Get Mystery Box with random crypto!

29 ሺሕ ዜጎች ከራያ እና አላማጣ አካባቢዎች መፈናቀላቸውን ተገለጸ ከሰሞኑ በትግራይ እና አማራ | ETHIO-MEREJA®

29 ሺሕ ዜጎች ከራያ እና አላማጣ አካባቢዎች መፈናቀላቸውን ተገለጸ

ከሰሞኑ በትግራይ እና አማራ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ላይ ባገረሸው ግጭት ምክንያት፤ 29 ሺሕ ዜጎች ከራያ እና አላማጣ አካባቢዎች መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት (ኦቻ) አስታውቋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት (ኦቻ) ትናንት ሚያዝያ 11/2016 ባወጣው ሪፖርት፤ በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉት ዜጎች በቆቦ፣ ሰሜን ወሎ እና ሰቆጣ ከተማ በሚገኙ መጠለያዎች ላይ ተጠልለው እንደሚገኙ ገልጿል፡፡

ከተፈናቀሉት 29 ሺሕ ዜጎች ውስጥ 70 በመቶዎቹ ሕጻናት እና ሴቶች ሲሆኑ፤ ቀሪዎቹ አዛውንቶች እና ታዳጊዎች ናቸው ያለው ሪፖርቱ፤ ከአጠቃላይ ተፈናቃዮች ውስጥ 23 ሺሕ የሚሆኑት ቆቦ ቀሪዎቹ 5 ሺሕ 980 የሚሆኑት ደግሞ ሰቆጣ ከተማ ተጠልለው እንደሚገኙ ገልጿል።

በአካባቢው ያለው ሁኔታ አሁንም ያልተረጋጋ በመሆኑ ተጨማሪ ዜጎች ሊፈናቀሉ ይችላሉ ያለው ጽ/ቤቱ፤ አሁን ላይ ለተፈናቃሉ ዜጎች ውሃ፣ ምግብ እና ሌሎች ሕይወት ማቆያ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።

ነገር ግን ለተፈናቃዮቹ የሚቀርበው የምግብ እና ውሃ እጥረት አሳሳቢ መሆኑን በመግለጽ፤ ተፈናቃዮቹ አፋጣኝ የነፍስ አድን እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አመላክቷል።

በተጨማሪም ለጋሽ አገራትና አጋር ተቋማት የሚያደርጉት ድጋፍ ውስን በመሆኑ፤ አሁን ላይ በአካባቢው ያለው ማህበረሰብ ለተጎዱ ተፈናቃዮች የሚችለውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል።

ኦቻ ለተፈናቃዮቹ በተለይም መጠለያ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችና የሕክምና አገልግሎት በአፋጣኝ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ያሳሰበ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ አደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚሽን ሰራተኞች ጉዳዩን ለመከታተል ሚያዚያ 11 ቀን 2016 ወደ ስፍራው ማቅናታቸውንም ገልጿል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት የትግራይ እና አማራ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሱባቸው የራያ አካባቢ ዳግም ግጭት መቀስቀሱ የሚታወስ ሲሆን፤ በዚህም ግጭት የህወሃት ታጣቂዎች ወደ ራያ እና አላማጣ አካባቢዎች መምጣታቸውን ተከትሎ፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ቤታቸውን ጥለው ለመሰደድ መገደዳቸው ተገልጿል፡፡

የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎም፤ የአማራ ክልል መንግሥት "ህወሕት ለአራተኛ ጊዜ ወረራ ፈጽሞብኛል" ሲል ወቅሷል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ፤ በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ "ክሥተቱ በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ወይም በህወሓት አልያም በትግራይ እና በአማራ ክልሎች መካከል የተፈጠረ ግጭት አይደለም" ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የፌደራሉ መንግሥት በበኩሉ የይገባኛል ጥያቄ በሚነሣባቸው በእነዚህ አካባቢዎች ባለው ወቅታዊ ሁኔታ፤ ሁሉም ወገኖች ለፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት እንዲገዙና ከተንኳሽ ተግባራት እንዲቆጠቡ የጠየቀ ሲሆን፤ ሁሉም ወገኖች ካለፈው ግጭት ትምህርት መውሰድ እንዳለባቸው አሳስቧል።