Get Mystery Box with random crypto!

በስንዴ እጥረት ምክንያት የዱቄት ፋብሪካዎች ስራ እያቆሙ ነው ተባለ (Via Ethio FM) | ᴇʟɪᴀꜱ ᴍᴇꜱᴇʀᴇᴛ

በስንዴ እጥረት ምክንያት የዱቄት ፋብሪካዎች ስራ እያቆሙ ነው ተባለ

(Via Ethio FM)

የፓስታና መኮሮኒ አምራች ፋብሪካዎች የስንዴ ምርት እጥረት ገጥሞናል፤ በዚህም ስራ ለማቆም ተገደናል እያሉ እንደሚገኙ ኢትዮ ኤፍኤም ዛሬ ዘግቧል።

የዱቄትና የዱቄት ውጤቶች አምራቾች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ሙሉነህ ለማ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት ስንዴ በአሁኑ ወቅት ኮንትሮባንድ ሆኗል፤ ማንም እንደፈለገ መግዛትም ሆነ መሸጥ አይችልም ብለዋል፡፡

መንግስት ለኤክስፖርት የሚሆን ስንዴን ለማግኘት ሲል ዩኒዮኖች ብቻ እንዲገዙ ፈቀደ፣ ለዱቄት አምራቾችም በዩኒዮኖች በኩል ታገኛላችሁ ተባሉ፣ በኋላም 12 ባለሃብቶች ተመርጠው ወደ ስራ ገቡ፣ ዱቄት አምራቾች ግን ስንዴ ሊያገኙ አልቻሉም ብለዋል፡፡

ይህ ችግር ከተፈጠረ 2 ወራትን አስቆጥሯል የሚሉት አቶ ሙሉነህ አምራቾች በእጃቸው ያለችውን ስንዴ እየቆጠቡ ሲጠቀሙ ቆይተው አሁን ላይ ስራ ማቆም ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህም በዳቦ ላይ የሚስተዋለው ጭማሬ እንዳለ ሆኖ የ1 ኪሎ መኮሮኒ ዋጋ ከ40 ብር ወደ 80 ብር ከፍ እንዲል አድርጎታል ነው የተባለው፡፡

እንደ አቶ ሙሉነህ ገለጻ በአሁኑ ወቅት ስንዴ እንደ ኮንትሮባንድ ተቆጥሮ በየኬላዎች በፍተሻ እየተያዘ ነው፡፡ በዚህም አምራቾች ገዝተው መተቀም አይችሉም፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች መጋዘን ላይ ስንዴ የተገኘባቸው ዱቄት ፋብሪካዎችም ሆነ ነጋዴዎች በህገ ወጥ መንገድ ግብይት ፈጽማችኋል በሚል ወከባ እየደረሰባቸው እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡

በመሆኑም ከሁሉም በፊት የሃገር ውስጥ ፍላጎትን ማሟላት ይቀድማልና ችግሩን ለመፍታት መንግስት ትኩረት እንዲሰጥ አቶ ሙሉነህ ጠይቀዋል፡፡

@EliasMeseret