኢካዎች ጋር እኔን ሊዘይሩ መጥተዋል። እጆቹንም አሏህ በክንፎች ለውጦለት በጀነት ውስጥ ይበርራል" ብለው ነገሯቸው። ይህ ነው የናፍቆት ጥናት። ሀያል የመግነጢስ ስበት። ከዓለም ወደ ሌላ ዓለም የሚጎትት። ከጀነት ኒዓም በልጦ ወደ ምድር የሚመልስ።

#ሶሉ_ዓለል_ሐቢብ!
አሏሁመሶሊ ወሰሊም ወባሪክ ዓላ ሰይዲና ወመውላና ሙሐመድ ወዓላ አሊሂ ወሶህቢሂ ወሰለም!
Atiqa Ahmed Ali