Get Mystery Box with random crypto!

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን በተሻለ ሁኔታ ለመምራት በሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎች ዙሪያ የጋራ ውይይ | Ethiopian Construction Work Professionals - ETCONp

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን በተሻለ ሁኔታ ለመምራት በሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎች ዙሪያ የጋራ ውይይት ተደረገ

የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር፣ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ አዋጅ እና በኮንስትራክሽን ግዥና ውል አስተዳደር ረቂቅ መመሪያ ላይ ትኩረቱን ያደረገ የጋራ ውይይት በአዳማ ከተማ አካሄደ፡፡ 

በውይይት መድረኩ ላይም  የሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል አመራሮች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ የሙያ ማህበራትና ሌሎች የሚመለከታቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

መድረኩን በክብር እንግድነት ተገኝተው በንግግር የከፈቱት ክቡር ወንድሙ ሴታ (ኢ/ር) በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር፣ የመሠረተ-ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የመድረኩን መዘጋጀት አስፈላጊነት ሲገልጹ እንደተናገሩት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ወጥነት ባለው መንገድ ለመምራት ስርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ በዋናነት በህግ ማዕቀፎች ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የህግ ማዕቀፎችን ማሻሻል የመጀመሪያው ስራ እንደሆነ በማመን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ አዋጅን በረቂቅ ደረጃ ለማዘጋጀት ተችሏል ብለዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በማያያዝ የኮንስትራክሽን ግዥና ውል አስተዳደር መመሪያን በተመለከተም አስካሁን ባለው ሂደት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ወጥነት ባለው መንገድ የሚመራበት የህግ ማዕቀፍ ስላልነበረው በሀገር አቀፍ ደረጃ ኢንዱስትሪው የሚመራበት ስርዓት አልተዘረጋም ነበር፡፡

ስለሆነም ወጥና ምቹ የሆነ ሜዳ  በመፍጠር ሁሉንም ተዋንያን በእኩል ደረጃ የሚያስተናግድ የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት በማስፈለጉ የግዥና ውል አስተዳደር ረቂቅ መመሪያን ማዘጋጀት ተችሏል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም ለውይይት የቀረቡት ሠነዶች በረቂቅ ደረጃ ላይ የቀረቡ በመሆናቸው ግብኣት ለመሰብሰብና የመጨረሻ ቅርጽ ለማስያዝ ለውይይት የቀረቡ መሆናቸውን ታሳቢ በማድረግ ከተሳታፊዎች የነቃ ተሳትፎ የሚጠበቅ እንደሆነና በአፈጻጸም ሂደት ቅሬታ በማያስነሳ ሁኔታ ሠነዱን ማዳበር እንደሚያስፈልግ በመግለጽ መድረኩን በይፋ አስጀምረዋል፡፡

የእርሳቸውን የመክፈቻ ንግግር ተከትሎ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ረቂቅ አዋጅ የውይይት መነሻ ሠነድ ያቀረቡት የኮንስትራክሽንና መሠረተ-ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ወ/ሮ መዲና አህመድ በገለጻቸው እንደተናገሩት የኮንስትራክሽን ዘርፉ ሚና ትልቅ መሆኑንና በመንግስት ከፍተኛ በጀት የሚመደብለት፣ የግሉ መዋዕለ ነዋይ የሚፈስበት ዘርፍ በመሆኑ አዋጁ እናት ህግ ሆኖ እንዲያገለግል ከሁሉም የዘርፉ ተዋንያን ብዙ እንደሚጠበቅ በመግለጽ የተዘጋጀውን 9 ክፍሎች እና 86 አንቀጾች ያሉትን የረቂቅ አዋጅ ሠነድ አቅርበዋል፡፡
ከእርሳቸው በመቀጠል የኮንስትራክሽን ግዥና ውል አስተዳደር ረቂቅ መመሪያን በተመለከተ በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የዲዛይን ማኔጅመንት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ፍሬው በቀለ አቅርበዋል፡፡

አቶ ፍሬው መመሪያውን በተመለከተ ሲገልጹ እንደተናገሩት በ13 ክፍሎች ተከፍሎ የቀረበው መመሪያ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ታይቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላከውን የተሻሻለውን የግዥ አዋጅ፣ እንዲሁም በገንዘብ ሚኒስቴርና በግዥ ኤጄንሲ የወጡ የህግ ማዕቀፎችን መነሻ በማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም በቀረቡት መነሻ የውይይት ሠነዶች ላይ በመመስረት በርካታ በግብአትነት የሚያገለግሉ ሀሳብና አስተያየቶች ከተሳታፊዎች ቀርበው በዘርፉ ተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎችና መነሻ የውይይት ሠነዱን ባቀረቡት አካላት ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቶ መድረኩን በመሩት በዕለቱ የክብር እንግዳ በተሰጠ የማጠቃለያ አስተያየትና ቀጣይ አቅጣጫ መድረኩ ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡

Via ስለሺ ዘገዬ

@etconp