Get Mystery Box with random crypto!

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ መንግሥት ኢ ሰብዓዊ አያያዝ እንዲያቆም ጥሪ አቀረበ። ኢሰመጉ | ETHIO-MEREJA®

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ መንግሥት ኢ ሰብዓዊ አያያዝ እንዲያቆም ጥሪ አቀረበ።

ኢሰመጉ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ "በታሰረበት ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ በፖሊሶች ድብደባ እንደተፈጸመበት" ማረጋገጡን አስታውቋል። ግንቦት 18 ቀን 2014 በቁጥጥር ሥር የዋለው ተመስገን በተፈጸመበት ድብደባ "በአይኑ እና በጎድን አጥንቱ ላይ ጉዳት እንደደረሰበት" የገለጸው ኢሰመጉ "የፖሊስ ጣቢያው ሀኪም በውጪ እንዲታከም የጻፉለት ቢሆንም ሊታከም እንዳልቻለ" ገልጿል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ባወጣው መግለጫ "የኢሰመጉ መርማሪ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን በታሰረበት ፖሊስ ጣቢያ ለመጎብኘት ሙከራ ባደረገበት ወቅት ተጨማሪ መረጃዎችን መሰብሰብ እንዳይችል የፖሊስ ጣቢያው ፖሊሶች ለመተባበር ፈቃደኞች አልነበሩም" ሲል ነቅፏል። የኢትዮጵያ መንግሥት "ለጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እንዲሁም በእስር ላይ ለሚገኙ በርካታ ጋዜጠኞች ህጋዊ አካሄዶችን በመከተል ፈጣን ፍትህ እንዲሰጥ" ኢሰመጉ በዛሬው መግለጫ ጥሪ አቅርቧል።

ጋዜጠኛውን የደበደቡ የፖሊስ አባላት በአስቸኳይ ተጠያቂ እንዲሆኑ የጠየቀው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ "ፖሊስ ጣቢያዎች በእስር ላይ ያሉ ሰዎች ያሏቸውን መብቶች በአግባቡ እንዲያከብሩ እንዲሁም የእስረኞች ሁኔታን መከታተል ይችሉ ዘንድ ለሰብዓዊ መብት ተቋማት ተባባሪ እንዲሆኑ" ጥሪ አቅርቧል።
T.me/ethio_mereja