Get Mystery Box with random crypto!

#ኸሚስ_አመሻሹ_ላይ! የታመመ ሀኪሙን ይከጅላል። የተራበ ቀላቢውን ይሻል። የተጠማ የውሃ ጉድጓዱን | Ethio Neshida & Menzuma

#ኸሚስ_አመሻሹ_ላይ!

የታመመ ሀኪሙን ይከጅላል። የተራበ ቀላቢውን ይሻል። የተጠማ የውሃ ጉድጓዱን ይምሳል። የጨለመው ኩራዙን ይለኩሳል። ያፈቀረ ተፈቃሪውን ያሳድዳል። እንዲህ ሆነና አንድ ዕለት ሰይዳችን ከመስጂዳቸው ጎራ ብለው ፀጉራቸውን ሊላጩ ተቀመጡ። ለዚህ የታደለ ሰው ፀጉራቸውን ሊቆርጥ ተሰየመ። ሶሀቦች ሁሉ ታደሙ። አፍጥጠው መጠባበቅ ጀመሩ። ለዘመናት ያልሙት የነበረ ይመስላል። ነብር ታዳኟን አሰፍስፋ የምትጠብቀውን ያህል እነርሱም የረሱልዬን ፀጉር ይጠባበቁ ጀመረ። ሁሉም ለራሱ ከጅሎታል። ሰይዲ ይህንን ጉጉታቸውን ያስተውላሉ። በእያንዳንዱ የፀጉር ዘለላቸው ላይ የተለያዬ ምስጢር አደረጉበት። ለእያንዳንዱ ሶሀባ ነሲቡን ከፈሉለት።

ፀጉር ቆራጩ ሲጨርስ ሰይዲዋ "በሶሀቦቼ መሀል አከፋፍለው" ሲሉ። አዘዙት። ሶሀባው ሁሉ መሻማት ጀመረ። አንድ ዘለላ ፣ ሁለት ዘለላ አንዳንዱ ከዚያም በላይ የደረሰው ነበረ። ከፊሉ ያሸተው ጀመረ። እኩሌታውም ይስመዋል። ሌላው እያየው ያነባል። በተወደደ እቃ ላይ አስቀምጠውታል። ይህንን ሁኔታ ከሩቅ ሆነው ሰይዱና አቡበክር ይመለከታሉ። ከነዚህ ውስጥ እጅግ አስደናቂ ነገር ተመለከቱ። ቀልባቸውን ገዝቷቸውል። በእርግጥ የአሏህ ስራ እያስገረማቸው ነው። የነብዪ የፍቅር መግነጢሳዊ ሀይል እያደነጋገራቸው ነው። ከእነዚያ ፀጉሩን ከሚሻሙት ሶሀባዎች መሀል አንዱ ሱሀይል ቢን አምር ሆኖ ተመለከቱት። አንድ ፀጉር ሲደርሰው ወዲያውኑ ወደ ዓይኑ አስጠግቶት ተንሰቀሰቀ። ይህንን በተመለከቱ ጊዜ እጅግ አለቀሱ። ቀልባቸውን አንከላወሱ። ምላሳቸውን አላወሱ።

"ትላንት ላይ በሁደይቢያ ስምምነት የነብዩን መልእክተኝነት መቀበል ተስኖት ስማቸውን ከነ ማዕረጋቸው ለመፃፍ የተፀየፈው ሱሀይል ዛሬ ከሶሀቦቻቸው ጎራ ሆኖ በፍቅራቸው ይገረፋል።" አሉ። በእርግጥ መድሀኒቱን አግኝቶ ነው። ለዘመናት የታመመውን ህመም ያሻሩለትን ሀኪሙን አፍቅሮ ነው። ትላንት ሊዋጋቸው ያሰፈሰፈ ሰው ዛሬ ነፍሱን ሊሰጣቸው ተማርኮ ነው። የፍቅር ማዕበል ተማቶት ነው። ከዚህ የበለጠ የፍቅር ምች አላስተዋልንም። የለይላ እና መጅኑንን ታሪክ አልናቅንም ሆኖም እጅጉን የበለጠው አለ። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ሰው ሰውን ሲያፈቅር ሶሀባዎች ነብዩን ሲወዱ አየን። በጆሮ የሰማነውን ታድመን ያየን ያህል ተማርከን በልባችን አመንን። አንድ እናክልና የበለጠ እንተዓጀብ!
ሰይዱና ኻሊድ ቢን ወሊድ በአንድ ዘመቻ ከጦር ቆባቸው ውስጥ ያስቀመጡት የሰይዲ ፀጉር ከቆባቸው ጋር ይጠፋባቸዋል። በተፋፋመ ጦር፣ በተጋጋመ ውጊያ ውስጥ ሆነው ባዘኑ። ትዕዛዝ ለጓዶቻቸው አስተላለፉ። ፈልገው ያመጡላቸው ዘንድ አዘዙ። እስኪመጣላቸው ድረስ ታመሙ፣ በጠና ደከሙ። በማይወጡት ለቅሶ ተዋጡ። ጓዶቻቸው ፈልገው አገኙና አመጡላቸው። እርሳቸውም ተደስተው ፈገግ አሉ። "ይህንን ፀጉር ከእኔ ጋር ይዤ በተገኘሁበት ዘመቻ ሁሉ ድል የእኔ ነበረ" ሲሉ ተናገሩ። ህመማቸውን ተፈወሱ። ሀዘናቸውን ተካሱ። ይህ ነው የፍቅር ህክምናው።

#ሶሉ_ዓለል_ሐቢብ!
አሏሁመሶሊ ወሰሊም ወባሪክ ዓላ ሰይዲና ወመውላና ሙሐመድ ወዓላ አሊሂ ወሶህቢሂ ወሰለም!
Atiqa Ahmed Ali