Get Mystery Box with random crypto!

ጃዋር መሀመድ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ አምባሰደርን የሰላም ጥሪ ማውገዙ አሳዛኝ | ETHIO-MEREJA®

ጃዋር መሀመድ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ አምባሰደርን የሰላም ጥሪ ማውገዙ አሳዛኝ ነው አሉ!

የአሜሪካ በኢትዮጵያ አምባሳደር አርቪን ማሲንጋ “የሰጡትን ሃቀኛ እና ድፍረት የተሞላበት መግለጫ” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማውገዙ ግራ የሚያጋባ እና አሳዛኝ ነው ሲሉ አንጋፋው ፖለቲከኛ ጃዋር መሀመድ ገለጹ።

ጃዋር መሀመድ ዛሬ በይፋዊ ፌስቡክ ገጻቸው ላይ አምባሳደሩ የሰጡትን መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት ይቀበለዋል ተብሎ የሚጠበቅ ባይሆንም አምባሳደሩ “በተለመደ ዲፕሎማሲያዊ ንግግር ሳይሸፋፍን ይልቁንም የአገር እውነተኛ ወዳጅ ማድረግ እንዳለበት ሁሉ በግልፅ እና በፍትሃዊነት ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች የፖለቲካ ግጭቶችን በትጥቅ ሃይል ለመፍታት የሚያደርጓቸውን አውዳሚ እና የተሳሳተ ሙከራ እንዲተዉ” መጠየቃቸውን አስፍረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትላንትናው ዕለት አምባሳደር አርቪን ማሲንጋ በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ ያቀረቡት መግለጫ በሕዝብ የተመረጠን መንግስት ለመገልበጥ የተነሱ ቡድኖችን በመዘርዘር መንግስት እንዴት አገሪቷን መምራት እንዳለበት የሚገልጽ ያልተገባ ምክርን ያዘለ ነው” ሲል ተቃውሞታል።

የአምባሳደሩ መግለጫ “ያልተረጋገጡ መረጃዎች ያሉትና የሁለቱን አገራት ግንኙነት የሚጻረር መሆኑን የገለጸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “ስህተቶች እንዲታረሙ” ከኤምባሲው ጋር በቅርበት እንደሚሰራ በመግለጫው ገልጿል።

መንግስት ተቃዋሚዎቹን በወታደራዊ መንገድ ለማጥፋት ወደመሞከር የተመለሰ ሲሆን ይህ የተሞከረ እና ያልተሳካለት ስልት ባለፉት ዓመታት አገሪቱን አውድሟል ሲሉ ፖለቲከኛው ጃዋር ገልጸዋል።

በሰላማዊ መንገድ የተገኘውን ውጤት ከማጠናከር ይልቅ ከፍተኛ ወታደራዊ እና የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎችን መንግስት እያደረገ፤ ከዚሁ ጎን ለጎን ገዢው ፓርቲ የፖለቲካ ምህዳሩን ዋስትና በማስጠበቅ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ ጀምሯል በማለትም አክለዋል።

በቅርቡ በነቀምት እና በባህር ዳር በተደረጉት የድጋፍ ሰልፎች ላይ ከተናገሩት በተቃራኒ በአብዛኛው የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች እየተስፋፉ እንጂ እየቀነሱ አይደሉም ያሉት ጃዋር መሀመድ፤ መከላከያ ሠራዊት በአንዳንድ አካባቢዎች ጥሩ ውጤት ያስመዘገበ ቢሆንም፣ “ስለ ታጣቂዎች የጅምላ መክዳት በተመለከተ የቅርብ ጊዜ ዘገባዎች በጣም የተጋነኑ እና አንዳንዶቹ ፍጹም የፈጠራ ወሬዎች ናቸው” በማለት ጽፈዋል።

አብዛኛዎቹ ዞኖች እና ወረዳዎች በመንገድ አለመገናኘታቸው ማሳያው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአየር ጉዞው በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር እንደሆነ የጠቀሱት ፖለቲከኛው ጃዋር፤ ገበሬዎች ማዳበሪያ መቀበልም ሆነ ሰብል መትከል አይችሉም፣ በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለው አፈና እና ሕግ-ወጥ ግድያ ህይወትን በገጠሩ ሕዝብ ላይ መቋቋም የማይቻል አድርጎታል ብለዋል።

     T.me/ethio_mereja
           ኢትዮ-መረጃ