Get Mystery Box with random crypto!

#ኸሚስ_አመሻሹ_ላይ! የመካ መኳንንት ግፍ በነብዩ ሶለሏሁ ዓለይሂ ወሰለም እና ባልደረቦቻቸው ላይ | Ethio Neshida & Menzuma

#ኸሚስ_አመሻሹ_ላይ!

የመካ መኳንንት ግፍ በነብዩ ሶለሏሁ ዓለይሂ ወሰለም እና ባልደረቦቻቸው ላይ በርትቷል። ዱላ እና ግርፋቱ ያለማባራት እየዘነበ ነው። ያኔ ነብያችን ባልደረቦቻቸውን ከሀበሻ ቀጥሎ ወደ መዲና ይጓዙ ዘንድ አዘዙ። ትዕዛዛቸውም ተፈፀመ። በመዲና የሰፈሩት ሶሀቦች "ሙሐጂር" ተሰኙ። ታዲያ ከእነዚህ ሙሐጂሮች አንዱ የነብያችን ወዳጅ ፣ አጎት እና የጥቢ ወንድም የሆኑት ሰይዱና ሐምዛ (ረ.ዐ) ነበሩ። እንዲያ ከሚሳሱላቸው ተወዳጅ ሠው ተለይተው በመዲና መቀመጣቸው አክስቷቸዋል፣ በጀግንነት ጀብዳቸው ላይ የናፍቆት ካባ ተደርቦ ሸፍኖባቸዋል፤ እጅጉን በናፍቆት ይንከላወሳሉ። ሌት ተቀን ከመዲና ሰዎች እና ሶሀቦች ጋር በመሆን የመዲናን መግቢያ ተራሮች ያማትራሉ። ነብያችንን ናፍቀው ዛፍ እና ቆጡን እየወጡ ይጠባበቃሉ። ጊዜው ራቀባቸው።

ይህ የሰይዱና ሐምዛ ፍቅር በዓይናቸው ባላዯቸው የመዲና ነዋሪዎችም ላይ በርትቶ ታይቷል። "የአሏህ መልዕክተኛ አለ" ተብሎ ተነገራቸው እንጂ በዓይናቸው አልተመለከቷቸውም ፣ ውብ እጆቻቸውን አልዳበሷቸውም ፣ ጨረቃ መልካቸውን አላዩም ፣ ጣፋጭ ንግግሮቻቸውን አላደመጡም። ይህም ሆኖ የፀሀይን መውጣት ተከትሎ ቀድመው የከተማዋ ጫፍ ላይ በመውጣት ይጠብቋቸው ነበረ። በእንዲህ ያለ ሁኔታ በሰኞ ቀትር ላይ ከሩቁ ሁለት ሰዎች የመዲናን ጎራ እያቆራረጡ ብቅ ሲሉ አንድ የመዲና አይሁድ ወጣት ይመለከታል። ናፋቂዎቹ ፀሀዩ ስለበረታባቸው ወደየቤታቸው እየተመለሱ ነበረ። በዚህ ጊዜ "እናንተ የቂላህ ልጆች ሆይ! በጉጉት ስትጠብቁት የነበረው ነብይ መጥቶላችኋል" እያለ ጮኸ። አንድ ወጣት አማኝም ድምፁን ከፍ አደረገና

"ها هو الرسول. اقبل الهادي البشير"
"እኚያው የአሏህ መልእከተኛ ፣ ቀጥተኛውን መንገድ አመላካቹ እና በመልካም አብሳሪው ነብይ መጡ" ሲል አዋጁን አወጀ። ታዲያ ይህ ወጣት ነብያችን የትኛው ፣ ሰይዲና አቡበክርም የትኛው እንደሆኑ አያውቅም ነበር። ግና ምፃታቸው በራሱ አንዳች የፍቅር መግነጢስ አሳረፈበትና በፍቅር ጥሪ ይጣራ ዘንድ ሳበው። እነዚያ ሳያዯቸው የናፈቋቸው ሰዎች በፍጥነት ወደ እርሳቸው ይገሰግሱ ጀመረ ፣ ሰይዳችንም ወደእነርሱ መጠጋታቸውን አፈጠኑት። ሰይዱና አቡበክር የፀሀዩን ሀሩር ሊከላከሉላቸው ሰይዳችንን በካባቸው አስጠልለዋል። በዚህ ነበረ ጉጉዎቹ የመዲና ሰዎች የሰይዳችንን እና የሰይድ አቡበክርን ማንነት ለይተው ለማወቅ የቻሉት። ሁሉም ወደ ነቢ ተጠጋ። ሰይዱና ሐምዛ ተጠግተው የናፍቆት ጥማቸውን በእቅፍ ጠጅ አረገቡት።

አንሷር ከሙሐጂር በአንድነት ተቀኝተው
طلع البدر علينا
እያሉ አሞገሷቸው። እርግጥም በዚያ ጠራራ ፀሀይ ውብ ጨረቃ ተፈልቅቃ መዲና ላይ ዘልቃለች። በእልልታ ተቀበሏቸው። ናፍቆታቸውን አቀዘቀዙ። በፍቅር ተገርፈው ፣ በናፍቆት ታስረው ከርመው በእይታ ታከሙ፣ በሰላምታ ተፈወሱ።
እጅግ ናፍቆት፣ እጅግ ፍቅር፣ ፍቅር ይህ ነው። ሳያዩ መናፈቅ።

#ሶሉ_ዓለል_ሐቢብ!
አሏሁመሶሊ ወሰሊም ወባሪክ ዓላ ሰይዲና ወመውላና ሙሐመድ ወዓላ አሊሂ ወሶህቢሂ ወሰለም!
Atiqa Ahmed Ali