Get Mystery Box with random crypto!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነውን ሐላላ ኬላ ሪዞርት | Ethiopian Construction Work Professionals - ETCONp

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነውን ሐላላ ኬላ ሪዞርት መርቀው ከፈቱ።

በምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባደረጉት ንግግር በጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ አማካኝነት ከተፈጠረው ሰው ሰራሽ ሃይቅ ዳርቻ የሚገኘው የሀላላ ካብ በ'ገበታ ለሀገር' ኮይሻ ኮሪደር ፕሮጀክት አካል በሆነው ሃላላ ኬላ ሪዞርት ውስጥ ተካቶ የለማ ድንቅ የቱሪስት መስህብ ስፍራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሀላላ ኬላ ሪዞርት ከመዝናኛ ስፍራነቱ በተጨማሪ ታሪካዊና ባህላዊ ሙዚየሞችና የምርምር ማዕከላትን ያካተተ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኘው የዳውሮ ዞን ለአይን የሚማርኩ መልከዓ ምድር፣ ታሪካዊና ባህላዊ መስህቦች ባለቤት ስለመሆኑም አንስተዋል።

ኢትዮጵያውያን ለብዙ ስራዎች አእምሯችሁ እንዲከፈት የህዝብና አካባቢ ሰላም በእጅጉ በሚገኝበት የዳውሮ ዞን በመምጣት አዳዲስ ሀሳቦችን ለማፍለቅና ውስጣዊ ሰላም ለማግኘት የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነውን ሐላላ ኬላ ሪዞርት እንዲጎበኙም ጥሪ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሸትን በማለባበስ እውነት ማድረግ እንደማይቻልና ውሸትን ቀባብቶ እውነት ለማስመሰል መሞከር እንደ ሐላላ ኬላ ያሉ ፕሮጀክቶችን ለመፍጠር አያስችልም ሲሉም አክለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊት የብዙ ባህልና ቋንቋዎች መገኛ ሀገር ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህንን ብዘኃነት እንደራስ መቀበልን መለማመድ ያስፈልጋል ብለዋል።

እንደ ዋልታ ዘገባ፤ ኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ ሀገር ናት የምንለው በባህልና ቋንቋ ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮም እጅግ ማራኪ ሕብረ ብሔራዊ ቀለማትን በውስጧ የያዘች ሀገር መሆኗን መረዳት ያስፈልጋል፤ በዚህም አንዱ አካባቢ ከሌላው የተለየ የራሱ ተፈጥሯዊ ገፀ በረከቶችን የያዘ በመሆኑ በአግባቡ በማልማት መጠቀም እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

በመጨረሻም የዳውሮ ማህበረሰብ የሐላላ ኬላ ሪዞርት እንደቀደሙ አባቶች ቅርስ በመጠበቅ ለትውልድ እንዲያሸጋግርና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን እንዲያረጋግጥ አሳስበዋል።

@etconp