Get Mystery Box with random crypto!

የፍትሕ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በዛሬው ዕለት ታስሮ በሚገኝበት ፖሊስ ጣቢያ | ETHIO-MEREJA®

የፍትሕ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በዛሬው ዕለት ታስሮ በሚገኝበት ፖሊስ ጣቢያ ድብደባ እንደተፈፀመበት ተሰምቷል!!

ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ ለዶቼ ቬለ እንደገለጸው የእስረኛ ቤተሰቦች ዛሬ ጠዋት ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ በተገኙበት ተመስገንን ለመጠየቅ ሄዶ ሲደበደብ ተመልክቷል። «ተመስገን ከዚህ በፊት እስር ቤት በነበረው ቆይታ ጆሮው ላይ ጉዳት እንደደረሰበ ይታወቃል፤ በጠያቂዎች እና በእስረኞች መካከል ያለው 10 ሜትር ገደማ የሚሆነው ርቀት ከሰዎች ጫጫታ ጋር ተዳምሮ መደማመጥ ስላላስቻለው «ትንሽ ቀረብ ቢል ቢያዋራኝ» ብሎ በትህትና ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ ሁለት ፖሊሶች ሌሎች እስረኞች እና ጠያቂዎች ባሉበት በቦክስ እና በእርግጫ መማታት ጀመሩ።» ሲልም ሁኔታው አስረድቷል።

ጋዜጠኛ ተመስገንን ደብዳቢዎቹ ፖሊሶች ይዘውት ወደ ሌላ ክፍል እንደወሰዱት እና እነሱንም ከአካባቢው እንዳባረሯቸውም ተናግሯል። ቆይቶም ቢሮ ውስጥ በቅርብ ርቀት ወንድሙን ገብቶ ማየት እንደቻለ የተናገረው ታሪኩ በዚህ ጊዜም ጋዜጠኛ ተመስገን ግራ ዓይኑ ስር አብጦ እና የለበሰው ቲሸርትም ተቀድዶ መመልከቱንም አክሎ ገልጿል። ጉዳዩን ለፖሊስ ጣቢያው ኃላፊዎች ለማስረዳት ሞክሮ እንደሁ የተጠየቀው ታሪኩ ፤ መሞከራቸውን አረጋግጦ ሆኖም የተደበደበ ወንድሙን ከማሳየበት በቀር አቤቱታቸውን ለማዳመጥ ፈቃደኛ እንዳልነበሩ ተናግሯል።

ድብደባውንም ለሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እና ለጠበቃው ማሳወቃቸውንም አመልክቷል። ጋዜጠኛ ተመስገን ግንቦት 18 ቀን 2014 ዓም አድ ዋ ድልድይ አጠገብ ከሚገኘው ቢሮው ድንገት ተወስዶ መታሰሩ ይታወሳል። ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን ምርመራው ተጣርቶ እስኪያልቅ በሚል ለግንቦት 29 ቀን 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።(ዶቼ-ቬለ)

T.me/ethio_mereja